1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዩናይትድ ስቴትስ አፍሪቃ ጉባኤ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 4 2015

የአፍሪቃና ዮናይትድስቴትስ መሪዎች ጉባዔ ከነገ ጀምሮ ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ ይካሄዳል። በአትላንቲክ ካውንስል የአፍሪቃ ማዕከል ከፍተኛ ባልደረባ አቶ ገብርኤል ንጋቱ በተለይ ለዶይቸ ቨለ እንዳስታወቁት፣ ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ይኸው የመሪዎች ጉባዔ ላይ አፍሪቃና አሜሪካ በጋራ ጉዳዮቻቸውና ጥቅሞቻቸው ላይ ይመክሩበታል ተብሎ ይጠበቃል።

https://p.dw.com/p/4KpvW
US-Afrika Gipfel in Washington/Ankunft
ምስል Saul Loeb/AFP

የአፍሪቃ አሜሪካ ትብብር

አቶ ገብርኤል እንዳሉት፣ የመሪዎቹ ጉባዔ አሜሪካ ከአፍሪቃ አጋሮቿ ጋር በጋራ መከባበርና ፍላጎት ላይ የተመሰረተ ጥቅሞቿን ለማጠናከር ይረዳል ተብሎ ይጠበቃል። «የዩኤስ አፍሪቃ ጉባዔ ኦፊሻሊ የሚሉት፣ የአፍሪቃና የዩናይትድስቴትስ ግንኙነት ክብደቱን የሚያሳይ ነው። መሪዎች ተሰብስበው ከአሜሪካው መሪ ጋራ መገናኘታቸው ይሄ በፕሬዚዳንት ኦባማ ጊዜ የተጀመረ ልምድ ነው፤ እና እኚህም ፕሬዚዳንት ቀጥለውበታል እና በኮቪድ ጊዜ ያው ተቋርጦ ነበር። በየጊዜው እየተገናኙ ምንድነው የጋራ ጥያቄዎቻችን ፍላጎታችን የሚለውን ለመነጋገር ነው።»

ከጉባዔው ዓላማዎች መኻከል፣ አዲስ ምጣኔ ሃብታዊ ተሳትፎን ማዳበር፣ ለዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶች የአሜሪካና አፍሪቃን ግንኙነት ማጠናከር የሚሉ ይገኙባቸዋል። የኮቪድ 19 እና የወደፊት ወረርሽኞችን ተጽእኖ መቀነስ፣ የምግብ ዋስትናን ማስተዋወቅ፣ ሰላምና ደህንነትን ማሳደግ፣ ለአየር ንብረት ቀውስና ምላሽ መስጠትና በውጭ የሚኖሩ ዜጎችን ትስስር የማጠናከር ግቦችንም ወጥኗል። በወቅታዊ አንገብጋቢ ዓለም አቀፍና የሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ውይይት የሚካሄድበት ይኸው የመሪዎች ጉባዔ፣ለኢትዮጵያ ያለውን ፋይዳ አስመልክቶ የጠየቅናቸው፣ በአትላንቲክ ካውንስል የአፍሪቃ ማዕከል ከፍተኛ አባል የሚከተለውን መልሰዋል።

«ከነበርንበት ጦርነት ወጥተን፣ ኢትዮጵያ ሰላም ፈላጊ መሆኗን አሳይታ፣ የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ በቀጥታ ትግበራ የገባችበች ጊዜ ስለሆነ፣ ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ በተለይ ለአሜሪካኖቹ ሁሌ ኢትዮጵያን በሆነው ባልሆነው አንዳንዴም በሆነ ባልሆነው የሚወነጅሏት፣ የኢትዮጵያን ማንነት ፍንትው ብሎ እንዲያዩ ሆኗል። ሰላም ፈላጊ መሆኗ ሰላም ስምምነት ከተፈረመም በኋላ ወዲህ ወዲያ ባለማለት ቀጥ ብላ ወደትግበራው መግባቷና ለሰላም እንደቆመች ማሳያ ድል ነው። በመሰረቱ መቼም ምንም ጊዜ ቢሆን በዴሞክራሲ ሳያቋርጡ መነጋገር ይጠቅማል፤ ከመኮራረፍና ከመገለል ይልቅ ተገናኝቶ መነጋገር ይጠቅማል።»

USA Washington | Freilassung Brittney Griner | Statement Joe Biden, Präsident | & Cherelle Griner, Ehefrau
ፕሬዝደንት ጆ ባይደንምስል Jonathan Ernst/REUTERS

አሜሪካ፣ የአፍሪቃ አገሮች በዓለም ላይ ፈጣን የህዝብ ቁጥር ዕድገት፣ ትልልቅ ነጻ የንግድ ቀጣናዎች፣የተለያዩ ስነ ምህዳርና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ከፍተኛ ድምጽ በመያዛቸው ምክንያት፣ያለአፍሪቃውያን አስተዋጽኦ፣ አጋርነትና አመራር  የዚህን ዘመን ተግዳሮቶች መወጣት አይቻልም በሚል እንቅስቃሴዋን ተያይዛዋለች። ይሁንና ሌሎች ዓለማትም ከአፍሪቃ ጋር ያላቸውን ወዳጅነት ለማጠናከር ውድድር ውስጥ መግባታቸው፣ አህጉሪቱም ወደ ሌሎች አማራጮች ማማተሯ አልቀረም። ለአብነትም፣ በቅርቡ በሱዳን ኻርቱም የተካኼደው የምሥራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት /ኢጋድ/ የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ፣ ከምሥራቁ ዓለም ጋር ያለው ግንኙነት መጠናከር እንደሚገባው አጀንዳ ይዞ መምከሩ፣ ለአሜሪካ የማስጠንቀቂያ ምልክት ተደርጎ እንደሚታይ አቶ ገብርኤል ይናገራሉ።

«አፍሪቃውያኖች ዝም ብሎ አሜሪካንን ወይም ምዕራቡን ዓለም ብቻ ሳይሆን ምሥራቁንም በእኩልነት አስከጠቀማቸው ድረስ ወደዛም ማየት ማነጋገር ለመገናኘት ፈቃደኞች ናቸው። እያሰቡም ነው የሚለው ትልቅ ማስጠንቀቂያ ነው ለአሜሪካኖች፤ እዛ ሁሉ ላይ ኢትዮጵያ ሚና አላት።»

ኢትዮጵያን ጨምሮ የ49 የአፍሪቃ መሪዎች በጉባዔው ላይ እንደሚገኙ የተጋበዙ ሲሆን፣ በአፍሪቃ ኅብረት የታገዱና የአሜሪካ መንግሥት ዕውቅና የማይሰጣቸው አገሮች፣ የፕሬዚዳንት ባይደን የጥሪ ወረቀት አልተላከላቸውም። የወቅቱን ወሳኝ ፈተናዎች በትብብር ለመወጣት የአፍሪቃን ድምጽ ማጉላት፣የጋራ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮችን ለማራመድ የአፍሪቃ አሜሪካን አጋርነት ማጠናከርና ማስፋፋት ከጉባዔው የሚጠበቁ ውጤቶች መካከል መሆናቸው ታውቋል።

ታሪኩ ኃይሉ 

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ