1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የወባ በሽታ ስርጭት በጊምቢ ወረዳ

ዓርብ፣ ሚያዝያ 11 2016

በምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ የወባ በሽታ መስፋፋቱና ከ200 በላይ ሰዎች በወባ መታመማቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ። በዚህ ቶሌ በተባለው አካባቢ የሚገኙ ዜጎች የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ ተፈናቅለው ወሎ እና ደብረብርሃን ቆይቶ በየካቲት ወር 2016 መጀመሪያ ላይ ወደቤታቸው የተመለሱ ናቸው።

https://p.dw.com/p/4ezUS
ፎቶ ከማኅደር፤ የወባ ትንኝ መከላከያ የመኝታ አጎበር
በምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ የወባ በሽታ መስፋፋቱና ከ200 በላይ ሰዎች በወባ መያዛቸው ተነግሯል። ፎቶ ከማኅደር፤ የወባ ትንኝ መከላከያ የመኝታ አጎበርምስል Jonathan Nackstrand/AFP

የወባ በሽታ ስርጭት በጊምቢ ወረዳ

በምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ የወባ በሽታ መስፋፋቱና ከ200 በላይ ሰዎች በወባ መታመማቸውን ነዋሪዎች ተናገሩ። በዚህ ቶሌ በተባለው አካባቢ የሚገኙ ዜጎች የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ ተፈናቅለው ወሎ እና ደብረብርሃን ቆይቶ በየካቲት ወር 2016 መጀመሪያ ላይ ወደቤታቸው የተመለሱ ናቸው። በቦታው መድኃኒት ካለመኖሩ ጋር ተዳምሮ ብዙ ሰዎች በወባ በሽታ እየተጎዱ እንደሚገኙ ያነጋገርናቸው  ነዋሪዎች አብራርተዋል። የዞኑ ጤና መምሪያ በበኩሉ በአካባቢው የወባ ስርጭት መኖሩን ገልጾ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቤታቸው ከተመለሱ ጊዜ አንስቶ ህኪምና በነጻ እየተሰጠ ይገኛል ብሏል።  ባለሙያዎች በቦታው በጊዜያዊነት ተመድበውም እየተሠራ እንደሆነም አመልክቷል። 

በመድኃኒት እጥረት ምክንያት ወባ ጉዳት እያደረሰ ነው

በወሎ ጃራ መጠለያ ለሁለት ዓመት ያህል ቆይተው በየካቲት ወር መጀመሪያ 2016 ዓ.ም ወደ ጊምቢ ወረዳ ቶሎ ቀበሌ መመለሳቸውን የነገሩን ነዋሪ በአካባቢው መደበኛ የህክምና ተቋም ባለመኖሩና በመድኃኒት እጥረት የወባ በሽታ ጉዳት እያደረሰ እንደሆነ ይገልጻሉ። ዘጠኝ ከሚደርሱ የቤተሰባቸው አባላት መካከል አራት ሰዎች በወባ በሽታ ተይዘው በመድኃኒት እጦት ለከፍ ችግር መጋለጣቸውንም ጠቁመዋል። ለተሻለ ህክምና ራቅ ወዳሉ የህክም ተቋማት ለመሄድም የህክምና ወጪው ከፍተኛ መሆኑን በመግለጽ የወባ ስርጭት እያስከለ ያለውን ጉዳት  አስረድተዋል።

ወደ ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ከተመለሱ ሁለት ወራት እንዳስቆጠሩ የነገሩን ሌላው ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ነዋሪም በወባ በሽታ ከ200 በመቶ በላይ ሰዎች መታመማቸውን አመልክተዋል። በቦታው የህክምና ባለሙያዎች ተመድበው እርዳታ ሲያደርጉ መቆየታቸውን የተናገሩት ነዋሪው መድኃኒት በመጥፋቱ በአሁኑ ወቅት አብዛኛው ሰው በወባ በሽታ መታመሙን ገልጸዋል። በቶሌ የወባ በሽታ ስርጭት በዚህ መልኩ ጨምሮ እንደማያወቅ የነገሩን ሌላው ነዋሪም በቂ የመድኃኒት አቅርቦት እንደሚስፈልጋቸው ተናግረዋል።

የወባ ትንኝ
የወባ ትንኝምስል picture-alliance/dpa

በቶሌ ቀበሌ 247 ሰዎች በወባ ታመዋል

የምዕራብ ወለጋ ዞን የጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ጫላ በዚሁ ጉዳይ ላይ በሰጡን ማብራሪያ በቶሌ ቀበሌ የወባ ስርጭት መጨመሩን እና በ247 ሰዎች ላይ ወባ መገኘቱን ተናግረዋል። ለተፈናቀሉ ዜጎች ከተመለሱ ጊዜ አንስቶ የህክምና ባለሙያ በመመደብ የህክምና ዕርዳታ ወባን ጨምሮ  በነጻ እየተሰጣቸው እንደሚገኝ የተናገሩት ኃላፊው አልፎ አልፎ የመድኃኒት እጥረት ሊያግጥም ይችላል ብለዋል።

«አካባቢው ሞቃታማና ለወባ ተጋላጭ ነው። ወባን በተመለከተ አቅርቦትና ባለሙያዎችን እዛው መድበን እያሠራን ነው። በቦታው የሚሰጠው የህክምና አገልግሎት እንደ መደበኛ ሆስፒታልና ጤና ጣቢያ ላይሆን ይችላል ነገር ግን ዛሬም ባለሙያዎች እዛው ሆነው አገልግሎት እየሰጡ ነው።»

በምዕራብ ወለጋ ዞን ከዚህ በፊትም የወባ በሽታ ስርጭት በወረርሽኝ መልክ መከሰቱን ተዘግቧል። በተለይም በሐምሌ እና ነሐሴ ወራት በሳምንት በዞን ደረጃ ወደ ሆስፒታል ከሚመጡት ሰዎች መካከል ከ500 በላይ ሰዎች ላይ ወባ በሽታ ይገኝ እንደነበር የዞኑ ጤና መመሪያ አመልክቷል።

ነጋሳ ደሳለኝ

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ