የጥቅምት 12 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ሰኞ፣ ጥቅምት 12 2016በቫሌንሺያ የግማሽ ማራቶን እልህ አስጨራሽ የሩጫ ፉክክር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ትናንት በኬኒያዊ አትሌት ለጥቂት ተቀድመዋል ። የኢትዮጵያሴቶች ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን (ሉሲዎቹ) ለ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ ሁለተኛ ዙር የመጀመሪያ ግጥሚያቸውን ከነገ በስትያ ያከናውናሉ ። ሉሲዎቹ ወደ 2ኛው ዙር ያለፉት ቻድን በመጀመሪያው ዙር በደርሶ መልስ ውጤት 10 ለ0 በማሸነፍ ነው ። በጀርመን ቡንደስሊጋ ኮሎኝ ትናንት የመጀመሪያ ድሉን አስመዝግቧል ። በዘንድሮ ስምንት የቡንደስሊጋ ጨዋታዎችም ቦሩሲያ ሞይንሽንግላድባኅን በሰፋ የግብ ልዩነት አሸንፎ አስደምሟል ። በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ፉክክሩ እጅግ ተጠናክሯል ። ማንቸስተር ሲቲ የመሪነት ቦታውን ሲረከብ ቼልሲ እና አርሰናል አቻ ወጥተዋል ። ተስተካካይ ጨዋታውን ዛሬ ማታ የሚያደርገው ቶትንሀም እና ሊቨርፑል በተመሳሳይ ነጥብ ከማንቸስተር ሲቲ እና ከአርሰናል በአንድ ነጥብ ብቻ ተበልጠው ተደርድረዋል ።
አትሌቲክስ
ስፔን ውስጥ ትናንት በተከናወነው የቫሌንሺያ የግማሽ ማራቶንየሩጫ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በኬኒያዊው ኪብዎት ካንዲዬ ለጥቂት ተቀደሙ ። ዮሚፍ ቀጄልቻ፣ ሀጎስ ገብረሕይወት እና ሰለሞን ባረጋ በትናንቱ ውድድር 2ኛ፣ 3ኛ እና 4ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቀዋል ። ሰለሞን እና ሀጎስ ከሦስት ሳምንት በፊት በላቲቪያ ሪጋ በነበረው የ5 ኪሎ ሜትር ርቀት ፉክክር 1ኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ይዘው በማሸነፍ ታላቅ ድል አስመዝግበው ነበር።
ኬኒያዊው ኪብዎት ካንዲዬ በትናንቱ ፉክክር አሸናፊ የሆነው 57 ደቂቃ ከ40 ሰከንድ በመሮጥ ነው ። 2ኛ ደረጃ የያዘው ዮሚፍ ቀጄልቻ በኬንያዊው የተቀደመው በአንድ ሰከንድ ብቻ ነበር ። ሀጎስ ገብረሕይወትም ከዮሚፍ በሽርፍራፊ ሰከንዶች ብቻ ተቀድሞ ሲገባ፤ ሰለሞን ባረጋ ከኬኒያዊው 10 ሰከንዶች በኋላ በመግባት አጠናቋል ። ኬንያውያን አትሌቶች፦ ከአምስተኛ እስከ 11ኛ ደረጃ ተከታትለው ሲይዙ ኢትዮጵያዊው ታደሰ ወርቁ ስፔናዊውን ካርሎስ ማዮ አስከትሎ በ12ኛ ደረጃ አጠናቋል ። በውድድሩ በአብዛኛው የተሳተፉት የስፔን አትሌቶች ናቸው ።
በሴቶች ተመሳሳይ ፉክክር፦ ኬኒያውያን ከ1ኛ እስከ 3ኛ ደረጃ በመያዝ አሸናፊ ሆነዋል ። ኢትዮጵያውያቱ ጎይተቶም ገብረሥላሴ እና ትእግስት ገዛኸኝ 4ኛ እና 5ኛ ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል። ለጀርመን የምትሮጠው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ሜላት ይሳቅ 6ኛ ደረጃ አግኝታለች ። በዚህ ውድድር አሸናፊ የሆነችው ኬኒያዎት ሯጭ ማርጋሬት ቼሊሞ ውድድሯን ለማጠናቀቅ የፈጀባት 1 ሰአት ከ4 ደቂቃ ከ46 ሰከንድ ነበር ። ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ንግሥቲ ሀፍቱ የብሪታንያዋ ሯጭ ሳማንታ ሐሪሰንን ተከትላ የ8ኛ ደረጃ አግኝታለች ።
እግር ኳስ
የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን (ሉሲዎቹ) ለ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ ሁለተኛ ዙር ማጣርያ ግጥሚያቸውን ከናይጄርያ ጋር ከነገ በስትያ አዲስ አበባ ውስጥ ያከናውናሉ ። የመልሱ ጨዋታ ናይጄሪያ አቡጃ ከተማ ውስጥ ጥቅምት 20 ይካሄዳል ። ሉሲዎቹ አምስተኛ ቀን ልምምዳቸውን ትናንት በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ አከናውነዋል ። ቀላል ጉዳት ገጥሟት የነበረችው ኒቦኒይ የን ከቡድኑ ጋር ተቀላቅላ ልምምድ ጀምራለች ። በኦሊምፒክ ሴቶች እግር ኳስ ማጣርያ የመጀመርያ ዙር ኢትዮጵያ ቻድን በደርሶ መልስ ውጤት 10 ለ0 በማሸነፍ ወደ 2ኛው ዙር መሸጋገሯ የሚታወስ ነው ።
የጥቅምት 5 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የስፖርት ዘገባ
ከመጀመሪያው ዙር በደርሶ መልስ ግጥሚያ ያሸነፉ ዘጠኝ ቡድኖች በአፍሪቃ ከፍተኛ ደረጃ የተሰጣቸው ሰባት ቡድኖችን ይቀላቀላሉ ። ከሰባቱ ከፍተኛ ግምት የተሰጣቸው ቡድኖች መካከል ከሉሲዎቹ ጋር የሚጋጠመው የናይጀሪያ ቡድን ይገኝበታል ። ከናይጀሬያ በተጨማሪ በዚህ ሁለተኛ ዙር የማጣሪያ ግጥሚያ ውስጥ፦ ደቡብ አፍሪቃ፣ ሞሮኮ፣ ዛምቢያ፣ ካሜሩን፣ ቱኒዝያ እና ቦትስዋና ይገኙበታል ። በዚህ ዙር በደርሶ መልስ የጥሎ ማለፍ ግጥሚያ ማሸነፍ የቻሉ ስምንት ቡድኖች በሦስተኛው ዙር የደርሶ መልስ የማጣሪያ ግጥሚያ ይፋለማሉ ። በመጨረሻው እና በአራተኛው ዙር የማጣሪያ ግጥሚያ አራት ቡድኖች ተወዳድረው ሁለት ቡድኖች ለ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ ግጥሚያ አፍሪቃን ወክለው የሚያልፉ ይሆናሉ ማለት ነው ።
ፓሪስ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2024 ለምታዘጋጀው የኦሎምፒክ ጨዋታዎች የሚሆን የአትሌቶች መንደር መረጣዋ አስተችቷታል ። ለአትሌቶች መንደርነት ከፓሪስ አቅራቢያ የተመረጠው ቦታ ከፈረንሳይ በድህነት ከሚታወቁ መንደሮች አብዛኞቹ የሚገኙበት ነው ። በዚህች ሰሜን እና ሰሜን ምሥራቅ የፓሪስ ከተማ አቅጣጫ በርካታ መንደሮችን ባቀፈችው ሴን-ሳን-ዴኒ በተሰኘችው አካባቢ 14,500 የኦሎምፒክ እና 6,000 የፓራሊምፒክ አትሌቶች መኖሪያ እየተገነባ ነው ። የአካባቢው ባለሥልጣናት ግንባታው የአካባቢውን የኑሮ ሁኔታ ይቀይራል የሚል ተስፋ ሰንቀዋል ። ነዋሪዎች በተቃራኒው ከወዲሁ ፍራቻ ገብቷቸዋል ። ወትሮም ድህነት ለኑሮ አስቸጋሪ ባደረጋት ሴን-ሳን-ዴኒ መንደር የኑሮ ውድነቱ እጅግ ያሻቅባል ተብሎም ተፈርቷል ።
እንደ ሉሲዎቹ ሁሉ እድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች ተጫዋቾች ለሴቶች ዓለም ዋንጫ ማጣርያ የትናንት ሳምንት ያስመዘገቡት ድል የሴቶች እግር ኳስ ኢትዮጵያ ውስጥ ከፍተኛ ትኩረት የሚያሻው ለመሆኑ አመላካች ነው ። ከ20 ዓመት በታች ተጫዋቾች የኢትዮጵያ የሴቶች ቡድን የእሁድ ሳምንት አበበ ቢቂላ ስታዲየም ውስጥ ከኢኳቶርያል ጊኒ ጋር ባደረገው ግጥሚያ 4 ለ1 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት ድል ማድረጉ አይዘነጋም ። ብሔራዊ ቡድኑ በቀጣይ ከማሊ አቻው ጋር ይጋጠማል ።
ፕሬሚየር ሊግ
በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ፦ ዛሬ ማታ ቶትንሀም በሜዳው ወሳኝ ግጥሚያ ይጠብቀዋል ። ቶትንሀም ፉልሀምን ካሸነፈ ነጥቡን 23 በማድረስ በፕሬሚየር ሊጉ የመጀመሪያውን ደረጃ ከማንቸስተር ሲቲ ይረከባል ማለት ነው ።
5ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አስቶን ቪላ ትናንት ዌስትሀም ዩናይትድን 4 ለ1 ድል አድርጎታል ። ነጥቡንም 19 አድርሶ ከመሪው ማንቸስተር ሲቲ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ 3 አጥብቧል ። ቅዳሜ ዕለት በነበሩ ግጥሚያዎች፤ ማንቸስተር ዩናይትድ ሼፊልድ ዩናይትድን እንዲሁም ማንቸስተር ሲቲ ብራይተንን 2 ለ1 አሸንፈዋል ። የጨዋታው መደበኛ 90 ደቂቃ ተጠናቆ በጭማሪው 5ኛ ደቂቃ ላይ የማንቸስተር ሲቲ ማኑዌል አካንጂ የብራይተን ተጨዋች መለያ ጎትቶ በመጣሉ በሁለት ቢጫ ካርድ በቀይ ከሜዳ ተሰናብቷል ። ቼልሲ እና አርሰናል ሁለት እኩል በመውጣት ነጥብ ተጋርተዋል ። ኒውካስል ክሪስታል ፓላስን 4 ለ0 በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት ድል አድርጓል ። የፕሬሚየር ሊጉ በርካታ ቀይ ካርዶች የታዩበት ነበር ። በርመስ፣ በርንሌይ እና ኤቨርተን እንደ ማንቸስተር ሲቲ ተጨዋቾቻቸው በቀይ ካርድ ከሜዳ ተአናብቶባቸዋል ። በርመስ በዎልቨርሀምፕተን የ2 ለ1 ሽንፈት ሲያስተናግድ ፤ ብሬንትፎርድ በርንሌይን 3 ለ0 አሸንፏል ። ኖቲንግሀም ከሉቶን ታውን ጋር ሁለት እክኩል ተለያይቷል ። ሊቨርፑል ቅዳሜ ዕለት በጨዋታም በልጦ ኤቨርተንን 2 ለ0 አሸንፏል ።
የፕሬሚየር ሊግ የሳምንቱ ጨረሻ ግጥሚያዎች ላይ ለሰር ቦቢ ቻርልተን መታሰቢያ ተጨዋቾች በክርናቸው ላይ ጥቁር ሪባን አስረው ታይተዋል ። የእንግሊዝ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን የቀድሞ ተጨዋች እና በሀገሪቱ ስፖርት አፍቃሪ ዘንድ እንደ ጀግና የሚታየው ሰር ቦቢ ቻርልተን ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ በ86 ዓመቱ አርፏል ። እንደ ጎርሪዮስ አቆጣጠር በ1996 እንግሊዝ የያኔው የጀርመን ቡንደስ ሪፐብሊክ ቡድንን በዓለም ዋንጫ ፍጻሜ በጭማሪ ሰአት 4 ለ2 ያሸነፈችበት ግጥሚያ የሰር ቦቢ ታላቁ ስኬት ነው ። ሰር ቦቢ ቻርልተን በዚiwe ዓመት የአውሮጳ ምርጡ የዓመቱ ተጨዋች ተብሎ ተመርጦ ነበር ።
ቡንደስሊጋ
የባዬር ሙይንሽን አሰልጣኝ ቶማስ ቱሁል በአውሮጳ ንፍቀ ክበብ የክረምት ወራት ረፍት ከመጀመሩ በፊት አዳዲስ ተጨዋቾች እንዲመጡላቸው አስተዳደሩን ጠይቀዋል። የባዬርን ሙይንሽን የክብር ፕሬዚደንት ዑሊ ሆይነስ የአሰልጣኙን ጥያቄ «ብልህነት የጎደለው» ሲሉ አጣጥለዋል ። የጀርመን ብሔራዊ ቡድን የቀድሞው ተጨዋች ዲይትማር ሐማን በበኩሉ የአሰልጣኙን ተደጋጋሚ ጥያቄ አጥብቆ ተችቷል ። በእርግጥም የአውሮጳ ተደጋጋሚ ባለድል የሆነው ቡድን ባዬርን ሙይንሽን አንድ ሁለት ተጨዋቾች ማስመጣቱ እንደማይቀር የ50 ዓመቱ ዲይትማር ተናግሯል ። ሆኖም እስከ ክረምት ረፍት ድረስ ያሉት ጨዋታዎች እየተገባደዱ መሆናቸውን በመጠቆም፦ «ይሄን ማብቂያ የሌለው ንጭንጭ ከእንግዲህ መስማት አልችልም» ሲል ለስካይ (Sky90) ጣቢያ ተናግሯል ።
የመስከረም 28 ቀን 2016 ዓ/ም የስፖርት ዝግጅት
በጀርመን ቡንደስሊጋ የሳምንቱ መጨረሺያ ግጥሚያ፦ ባዬር ሙይንሽን ማይንትስን በሜዳው 3 ለ1 አሸንፎ ነጥቡን 20 አድርሷል ። በደረጃ ሰንጠረዡ ላይም 3ኛ ነው ። የቅዳሜውን ግጥሚያ በተመለከተ አሰልጣኝ ቶማስ ቱኁል እንደተጠበቀው ውጥረት የተሞላበት ግጥሚያ እንደነበር ተናግረዋል ።
«እንደተጠበቀው ውጥረት የሞላበት ከባድ ግጥሚያ ነበር ። መጀመሪያ ላይ ሁለት ግቦችን በፍጥነት በማስቆጠር እጅግ በጣም ውጤታማ ነበርን ። ከዚያ በኋላም ጨዋታውን ለማፍጠን ጥሩ ሁኔታዎች ተመቻችቶልናል ። በእርግጥ በቀጣይ ደቂቃዎችም ሦስተኛ ግብ ለማስቆጠር ጫፍ ደርሰን ነበር ። የመጨረሺያ ኳስ በማቀበሉ ረገድ ትንሽ ኢፍጹማዊነት ተስተውሏል ። ትንሽ ብቻ ። አለ አይደል ምናልባት ጨዋታውን ስልቱን ቀይሮ ግብ ለማስቆጠር በድጋሚ ትልቅ አጋጣሚ የመፍጠር ነገር ። »
በቡንደስሊጋው ሽቱትጋርት በ21 እንዲሁም ባዬር ሌቨርኩሰን በ22 ነጥብ የመሪነቱን ስፍራ ይዘዋል ። ኮሎኝ እስካሁን ካደረጋቸው ከስምንት ግጥሚያዎች ትናንት በመጀመሪያ የዘንድሮ የቡንደስሊጋ ድሉ ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅን 3 ለ1 አሸንፎ አስደምሟል ። ቦሩስያ ሞይንሽንግላድባኅ በ72ኛው ደቂቃ ላይ ማኑ ኮኔ በቀይ ካርድ ከሜዳው ተሰናብቶበታል ። ኮሎኝ ትናንት ድል ቢቀዳጅም በ4 ነጥቡ ግን ወራጅ ቀጣናው ውስጥ ተወስኗል ። ቦሁም ተመሳሳይ 4 ነጥብ ይዞ 17ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ፤ ማይንትስ በ2 ነጥብ ወራጅ ቀጣናው ግርጌ ስር ተዘርግቷል ።
ሐይደንሀይም በሜዳው ትናንት አውግስቡርግን ገጥሞ የ5 ለ2 ሽንፈት አስተናግዷል ። በ17 ነጥቡ 5ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ላይፕትሲሽ ዳርምሽታድትን እንዲሁም ፍራንክፉርት ሆፈንሀይምን በተመሳሳይ በሜዳቸው 3 ለ1 አሸንፈው ተመልሰዋል ። ሆፈንሀይም በ15 ነጥብ ከላይፕትሲሽ ስር 6ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ቮልፍስቡርግ በባዬርን ሌቨርኩሰን የ2ለ1 ሽንፈት አስተናግዷል ። ፍራይቡርግ ቦሁምን 2 ለ1 አሸንፏል ። ዑኒዮን ቤርሊን በሜዳው በሽቱትጋርት የ3 ለ0 ሽንፈት ሲገጥመው፤ ቦሩስያ ዶርትሙንድ በጠበበ ሁኔታ ቬርደር ብሬመንን 1 ለ0 አሸንፏል ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ