1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጨፌ ኦሮሚያ ስድስተኛ መደበኛ ጉባኤ

ሰኞ፣ የካቲት 11 2016

የሰላምና ጸጥታን ጨምሮ የክልሉ አሁናዊ ጉዳዮች የተመከሩበት ጨፌ ኦሮሚያ ከትናንት ጀምሮ በአዳማ ከተማ ገልማ አባገዳ ሲያካሄድ የቆየውን ሦስተኛ ዓመት ስድስተኛ መደበኛ ጉባኤውን ዛሬ አጠናቋል። ጉባኤው የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ እና የዚህ ምክር ቤት አባል የነበሩትን የአቶ ታዬ ደንደዓ ያለመከሰስ መብትንም አንስቷል።

https://p.dw.com/p/4caE9
የጨፌ ኦሮሚያ ጉባኤ
የጨፌ ኦሮሚያ ስድስተኛ መደበኛ ጉባኤ ምስል Seyoum Getu/DW

የጨፌ ኦሮሚያ ስድስተኛ መደበኛ ጉባኤ

ጨፌ ኦሮሚያ ከትናንት ጀምሮ በአዳማ ከተማ ገልማ አባገዳ ሲያካሄድ የቆየውን ሦስተኛ ዓመት ስድስተኛ መደበኛ ጉባኤውን ዛሬ አጠናቋል። ጨፌው የክልሉ የሰላምና ጸጥታ ጉዳዮችን ጨምሮ የክልሉ አሁናዊ ጉዳዮች ላይም መክሯል። ጨፌ ኦሮሚያ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ እና የዚህ ምክር ቤት አባል የነበሩትን የአቶ ታዬ ደንደዓ ያለመከሰስ መብትንም አንስቷል። ጉባኤው ዛሬ በክልሉ መንግሥት ተጠሪ የቀረበለትን ስምንት ሹመቶችንም በማጽደቅ ተጠናቋል።

ስለሰላም እጦት የጨፌ አባላት ጥያቄ

ትናንት ተጀምሮ ዛሬ በተጠናቀቀው የጨፌ ኦሮሚያስድስተኛ ዘመን ሦስተኛ ዓመት ስድስተኛ መደበኛ ጉባኤ የበርካቶችን ትኩረት ከሳቡት እና የምክር ቤቱ አባላትም በስፋት ጥያቄ ካነሱበት የክልሉ አሁናዊ የሰላምና ፀጥታ ይዞታ ተጠቃሽ ነው። የምክር ቤቱ አባላት በጥያቄያቸው በክልሉ ዘላቂ ሰላም ሊወርድ ስለሚችልበት የመፍትሄ ሃሳብ አንስተዋል።

ከጠያቂዎቹ አንደኛው፤ «ህዝባችን በየጊዜው እየታፈነ ሰምቶ የማያውቀውን የብር መጠን እየተጠየቀ ይገኛል። አስከፊ እሮሮ ውስጥ ነው። በዚህ ላይ የጸጥታ ኃይሎች የሚያደርጉትን መስዋእትነት ማሳነስ አልፈልግም። ይህ መስዋእትነት ግን በተቀናጀ መልኩ እየተፈጸመ ስላልሆነ አሁንም ድረስ ህዝባችን ዋጋ እየከፈለ ነው። በዚህ ላይ የፖለቲከኞች እና የጸጥታ ኃይሎች ቅንጅት ተበጅቶ እልባት እንድገኝበት ለማለት ነው» ብለዋል።

ሌላም አስተያየት ሰጪ የጨፌ አባል ሃሳባቸውን ቀጠሉ። «የጸጥታ ችግር አሁን ላይ ያለብን ትልቁ ችግራችን ነው። ሰላም የሁሉም ልማትና እድገት መቋጫ ነው። ለዴሞክራሲ እድገትም ብሆን ሰላም ያስፈልገናል። በጸጥታ ኃይሎች፣ አመራሮቻችን እና ህዝባችን ላይ እየደረሰ ያለው የሰላም እጦት በእጅጉ የሚያስከፋ ሆኖ፤ እኔ ግን እደጥያቄ ማንሳት የምፈልገው እንደመንግሥት እያስተዳደርን ስለሆነ አስቀድሞ ሁኔታዎችን ተንትነን መዘጋጀት ላይ ምን እንመስላለን የምለውን ብታብራሩልን ለማለት ነው። ህዝባችን መረጋጋት እንዲያገኝ ምን እየተሠራ ነው። የሕግ የበላይነትን ለማስከበር ምን ሂደት አለ» ሲሉም ጠየቁ።

ጨፌ ኦሮሚያ
የጨፌ ኦሮሚያ ቃል አቀባይ ሰአዳ አብዱራህማን እንዲሁም ምክትል ቃል አቀባይ ኤልያስ ዑማታምስል Seyoum Getu/DW

ስለ ክልሉ የጸጥታ ችግሮች እልባት የክልሊ ባለሥልጣናት ምላሽ

በዚህ በክልሉ ሰላም መቼ ይሆን የሚሰፍነው በሚል ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ከሰጡት የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በምክትል ርዕሰ-መስተዳድር ማዕረግ የሰላም፣ አስተዳደር እና ፍትህ ክላስተር አስተባባሪ ኮሚሽነር ከፍያለሁ ተፈራ ይገኛሉ። «ተደራጅቶ ህዝብን ሲጠልፍ እና ሲገድል የሚውለውን ጠላት ለመቀልበስ የጸጥታ ኃይል ትልቅ ሥራ ሰርቷል። አስቸጋሪ የሆነብን ይህ ጠላት ሲመታ ተበትኖ ወደ ከተማ በመግባት እራሱን ይቀያይራል። ይሄ ኃይል ነው ህዝባችንን ሲዘርፍና ሲገድል የሚውለው። ይህን ችግር ከመሰረቱ ለመፍታት ህዝባችን በየቦታው እራሱን አደራጅቶ ታጥቆ ቀየውን መጠበቅ ነው የሚያስፈልገው። ካልሆነ ከችግሩ አንላቀቅም። የሚመለከተውን ሁሉ አቀናጅተን መሥራት ያስፈልጋል» ነው ያሉት።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳም በኦሮሚያ ክልል ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ወደ ሰላም እንዲመለሱ ነው የጠየቁት። «ዓላማውን ሳይገነዘቡ ታጥቆ በክልላችን የሚንቀሳቀሰውን ቡድን የተቀላቀሉት በሰላም እንዲገቡ እንጠይቃለን። ከዚህ ውጪ ግን ለጠላት መሳሪያ መሆናቸውን ይወቁ። ማንን ለመርዳት ነው ፕሮጀክት እንዳይገነባ የሚያወድሙት? የማን ትግል እንዲሰምር ነው የህዝብ መውጪ መግቢያ የሚዘጉት? አሳፋሪ ነው። ይህን የእርግማን ኃይል ከመሃላችን ለመንቀል ጠንክረን እንሠራለን» ብለዋልም።

ጨፌ ኦሮሚያ ዛሬ የሁለት ቀናት ጉባኤውን ሲያጠናቅቅ በቅርቡ በፌዴራል ፖሊስ ቁጥጥጥር ስር ውለው የታሰሩትን የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ እና የጨፌው አባል የነበሩትን የአቶ ታዬ ደንደዓን ያለመከሰስ መብት አንስቷል። በክልሉ ስምንት የኃላፊነት ቦታዎች ላይም አዳዲስ ሹመቶችን አጽድቋል።

ሥዩም ጌቱ 

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ