1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ሠራተኞች ለተፈናቃዮች ያሰባሰቡት ርዳታ

ማክሰኞ፣ ጥር 3 2014

የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ሠራተኞች በማህበራዊ መገናኛ ዘዴ ባደረጉት  የገንዘብ ማሰባሰብ ዘመቻ ከ2 ሚሊዩን ብር በላይ ገንዘብ በምስራቅ ወለጋ ዞን ኪራሙና ጊዳ አያና ወረዳ ለሚገኙ ተፈናቃዩች ማሰባሰባቸውን ገለጹ፡፡ ዩኒቨርሲቲውም ተጨማሪ የአንድ ሚሊዩን ብር ድጋፍ ማድረጉን አስታውቋል፡፡

https://p.dw.com/p/45Njd
Äthiopien Wollega Universität
ምስል Privat

ከ 2 ሚሊዩን ብር በላይ ተሰባስቦአል፤ዩንቨርስቲዉም ገንዘብ ሰጥቶአል

የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ሠራተኞች በማህበራዊ መገናኛ ዘዴ ባደረጉት  የገንዘብ ማሰባሰብ ዘመቻ ከ2 ሚሊዩን ብር በላይ ገንዘብ በምስራቅ ወለጋ ዞን ኪራሙና ጊዳ አያና ወረዳ ለሚገኙ ተፈናቃዩች ማሰባሰባቸውን ገለጹ፡፡ ዩኒቨርሲቲውም ተጨማሪ የአንድ ሚሊዩን ብር ድጋፍ ማድረጉን አስታውቋል፡፡ በአጠቃላይ ከ3 ሚሊዩን በላይ በሚገመት ገንዘብ የተለያዩ የእህልና ቁሳቁሶችን በመግዛት  ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ ማድረሳቸውን የወለጋ ዩኒቨርሲቲና የድጋፍ አሰባሳቢዎቹ ለዲዳቢሊው ተናግረዋል፡፡

በምስራቅ ወለጋ ነቀምቴ ከተማ ውስጥ የሚገኘው የወለጋ ዩኒቨርሲቲ ሰራተኞች ከወራት በፊት በማህበራዊ ሚዲያ ተፈናቃዩች ለማገዝ የገንዘብ ማሰባሰብ ዘመቻ መጀመራቸውን ይናራሉ፡፡ በወለጋ ዩኒቨርሲቲ የሴቶች፣ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ኃላፊ ዶ/ር አሊማ ጂብሪል ከድጋፍ አሰባሳቢዎቹ መካከል አንዱ ሲሆኑ በማህበራዊ ሚዲያ በመታገዝ ባደረጉት ገንዘብ የማሰባሰብ ዘመቻ ከ2 ሚሊዩን ብር በላይ መሰብሰባቸውን ገልጸዋል፡፡ ከአካባቢው ማህበረሰብ እና በውጭ ሀገር የሚኖሩ ዜጎችም ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚውል የተለያዩ ድጋፎችን በየወረዳ  ማድረሳቸውን እንደዚሁ ጠቁመዋል፡፡

Äthiopien Wollega Universität
ምስል Privat

የወለጋ ዩኒቨርሰቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሐሰን ዩሱፍ በበኩላቸው  የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አገልግሎት ስራውን በማጎልበት  ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይም በምስራቅ ወለጋ ዞን ወረዳዎች እና የተወሰኑ የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ወረዳዎች የሚገኙ የተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ ለማድረስ ዩኒቨርሲቲው ድጋፍ እየሰባሰበ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ በጊዳ አያና ወረዳና ኪራሙ የተባሉ ወረዳዎች ውስጥ ለሚገኙ ተፈናቃዎች የሚውል  የአንድ ሚሊዩን ብር ድጋፍ ዩኒቨርሲቲው ማድረጉን አመልክቷል፡፡ ከዚህ ቀደም በመንገድ መዘጋት ምክንያት ለረዥም ጊዜያት ድጋፍ ለማድረስ ተቸግረው እንደነበረም አክለዋል፡፡

በምስራቅ ወለጋ ዞን አራት በሚደርሱት ወረዳዎች በነበሩት አለመረጋጋቶች በርካታ ሰዎች ተፈናቅለው በየወረዳ ከተማ ተጠልሎ እንደሚገኙ የአካባቢው ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ በጊዳና አያና እና ኪራሙ በመጀመሪያ ዙር ድጋፍ እንደረሳቸው ነዋሪዎች የገለጹ ሲሆን ነገር ግን የሚቀርቡ ድጋፎች በቂ አለመሆናቸውንም አክለዋል፡፡

በምስራቅ ወለጋ የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ ተፈናቅሎ በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ ለሚገኙ ዜጎች እርዳታ ለማዳረስ እየሰሩ እንሚገኙም የዞኑ ዋና አስተዳዳር አቶ አለማየሁ ተስፋ ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ በሰጡን ማብራሪያ ጠቁመዋል፡፡ በዞኑ ጉቴ ግዳ በሚባል ወረዳ ከ30ሺ በላይ የሚደርሱ ተፈናቃዩች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡

ነጋሳ ደሳለኝ

አዜብ ታደሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ