የፈረሰችው ፒያሳ (የምስል ዘገባ)
ፒያሳ የተሟላ የከተማ ሕይወት መሠረት፣ መገለጫም ነበረች። ትያትር ቤቶች፣ ሙዚቃ ቤቶች ፣ የትዳር ቀለበት ፣ ሰዓት፣ መነጽር ፣ አልባሳት ቤቶች፣ በጥቅሉ የዘመናዊነት ምልክቶች ሁሉ ፒያሳ ውስጥ ነበሩ። አሁን ግን ፈርሳለች።
ከራስ መኮንን ድልድይ ወደ ሲኒማ አምፒየር ወርቅ ቤቶች የነበሩበት ስፍራ
በዚህ ስፍራ ውስጥ ታሪካዊ ኬክ ቤቶች ፣ ወርቅ ቤቶች፣ ልብስ መሸጫ ቤቶች ፣ ቡና ቤቶች ይገኙበት ነበር
የሀገር ፍቅር ትያትር በር
የአሁኑ የሀገር ፍቅር ትያትር ስያሜው ሀገር ፍቅር ማሕበር በሚል ነበር በ 1927 ዓ.ም የተመሰረተው። ማሕበሩ የተመሠረተበት ዋናው ዓላማም ፋሺስት ጣልያን ኢትዮጵያን ለመውረር መዘጋጀቱን ተከትሎ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለማንቃትና በአንድነት እንዲቆም ለማድረግ የተቋቋመ ነው። የሀገሪቱ አንቱ የተባሉ የኪነ ጥበብ ሰዎችም ታላላቅ ሥራዎችን የሠሩበት ነው።
ከራስ መኮንን ድልድይ አለፍ ብሎ የነበረ ግዙፍ ሕንፃ
የራስ መኮንን ድልድይ ለመጀመርያ ጊዜ በ 1903 በዐፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት በኖራ ግንብ የተሠራ ነው። ድልድዩን አለፍ ብሎ በታችኛው መስመር የሚገኘው ይህ ግዙፍ ሕንፃ ልዩ ልዩ ሱቆች የሚገኙበት ነበር ።
አራት ኪሎ የአርበኞች ሃውልት ፊህ ለፊት የነበረ ሕንፃ
የአራዳ እምብርት ከሆኑት ሥፍራዎች አንዱ የአራት ኮሎው የአርበኞ አደባባይ ሲሆን ዙሪያውን በትምህርት ሚኒስቴር፣ በጆሊ ባር የተከበበ ሲሆን ይህ ሕንፃ በአንደኛው አቅጣጫ የሚገኝ ነበር)
ሀገር ፍቅት ቲያትር አካባቢ
የሀገር ፍቅር ትያትር ከፋሽስት ጣልያን ወረራ በኋላ በ1933 የኢትዮጵያ ሕዝብ የሀገር ፍቅር ማሕበር ተብሎ በተንጣለለው ግቢ ቢዘልቅም ቅጥር ግቢው ሕጋዊ ካርታ ያገኘው ነሐሴ 9 ቀን፣ 2010 ዓ.ም ነበር። በቅርቡም እድሳት ተደርጎለታል። ሕዝብን በኪነ ጥበብ ለማነሳሳት የተቋቃመው ይህ የአሁኑ ትያትር ቤት የጥበብ ቤት ሆኖ የሀገሪቱን እንቁ የኪነጥበብ ባለሙያዎች አፍርቷል።
በመኮንን ባቅላባ ቤት አካባቢ
መኮንን ባቅላቫ ቤት በአዲስ አበባ ከተማ ለብዙ ባለትዳሮችና ፍቅረኞሞች የታሪካቸው አካል ነበር። ፒያሳ ላይ ለ63 ዓመታት የሠራው ይህ ቤት ከ1953 ዓም ጀምሮ እስከ 2016 ዓ .ም ብዙዎችን አገልግሏል። ዛሬ ታሪክ ሆኗል።
ጣይቱ ሆቴል አካባቢ የሚገኝ እድሜ ጠገብ ሆቴል
ጣይቱ ሆቴል በኢትዮጵያ የመጀመርያው ዘመናዊ ሆቴል ነው። አሁን በእድሳት ላይ ይገኛል። ከዚህ ሆቴል አጠገብ ብዙ ሆቴሎች፣ ምግብ ቤቴች እና ቡና ቤቶች ይገኛሉ። ከእነዚህ መካከል ይህ አንዱ ነበር።
ከአያሌው ሙዚቃ ቤት ፣ ወደ ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ አደባባይ
ድምፃዊ የግጥምና ዜማ ደራሲ እንዲሁም የሙዚቃ አቀናባሪ ነው፤ አንጋፋዉ አርቲስት አያሌዉ መስፍን። ወሎ የሙዚቃ ባለ ሙያዎችን የሙዚቃ ምሁራንን፤ ያፈራች መሆንዋን አብዛኞች ይመሰክሩላታል። «አያሌዉ መስፍን ሙዚቃ ቤት ጋር እንገናኝ» የብዙ ሰዎች የቀጠሮ ቃል ነበር።