1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ፈቃድ

ረቡዕ፣ መስከረም 29 2017

“ባንክ ያልሆኑ የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ይቋቋማሉ። ለነዚህ ባንክ ላልሆኑ የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎችም በገበያ ዋጋ የውጭ ምንዛሪ ጥሬ ገንዘብ እንዲሸጡና እንዲገዙ ሕጉን ተከትለው ለብሔራዊ ባንክ ሲያመለክቱ ብቻ እንዲሰሩ የስራ ፈቃድ ይሰጣቸዋል።“ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ ማሞ ምህረቱ

https://p.dw.com/p/4lXld
ባንክ ላልሆኑ 5 የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች የሥራ ፈቃድ መሰጠቱን
ባንክ ላልሆኑ 5 የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች የሥራ ፈቃድ መሰጠቱንምስል Napoli/Giacomino/ROPI/picture alliance

የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ፈቃድ

መንግስት በቅርቡ የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ማድረጉ ይታወቃል። ከዘርፈብዙ የማሻሻያ ፖሊሲዎች አንዱ የውጭ ምንዛሪ ተመን በገበያ እንዲወሰን ማድረግና በመደበኛ ባንኮችና በትይዩ የጥቁር ገበያ ያለውን የውጭ ምንዛሪ ለማጥበብ ባንክ ላልሆኑ የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ፈቃድ መስጠት ይገኝበታል። በዚሁም መሰረት ብሔራዊ ባንክ ሰሞኑ ለ5 የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ፈቃድ ሰጥቷል። 
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ለውጡ ካካተታቸው
የውጭ ምንዛሪ አስተዳደር ሥርዓቱበባንኮችና በደንበኞቻቸው መካከል በሚደረጉ መስተጋብሮች ወደሚወሰንበት የገበያ ሥርዓት ይሸጋገራል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሚና የተረጋጋና ጤናማ የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት መስፈኑን ማረጋገጥ ላይ ያተኮረ ይሆናል። ከእንግዲህ ወዲያ የውጭ ምንዛሪ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የማስተላለፍ ግዴታ ቀሪ ሆኗል። በመሆኑም ላኪዎችና ንግድ ባንኮች ያፈሩትን የውጭ ምንዛሪ ለራሳቸው ማስቀረት ይችላሉ። ይህም ለግል ዘርፉ የሚሰጠውን የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት በእጅጉ እንደሚያሻሽል ይታመናል።“
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ ማሞ ምህረቱ የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያ ፖሊሲው ያካተታቸውን ለውጦችን ይፋ ባደረጉበት ወቅት ከተናገሩት የተወሰደ። ይህ የተማከለና ውስብስብ የውጭ ምንዛሪ ስርዓትን በማስቀረት የውጭ ምንዛሪ የሚያስፈልጋቸው አምራቾችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በገበያ በሚወሰን የውጭ ምንዛሪ በቀላሉ በማግኘት ኢኮኖሚውን ያነቃቃዋል ተብሎ እንደሚታመን ተነግሯል።

ባንክ ላልሆኑ 5 የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች የሥራ ፈቃድ መሰጠቱን
የዚህ ፖሊሲ አካል የሆነውን የውጭ ምንዛሪ አገልግሎትባንክ ላልሆኑ የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች የሥራ ፈቃድ ለመስጠት የፖሊሲ ማሻሻያ መደረጉንም አቶ ምህረቱ አስረድተዋል።
“አሁን ስራ ላይ ካሉና በባንኮች ከተቋቋሙ የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች በተጨማሪ ባንክ ያልሆኑ የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች ይቋቋማሉ። ለነዚህ ባንክ ላልሆኑ የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎችም በገበያ ዋጋ የውጭ ምንዛሪ ጥሬ ገንዘብ እንዲሸጡና እንዲገዙ ሕጉን ተከትለው ለብሔራዊ ባንክ ሲያመለክቱ ብቻ እንዲሰሩ የስራ ፈቃድ ይሰጣቸዋል።“

ይህን የፖሊሲ ማሻሻያን ተከትሎ ሰሞኑ ባንክ ላልሆኑ 5 የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች የሥራ ፈቃድ መሰጠቱንም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይፋ አድርጓል።
እነዚህ ቢሮዎች ያለ ጉምሩክ ዲክለራሲዮን ከደንበኞች እስከ 10 ሺህ የአሜሪካን ዶላር፣ የጉምሩክ ፈቃድ ከሚያቀርቡት ደግሞ ከዚያ በላይ የውጭ ምንዛሪ በጥሬ ገንዘብ መግዛት እንደሚችሉ፤ በተጨማሪም ተፈላጊ የጉዞ  መረጃ ላላቸው የግል ተጓዦች እስከ 5 ሺህ የአሜሪካን ዶላር፤ ለንግድ ሥራ ተጓዦች ደግሞ እስከ 10 ሺህ የአሜሪካን ዶላር በጥሬ ገንዘብ መሸጥ እንደሚችሉ በመመሪያው ተካቷል።
ባንክ ያልሆኑት የውጭ ምንዛሪ ፈቃድ ያገኙት ቢሮዎች ሥራውን ለማከናወን 15 ሚሊዮን ብር ካፒታል እና በባንክ በዝግ ተቀማጭ የተደረገ 30 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልጋቸው  ተገልጿል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በአሠራሩ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እና ክትትል እንደሚያደርግም አስታውቋል። 

 የፈቃዱ አሰጣጥ አንደኛው ዓላማ በጥቁር ገበያው ያለውን የውጭ ምንዛሪ ተመን ማቀራረብ እንደሆነ ታውቋል።
የፈቃዱ አሰጣጥ አንደኛው ዓላማ በጥቁር ገበያው ያለውን የውጭ ምንዛሪ ተመን ማቀራረብ እንደሆነ ታውቋል።ምስል Seyoum Getu/DW

በጥቁር ገበያው ያለውን የውጭ ምንዛሪ ተመን ማቀራረብ
የምጣኔ ሐብት ባለሙያው አቶ ዋሲሁን በላይ የፈቃዱ አሰጣጥ አንደኛው ዓላማ በጥቁር ገበያው ያለውን የውጭ ምንዛሪ ተመን ማቀራረብ እንደሆነ ለዝግጅት ክፍላችን ተናግሯል። ይህን ዓላማም እስከአሁን ባለው መረጃ መሰረት የተሳካ እንደሆነ ይገልጻሉ።
“ከትልልቅ ማዕቀፎቹ አንዱ ዩኒፊኬሽን መፍጠር ነው። ምክንያቱም የውጭ ምንዛሪን ማስተዳደር የሚያስፈልግ ከሆነ ሁለት ገበያ በጣም በሰፊው ማንቀሳቀስ አስቸጋሪ ነው፤ ባንኩም ጥቁር ገበያውም። ስለዚህ ዩኒፊኬሽን መፍጠር እንደአንድ ግብ ይዞ ነበር። በጥቁር ገበያና በመደበኛ ባንኮች ያለው ምንዛሪ ማቀራረብ የሚል። ስለዚህ ዩኒፊኬሽን በመፍጠር ደረጃ እንዳሳካ ነው። “
ማሻሻያውን ተከትሎ ባለፉት ሁለት ወራት በባንኮችና በትይዩ ገበያ ያለውን የውጭ ምንዛሬ ልዩነት ወደ 3 በመቶ ዝቅ ማድረግ መቻሉን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መረጃ ያመላክታል። ይህም ጤናማ ሊባል የሚችል አፈጻጸም እንደሆነ ባንኩ ያስረዳል።
የውጭ ምንዛሪ የፖሊሲ ማሻሻያው በመደበኛ ባንኮችና በትይዩ የጥቁር ገበያ ያለውን የምንዛሪ ተመን ማቀራረረብ እንደግብ ብቻ መውሰድ በቂ እንዳይደለ ግን ዓለም አቀፍ ልምዶች ያመላክታሉ። የጥቁር ገባያው ለውጡን ተከትሎ በተጋነነ ልዩነት ቢያሻቅብና የመደበኛ ባንኮችም አብረው በተመሳሳይ መጠን ቢያሻቅቡ እንደስኬት መውሰድ እንደማይቻል የምጣኔ ሐብት ባለሙያው አቶ ዋስይሁን ያስረዳሉ።

የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸምን ተከትሎ በባንኮች ያለው የውጭ ምንዛሬ ክምችት በ80 በመቶ መጨመሩን  የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ተናግረዋል።
የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸምን ተከትሎ በባንኮች ያለው የውጭ ምንዛሬ ክምችት በ80 በመቶ መጨመሩን  የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ተናግረዋል።ምስል CC BY 2.0/U.S. Institute of Peace


በባንኮች ያለው የውጭ ምንዛሬ ክምችት ማደግ
የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸምን ተከትሎ በባንኮች ያለው የውጭ ምንዛሬ ክምችት በ80 በመቶ መጨመሩን  የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ተናግረዋል። ይህም የነበረውን  የውጭ ምንዛሬ እጥረት ትርጉም ባለው መልኩ እንዲቀረፍ ማድረጉን በማከል። የምጣኔ ሐብት ባለሙያው ይህን ሐሳብ ይጋራሉ። ነገር ግን ለግል ባለሐብቱ በሚፈለገው መልኩ እያቀረቡ ካልሆነም ክምችቱ ሊያድግ እንደሚችል ጠቁመዋል።
“የሪዘርቡ ማደግ ምንን ሊያሳይ ይችላል? ክምችቱ ወደባንክ መጥቶ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን LC ለከፈቱ ለግል ሴክተሩ በተገቢው ሁኔታ የሚያቀርቡ ካልሆነም መከማቸቱም አይቀርም።“

የውጭ ባንኮች መግባት
የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ  ፖሊሲ ማሻሻያው የውጭ ባለሐብቶች በፋይናንሳዊ ሥራዎች እንዲሳተፉም ይፈቅዳል። ይህ የራሱ የሆነ መልካም ዕድልና ፈተናዎች ሊያስከትል እንደሚችል የምጣኔ ሐብት ባለ ሙያዎች ያስረዳሉ። አቶ ዋሲሁን
“የውጭ ባንኮች ይገባሉ ማለት የፋይናንስ አቅም ሊኖራቸው ይችላል ብሎ ማሰብ ይቻላል። የቴክኖሎጂ አቅም ያላቸው ሊሆኑ እንደሚችሉ፤ የማነጅመንት ኮምፒተንሲ ሊኖራቸው እንደሚችሉ ማሰብ ይቻላል። ስለዚህ እነዚህን አቅሞች ይዘው መጡ ማለት ፉክክር ሊኖር ይችላል። ፉክክር ሚኢኮኖሚ ውስጥ የሚፈጥረው በጣም ብዙ ኢነርጂ አለ። ይህ ኢነርጂ ኢኮኖሚውን ሊያግዘው እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለው “ 
እንደ ተግዳሮት ከሚወሰዱ ጉዳዮች አንዱ ፉክክሩን መሸከም የሚችሉ ባንኮች ላይኖሩን ይችላሉ የሚል እንደሆነ የገለጹት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ባንኮቹ በመዋሐድ የካፒታልና የቴክኖሎጂ አቅማቸውን በማሳደግ ተወዳዳሪ ሊሆኑ እንደሚችሉ ያስረዳሉ። ሌላኛው ተግዳሮት ደግሞ የውጭ ባንኮች ያጠራቀሙት ካፒታል ይዘውት ሊወጡ ይችላሉ የሚል ሲሆን ለዚህም ብሔራዊ ባንክ ጠንካራ የክትትል ሥርአት ካበጀ ትርጉም ያለው ተጽዕኖ ላይፈጥር ይችላል ሲሉ ባለሙያው ያብራራሉ።

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር

ኂሩት መለሰ