1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአውሮጳ ኅብረት እና የፈረንሳይ መሪዎች የቻይና ጉብኝት

ዓርብ፣ መጋቢት 29 2015

የሩሲያ ዩክሬንን ጦርነት ለማስቆም ቻይና ከፍተኛ ሚና እንድትጫወት እየተጠየቀ ነው። በጦርነቱ ከዩክሬን ጎን የተሰለፉት ምዕራባውያን ሃገራት ቀውሱን በማስቆሙ በኩል ከሰሞኑ ትኩረታቸውን ቻይና ላይ አድርገዋል። ለዚህም የፈረንሳይ ፕሬዝደንት ኢማኑዌል ማክሮ እና የአውሮጳ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝደንት ዑርዙላ ፎንደር ላይን ቻይናን ጎብኝተዋል።

https://p.dw.com/p/4Pp7F
Frankreichs Präsident Macron besucht China - von der Leyen
ምስል Ludovic Marin/Pool AFP/AP/dpa/picture alliance

የቻይና ሚና ለሰላም

በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ምክኒያት በዓለማችን በተለይም በአውሮጳ የተከሰተው ሰባዊ ቀውስ፣ የኢኮኖሚ ችግርና የደህንነት ስጋት የአውሮጳ መሪዎችን ወደ ቻይና መለስ ቀለስ እንዲሉ አድርጓቸዋል እየተባለ ነው። በቅርቡ የስፔኑ ጠቅላይ ሚኒስተር ከዚያም በፊትና ቀደም ብሎም የጀርመን ቻንስለርና የካውንስሉ ፕሬዝዳንት ቻርለስ ሚሸል በተናጠል በቤጂንግ ተገንተው የነበረ ሲሆን፤  ባለፉት ሦስት ቀናት ደግሞ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ሚስተር ማክሮ ከኮሚሽኑ ፕሬዝዳንት ወይዘሮ ዑርዙላ ፎን ዴርሌየን ጋር በመሆን ቻይናን ጎብኝተዋል። የአሁኑ የማክሮ ጉብኝት ልዩ የሆነው ከኮሚሽኑ ፕሬዝዳንት ጋር በአንድነት መደረጉ  ባቻ ሳይሆን፣ በቅርቡ ቻይና ከሩሲያ ጋር ያላትን ግንኙነት በመሪዋ ሚስተር ሺ ጂፒንግ የሩሲያ ጉብኘት ለዓለም ይፋ ካደረገች በኋላ በመሆኑ ነው። ወይዘሮ ፎንዴርሌየን እንደሚሉት ግን ጉብኝቱ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው  ቻይና የዩክሬንን ጦርነት ለማስቆም ወሳኝ ሚና ልትጫወት ስለምትችል ነው።

በዩክሬን ጦርነት ጉዳይ ሁሉም የአውሮጳ እና የኔቶ አባል አገሮች ተመሳሳይ አቋም አላቸው ቢባልም፤ ቻይናን በሚመለከት ግን ሁሉም በአንድ መስመር ላይ የቆሙ ናቸው ማለት ግን አይቻልም።  ዋናዋ የኔቶ አባልና የጸረ ሩሲያው ትግል ፊት መሪ አሜሪክ ከቻይና ጋር የራሷም ቅራኔና ፉክክር ሳላላት ጭምር፤ ቻያናን ከሩሲያ ጎን ሙሉ በሙሉ እንደቆመች የምትገልጽ ሲሆን፤ ሌሎች በተለይም እንደ ፈረንሳይና ጀርመን የመሳሰሉት ግን በዚህ የአሜሪካ አቋም እንደማይይስማሙ ነው የሚታመነው። በፓሪስ  ግሎባል ፖሊሲ ኢንሲቲቱተ ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት  ሚስተር ጃክ ሮላንድም ፤ «ቻይናን በሚመለከት በአውሮጳና አሜሪካ መካከል ልዩነት መኖሩ ግልጽ ነው»  በማለት በአውሮጳውያኑ በኩል ምንም እንኳ የንግድ ፍሰቱ የተመጣጠነ  ያለመሆንና  ለነጻ ገበያና ኢንቨስትሜንት መሳለጥ የሚያግዙ መዳላደሎች ያለመኖር ችግር ቢኖርም፤ እንደ ፕሬዝዳንት ማክሮን ያሉ የኅብረቱ መሪዎች ግን  ቻይናን ተፎካክሪ ብቻ ሳትሆን አጋርም እንደሆነች እንደሚያምኑ ገልጸዋል።

China EU-Kommissionspräsidentin Ursula von der Leyen
የአውሮጳ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝደንት ዑርዙላ ፎንደርለንምስል Andy Wong/AP Photo/picture alliance

በዩክሬን ጦርነት ላይ ቻይና ቀደም ሲል ያቀረበችውን የሰላም ሀሳብ ፕሬዝዳንት ማክሮ ከሌሎቹ የኅብረቱና የኔቶ አገሮች መሪዎች በተለየ ሁኔታ በአወንታ የሚያዩት መሆኑን ሲናገሩ የተሰሙ ሲሆን፤ ከፕሬዝዳንት ሺ ጂፒንግ ጋር በነበራቸው ውይይትም፤ እሳቸው ሩሲያን ወደ ውይይት ጤረጴዛ እንድትመጣ እንደሚያደርጉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የቻይናው መሪ በበኩላቸው፤ «የዩክሬንን ቀውስ በሚመለክት፤ ቻይና ችግሩ በውይይትና በንግግር እንዲፈታ ነው የምትፈልገው» በማለት ሌሎችም ቀውሱን ከማባባስና ግጭቱን ከማስፋት እንዲቆጠቡ መልክት አስተላለፈዋል።

ፎንዴርሌየን በተጨማሪም ቻይና ከሁሉም በላይ የጦር መሳሪያ ለሩሲያ እንዳታቀብል አደራ ብለዋል። «ቻይና ማንኛውንም አይነት የጦር መሳሪያ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ለሩሲያ እንደማትሰጥ ተስፋ እናደርጋለን» በማለት የጦር መሳሪያን ለወራሪ ኃይል ማቀበል ከኅብረቱ ጋር ያለውን ግንኙነት እንደሚጎዳ ግልጽ አድርገዋል።

Frankreichs Präsident Macron besucht China - von der Leyen
የፈረንሳይ ፕሬዝደንት እና የአውሮጳ ኅብረት መሪዎች የቻይና ጉብኝትምስል Ludovic Marin/Pool Photo via AP/picture alliance

 ዛሬ የተጠናቀቀውና ከአውሮፓ ጋር ያለውን የኢኮኖሚና ንግድ ግንኙነት ለማስቀጠልና ከሁሉም በላይ ግን በዩክሬኑ ጦርነት ቻይናን የመፍትሄው አካል እንድትሆን ለማግባብት ታስቦ የተደረገው የማክሮንና የፎንዴርሌየን የቻይና ጉብኝት፤ ሙሉ በሙሉ የተሳካ ነበር ባይባልም ምንም ውጤት አላስገኘም ግን አይባልም። ፕረዝዳንት ማክሮ በጉዟቸው በርካታ የቢዝነስና ኩባንያ ሀላዎችንም አስከትለው የነበር ሲሆን፤ በፈረንሳይና ቻይና መካከል አንዳንድ የኢኮኖሚና የንግድ ስምምነቶች እንደተፈራሙም ታውቁል። ከሁሉም በላይ ግን የፍራንስ 24ቱ ጋዜጠኛ ጃክ ፓሮክና ሌሎችም እንደሚሉት ጉብኝቱ ሁለቱም መሪዎች፤ ቻይና ከሩሲያ ጋር ያላትን ወዳጅነት በመጠቀም የዩክሬኑ ጦርነት እንዲቆምና ሰላም እንዲሰፍን የበኩሏን እንድታደርግ ጥሪ የቀረበበት ሆኖ ታይቷል።

ገበያው ንጉሤ 

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት ስለሺ