የኦሮሚያ ግጭት፡ የሰላማዊ ሰዎች ግድያ እና የሰላም ጥሪ
ሰኞ፣ መጋቢት 30 2016ለመዲናዋ አዲስ አበባ እጅግ ቅርብ ርቀት ላይ የምገኘው የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በኦሮሚያ ክልል የሰላምና ፀጥታ ይዞታው እጅጉን ፈታኝ ከሆኑባቸው አከባቢዎች በቀዳሚነት የሚጠቀስ ሆኗል፡፡ በዚህ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች የታጣቂዎች እንቅስቃሴ እንደሚዘወተር የሚገልጹት የአከባቢው ነዋሪዎች ተደጋጋሚ ያሉት ግድያ በሰላማዊ ዜጎች ጭምር ላይ እንደሚፈጸም ጥቆማቸውንም ይሰጣሉ፡፡
በዞኑ ከቶሌ ወረዳ አስተያየታቸውን የሰጡን አንድ ለደህንነታቸው ስባል ስማቸውን እንዳንጠቅስ የጠየቁ ነዋሪ በቅርቡ በተለይም ከ10 ቀናት ወዲህ በዚህ ወረዳ ተባብሷል ባሉት የአማጺ ታጣቂዎች እና የመንግስት ሰራዊት እንቅስቃሴ ሰላማዊ ዜጎችም ጭምር መገደላቸውን ጠቁመዋል፡፡
ነዋሪው በአስተያየታቸው ሁለቱም የታጠቁ አካላት አንዱ ሌላውን የታጠቀ አካል ትደግፋለህ በሚል በገቢያ እና በቤታቸው ጭምር እንደምገደሉ አንስተዋል፡፡ በተመሳሳይ ዞን ውስጥ በምገኘው አመያ በተባለ ወረዳም የነዋሪዎች መኖሪያ መንደር ጭምር የወደሙበት ውጊያ እና ጥቃት መፈጸሙ ተመልክቷል፡፡ ይህ ደግሞ በአከባቢው ነዋሪዎች ላይ ከሚያደርሱ የህይወት ጥፋት እና ኢኮኖሚያዊ መስተጓጉል በላቀ ከፍተኛ ስጋትን ያጫረ ማህበራዊ ቀውስ ስለማስከተሉም አስተያየት ሰጪው አስረድተዋል፡፡
ስለ ጥቃቱ የኦነግ መግለጫ
ከዚህ ባሻገር ተቃዋሚው የኦሮሞ ነጻነት ግንባ (ኦነግ) በሳምንቱ የመጨረሻ ቀናት ባወጣው መግለጫ በዚሁ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ቶሌ ወረዳ 20 ያህል ሰላማዊ ሰዎች በመንግስት ሰራዊት ተገድለዋል ሲል ከሷል፡፡ ኦነግ የ20 ሰዎች ስም ዝርዝር ባካተተበት በዚህ መግለጫው በሰላማዊ ዜጎች ላይ ይፈጸማል ያለው ወታደራዊ እርምጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ መክፋቱን አስረድቷል፡፡ ኦነግ በቶሌ ተወስዷል ያለው “የጅምላ ግድያ” አስከፊ ነው በማለት ግድያውንም ኮንኗል፡፡
የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ለሚ ገመቹ በዚህ ላይ ለዶቼ ቬለ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ፡ “በሰላማዊ ዜጎች ላይ ያነጣጠረው ጥቃት በጦር ወንጀልም ሊያስጤቅ የሚችል” ሲሉ ተችተዋል፡፡ አቶ ለሚ ከጊዜ ወደ ጊዜ ተባብሷል ባሉት በመሰል የሰላማዊ ሰዎች ጥቃት በርካቶች ህይወታቸውን እንደሚያጡም በመግለጽ የነዋሪዎች ሃብት ንብረትም እንደሚወድም ከማህበረሰብ እና “አደረጃጀታችን” ካሉት አካላት የሚደረሷቸው መረጃዎች እንደሚያሳዩም ገልጸዋል፡፡
ኦነግ መግለጫ ካወጣበት የቶሌ ጥቃት በተጨማሪ በአመያ ወረዳም በክልሉ ታጥቀው በምንቀሳቀሱ አማጺያን ጭምር በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች መኖራቸውን ነዋሪዎች ብገልጹም ኦነግ ስለዚህ ያለው ነገር የለም፡፡ አቶ ለሚን በክልሉ ለሚፈጸሙ ግድያዎች ከመንግስት ሰራዊት በተጨማሪ ስለሌሎች የታጠቁ አካላት ጥቃት የፓርቲው አቋም ምን ይሆን የሚል ጥያቄ አቅርበንላቸው፤ “በስልጣን ላይ ከለው መንግስት በተሻለ የዜጎችን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት ያለበት አካል ባለመኖሩ በተጠያቂነት የምንጠቅሰው መንግስት ነው” ሲሉ መልሰዋል፡፡
የመንግስት የሰላም ጥሪ
ዶይቼ ቬለ በዞኑ ተፈጸመ ስለተባለው ጥቃት እና አሁናዊ ይዞታውን በማስመልከት ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ለዞኑ ኮሚዩኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኃይሉ ጀልዴ ስደውል፤ ኃላፊው በያከባቢው የሰላማዊ ዜጎች ጥቃቱ መኖሩን አረጋግጠው አሁን ላይ ለስራ ሌላ ቦታ በመሆናቸው ተጨማሪ ማብራሪያ መስጠት እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ለምስተዋለው አለመረጋጋት ከዚህ ቀደም መንግስት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት ማድረጉን አስታውቆ ሂደቱ ግን በተደጋጋሚ መክሸፉ መገለጹ ይታወሳል፡፡
ይህንኑን መነሻ በማድረግ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ከሰሞኑ በይፋዊ ማህበራዊ ገጻቸው ላይ ሰላም! ሰላም! ሰላም! ብለው ባሰራጩት ዘለግ ያለ ጽሁፍ ላይ መንግስታቸው በክልላቸው ያለውን የጸጥታ ችግር በሰላማዊ አማራጭ ለመፍታት ጥረት መደረጉን አስታውሰው፤ “በአገር ውስጥ እና ከአገር ውጪ ስተበተቡ ነበሩ” ባሏቸው “ሸፍጥ” መደናቀፉን ጠቁመዋል፡፡
ቄሌም ወለጋ በፀጥታ ችግር የሰዎች ሕይወት እየጠፋ ነው
አቶ ሽመልስ በይፋዊ ማህበራዊ ገጻቸው በጻፉት በዚሁ ጽሁፍ “በራችን ለሰላም ክፍት ነው” ብለው አሁንም መንግስታቸው ከህዝብ እና ባለድርሻ አካላት ጋር ተማክሮ
የሰላም ጥሪን በማሳለፍ ሰፊ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ በዚህም በቀረበው ጥሪ መሰረት በሺዎች የሚቆጠሩ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን አውርደው እየተመለሱ ነው ያሉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር፤ “የኦሮሞ ህዝብ ከጦርነት እንደማያተፍ” ገልጸው፤ ልዩነቶች በውይይት እንዲቋጩ በማለት ጥሪ አሰምተዋል፡፡
ሥዩም ጌቱ
እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሠ