1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኢትዮጵያና ሶማሌላንድ ዉል ከቪየናዉ ስምምነት አኳያ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 23 2016

ለዴቼ ቬለ ያጋሩ አንድ የአለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ተንታኝ ባለው አለም አቀፍ የዲፕሎማሲ አሰላለፍ ሶማሌላንድ እንደ ሀገር የምትታወቅ አለመሆኑን እና ኢትዮጵያ የፈረመችው የቪየና ኮንቬንሽን ሀገራት መሰል ስምምነቶችን የሚፈራረሙት ከአቻ አካላት ጋር እንዲሆን ሕግ የሚያስገድድ መሆኑን ለተነሳው የሕግ ጥያቄ አብራርተዋል።

https://p.dw.com/p/4anuo
ሁለቱ መሪዎች በተፈራረሙት የመግባቢያ ሰነድ መሰረት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ወደብ ታገኛለች
ከግራ ወደቀኝ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስር አብይ አሕመድና የሶማሊላንዱ መሪ ሙሴ ቢሂ አብዲ የመግባቢያ ስምምነቱን ከፈረሙ በኋላምስል TIKSA NEGERI/REUTERS

የኢትዮጵያና የሶማሊላንድ ዉል ከቪየና ስምምነት አኳያ

   ኢትዮጵያ እንደ ሉዓላዊ ሐገር ዓለም አቀፍ እዉቅና ከሌላት ነገር ግን ራስዋን የሶማሊላንድ ሪፐብሊክ ብላ ከምትጠራዉ ጋር ትናንት የተፈራረመችዉ የመግባቢያ ሰነድ ከተለያዩ ወገኖች ድጋፍ፣ ካንዳዶች ተቃዉሞ፣ ከሌሎች ደግሞ ጥርጣሬና ሥጋት ገጥሞታል።የኢትዮጵያና የሶማሊ ላንድ መሪዎች ትናንት በተፈራረሙት የመግባቢያ ዉል መሠረት ኢትዮጵያ ለጦር ሠፈርና ለንግድ አገልግሎት የምታዉለዉ፣ ለ50 ዓመታት በሊዝ የምትይዘዉ የባሕር በር ታገኛለች ተብሏል።ሶማሊላንድ በአንፃሩ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ወይም ከቴሌኮሙኒኬሽ ድርሻ ይኖራታል።ሶማሊላንድ የግማደ ግዛትዋ አካል አድርጋ የምትቆጥራት የሶማሊያ ፈደራል ሪፐብሊክ መንግስት ስምምነቱን ተቃዉሞታል።

የስምምነቱ ዐበይት ጭብጦች 

ኢትዮጵያ የባሕር በር ልታገኝ የምትችልበትን የመግባቢያ ስምምነት በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድእና ምንም እንኳን ራሷን ከ1991 ጀምሮ እንደ ሀገር ብትቆጥርም በተናጠል በሀገራትም ይሁን በዓለም አቀፍ ተቋማት ዘንድ እውቅና በተነፈገችው በሶማሌላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሂ አብዱ ትናንት አዲስ አበባ ላይ ተፈርሟል። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ስምምነቱ ለኢትዮጵያ የሚያስገኘውን ጉልህ ጥቅም ዘርዝረዋል። 
"በሶማሌላንድ ውስጥ ኢትዮጵያ የሚሊቴሪ ቤዝ - ወታደራዊ ሠፈር እና ኮሜርሻል ማሪታይም- የባሕር መርከብ ሠፈር እንዲኖራት ይፈቅዳል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በይዘቱ በሊዝ የሚታሰብ ይሆናል፣ ለ ሃምሳ አመት እና ከዚያ በላይ ደግሞ በማስፋፊያ የሚካሄድ እንዲሆን ያደርጋል" 
 

የኢትዮጵያና የሶማሊላንድ መሪዎች በተፈራረሙት የመግባቢያ ስምምነት መሰረት ኢትዮጵያ የሐርጌሳ ወደብንም ትጠቀማለች
የሐገረ መንግስት እዉቅና የሌላት ሶማሊላንድ ካሏት ወደቦች አንዱና ታዋቂዉ የሐርጌሳ ወደብ ነዉ። ምስል Yannick Tylle/picture alliance

በስምምነቱ ሶማሌላንድ ከኢትዮጵያ ልታገኝ የምትችለው ጥቅምም በግልጽ ተመላክቷል። 

"በቴሌኮም ይሁን ፣ በአየር መንገድ ይሁን ጥቅም በሚያስገኙ መሠረተ ልማቶች ዙሪያ ድርሻ ለመስጠት የሚያስችል እድል ስለነበረው ይሄን ድርሻ የመግባቢያ ስምምነቱ ያመላክታል" 


የአለምአቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ተንታኝ አስተያየት 

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልወደዱ አስተያየታቸውን ለዴቼ ቬለ ያጋሩ አንድ የአለም አቀፍ ሕግ እና የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ተንታኝ ባለው አለም አቀፍ የዲፕሎማሲ አሰላለፍ ሶማሌላንድ እንደ ሀገር የምትታወቅ አለመሆኑን እና ኢትዮጵያ የፈረመችው የቪየና ኮንቬንሽን ሀገራት መሰል ስምምነቶችን የሚፈራረሙት ከአቻ አካላት ጋር እንዲሆን ሕግ የሚያስገድድ መሆኑን ለተነሳው የሕግ ጥያቄ አብራርተዋል። 


[ የቪየና ኮንቬንሽን "ስምምነት አቻ በሆኑ አካላት መካከል ሊፈፀም ይገባል ይላል። ስለዚህ ኢትዮጵያ ሀገር ሆና እንደ ሀገር ከሌላ አንድ ሀገር ጋር የምታደርገውን ውል ነው ውለታ ነው ብሎ የሚወስደው። ትልቁ ጥያቄ የሚሆነው ሶማሌላንድ ሀገር ነች ወይ ? ባለው የአለም አቀፍ ግንኙነት አሰላለፍ ውስጥ ሶማሌላንድ እንዴት ነው የምትታየው ? ከተባለ ሶማሌላንድ ሀገር አይደለችም" ብለዋል።

ሶማሊያ፣ ሶማሌላንድን እንደግዛቷ ስለምታይ፣ አፍሪካ ሕብረት ደግሞ ለሶማሌላንድ እውቅና ከመንፈጉ ባሻገር የራሳቸውን አገረ - መንግስት ለመመስረት በተንጠልጠል ላይ የሚገኙት የናይጀሪያ ቢያፍራ እና የሞሮኮ ሳሃራዊ ሪፐብሊክ ግዛቶች ግፊታቸውን ቀጥለው እንዳይገነጠሉ የሚያደርገውን ጥረት ለመጠበቅ ስለሚፈልግ በዚህ ስምምነቱ ምክንያት ኢትዮጵያ ከጎረቤት ሀገር ሶማሊያም ይሁን ከአፍሪካ ሕብረት ጋር ያላት ግንኙነት እንዳይሻክር ባለሙያው ሥጋታቸውን ገልፀዋል። የአፍሪካ ሕብረት ለኤርትራም ይሁን ለደቡብ ሱዳን እውቅና የሰጠው ከተገነጠሉባቸው እናት ሀገራት ለመለየታቸው እውቅና አስቀድሞ ስላገኙ መሆኑን በመጥቀስ የሶማሊያ እና ሶማሌላንድ ሁኔታ ግን የተለየ መሆኑን ጭምር ተንትነዋል።

እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ከ1991 ጀምሮ ከሞቃዲሾ አስተዳደር የተገነጠለችዉ የሶማሊላንድ ርዕሰ ከተማ ሐርጌሳ  በከፊል
እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ከ1991 ጀምሮ ከሞቃዲሾ አስተዳደር የተገነጠለችዉ የሶማሊላንድ ርዕሰ ከተማ ሐርጌሳ በከፊልምስል DW/Richard Lough

 

"ከሚነጠሏት ሀገር [ ኤርትራ እና ደብብ ሱዳን] መጀመርያ እውቅናው ስለመጣ ነው። አሁን ባለው በሶማሌላንድ ጉዳይ ላይ ግን እናት ሀገር ከምትባለው ሶማሊያ እውቅና የለውም" 

ከሶማሊያ እየተሰጡ ያሉ አስተያየቶች 

ኢትዮጵያ በግልጽ ባይሆንም ለሶማሌላንድ የሀገርነት እውቅና ሰጥታ መቆየቷን ማሳያ በመጥቀስ ጭምር ያብራሩት ባለሙያው ኢትዮጵያ የባሕር በር የምታገኝበት እድል መመቻቸቱ ግን አስደሳች ዜና መሆኑን ጠቅሰዋል። 

ይህንን ስምምነት ተከትሎ የሶማሊያ መንግሥት ዛሬ አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ይገኛል። ሶማሊያዊያን በየማህበራዊ መገናኛ ዐውታሮች ስምምነቱን በመቃወም ድምፅ እያሰሙ ሲሆን ሶማሊያን ከ 2017 - 2022 በፕሬዝዳንትነት ያገለገሉት ሞሐመድ አብዱላሂ ፎርማጆ "ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር ዛሬ የተፈራረመችው ስምምነት ለሶማሊያ እና ለመላው አፍሪካ አሳሳቢ ጉዳይ ነው። ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ማክበር ለቀጣናዊ መረጋጋት እና የሁለትዮሽ ትብብር መልሕቅ ነው" በማለት የሶማሊያ መንግሥት ተገቢውን ምላሽ መስጠት አለበት ሲሉ በ ኤክስ ትናንት ምሽት ጽፈዋል።

ሰለሞን ሙጬ

ነጋሽ መሐመድ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር