1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአሜሪካ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ዘገባ፤ የኢትዮጵያ ምላሽና የህወሃት ከሽብረተኛነት መሰረዝ

ዓርብ፣ መጋቢት 15 2015

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚው በየዕለቱ ሃሳቡን የሚሰነዝርበት አዳዲስ ጉዳይ መከሰቱ ቀጥሏል።

https://p.dw.com/p/4P9X1
Äthiopien USA Demeke Hasen Antony Blinken
ምስል Ethiopian Foreign Ministry

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚው በየዕለቱ ሃሳቡን የሚሰነዝርበት አዳዲስ ጉዳይ መከሰቱ ቀጥሏል። በዚህ ሳምንትም እንዲሁ በርካታ ርዕሰ ጉዳዮች መነጋገሪያ ቢሆኑም ዋሽንግተን እና አዲስ አበባን ውዝግብ ውስጥ የከተተው ዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በቅርቡ ፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪቃ ላይ በመንግሥት እና በህወሃት መካከል በተደረገው ሰላም ስምምነት የተቋጨው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ወቅት «ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተፈጽሟል» ሲል ያወጣው ዘገባ የበርካቶች መነጋገሪያ ሆኖ ቀጥሏል። አስተያየቶቹንም ተገቢ ነው በማለት የደገፉ፤ የተቃወሙ እና የለም አጀንዳው ሌላ ነው የሚል ጥርጣሬ ያላቸው ብሎ በሦስት ከፍሎ ማየት ይቻላል።

በተለይ አዲስ አበባን ለቀናት ጎብኝተው የተመለሱት የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአንቶኒ ብሊንከን መሥሪያ ቤታቸው «ሕግና ተጨባጭ እውነትን በጥንቃቄ» ከመረመረ በኋላ ወሰንኩ ባሉት ዘገባ በጦርነቱ የተሳተፉ ተፋላሚ ኃይላት በሙሉ የጦር ወንጀል ፈፅመዋል የሚል መግለጫ ነው የሰጡት። ድርጊቱን የፈጸሙትም በሕግ እንዲጠየቁ አሜሪካን አሳስባለች። የኢትዮጵያ መንግሥትም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል በሰጠው ምላሽ ዘገባውን ወገንተኛ እና ከፋፋይ ሲል ውድቅ አድርጓል። ይኽን በተመለከተ በፌስቡክ አስተያየታቸውን ካካፈሉት አንዱ አላያ አሊ ፤ «ኢትዮጵያ ትቀበላለች እንቢ ያለው መንግሥት ነው» ሲሉ፤ ረዲ ያብሥራ የተባሉት ሌላው የፌስቡክ ተጠቃሚል እንዲሁ፤ «የትኛዋ ኢትዮጵያ ናት የማትቀበለው... የብልፅግና ምላስ ላይ ያለችው ወይስ .... በየቀኑ .. ዜጎቿ .... በብሔር በሃይማኖት በርሀብ በመፈናቀል .... እንደ ቅጠል የሚረግፉባት ኢትዮጵያ ናት.... ለዩልን?» ብለዋል። ሸዊት ገብረእግዚአብሔርም እንዲሁ፤ «እና ማን እንዲቀበልላት ትፈልጋለች?» በማለት ከጠየቁ በኋላ « ለተፈፀመው ግፍ ጊዜው ይርዘም ይጠር ማንም ከተጠያቂነት አያመልጥም ይህ የሚይቀር ነገር ነው» ብለዋል።

Äthiopien | PK US Außenminister in Addis Abeba
የአሜሪካን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከንምስል Tiksa Negeri/AP Photo/picture alliance

ደሳለኝ ተገኔ፤ «በዚች አገር ያልተፈፅም ነገር አለ እንዴ?» ብለው ሲጠይቁ፤ ሙሴ ሎሚ በበኩላቸው፤ «በአሜሪካ  መንግሥት ይፋ የተደረገው ረፖርት ከተደረገው ድርጊት እጅጉን ያነሰ ነው! ከዛ በላይ ነው!!!» ነው የሚሉት።

ግፉ በዛ በለው የተባሉ የፌስ ቡክ ተጠቃሚም፤ «ማንም በሰላማዊ ሰው ላይ ወንጀል የፈጸመ መጠየቅ አለበት።» ባይ ናቸው። አባይ አየነው ደግሞ፤ «እውነት ነዉ ምንም ዓይነት ውጤት በሌለዉ ግጭት ንጹሐን ሊነገር የማይችል ግፍ ደርሶባቸዋል። ከኢትዮጵያ መንግሥት ጀምሮ በእውነት የተመሰረተ ማጣራት ይደረግ።» ይላሉ። ጌታቸው ማሞም፤ «እውነቱ ይውጣ » ነው የሚሉት። ተፈሪ ፋንታሁንም እንዲሁ፤ «ተጠያቂነት መኖር አለበት!» ይላሉ።

ነጋሽ ኤን ኤች በበኩላቸው፤ «በ 21 ክፍለ ዘመን ቁልጭ ብሎ የተፈፀመ ግፍ ነው።  ማንንም ማታለል ወይ መዋሸት አይቻልም። የህዝብ ችግር አንዲያበቃ ከተፈለገ በፍጥነት ውሳኔ መሰጠት አለበት እንጅ ግፉ እማ ማንም ተራሰውም አውቆት ያደረ ነዉ።» ባይ ናቸው። ጥላሁን ጌታቸው ጌታቸው ደግሞ፤ «እኛ የኢትዮጵያ ጦርነት አንፈልግም። ምዕራባዊያን እባካችሁ ከጫቃችን ላይ ውረዱ። ጠብ አትጫሩብን ። አንፈልጋችሁም። የጎን ውጋት አትሁኑብን።» ይላሉ። ጌቱ አለማየሁ ጭራሽ ዘገባው አልተዋጠላቸውም እናም፤ «ቅዠት የተሞላ ሪፖርት ነው የቀረበው ተፈፃሚ አይሆንም» ብለዋል። ዘገባውን በጥርጣሬ ከተመለከቱት አንዱ፤ የፌስቡክ ተጠቃሚው ጆም ጆ ጀምስ በእንግሊዝኛ የሰጡት አስተያየት እንዲህ ያላል፤ «ስለ ሰብአዊ መብቶች አይደለም። ስለመቆጣጠር ነው። እኛ ኢትዮጵያውያን አንሸጥም። ምንም እንኳን ብንለያይም ሀገራችንን ለሽያጭ አናቀርብም፤ ቀይ መስመር ነው።» የፀዳው ፀጋዬም አካሄዱ የጣማቸው አይመስሉም፤ «ኧረ ወዴት ወዴት ?? አንደኛው አንደኛውን ከወንጀል ለማስመለጥ የተዘየደ ሴራ ፍፁም ተቀባይነት የለውም !!!!! ፍትህ ለተበደሉ!» በማለት በርካታ ጥያቄ እና ቃለ አጋኖ ምልክቶች ያሰፈሩበትን አስተያየት ነው ያጋሩት።

Ethiopia Ministry of Foreign affairs podium | Addis Abeba, Ethiopia
ምስል Solomon Muchie/DW

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጣውን መግለጫ ካልተቀበሉት መካከል፤ ታደሰ ኃይለማርያም በበኩላቸው፤ «የአሜሪካ መንግሥት ከዚያ ሁሉ አጣዳፊ ሩጫ በኋላ የጦርነቱን ጠማቂና ጠንሳሽ በመተዉ የሀጢያቱ ሁሉ ባለቤት በማድረግ መንግሥት ላይ መጫኑ አስገራሚም አስደማሚም ነው!» በማለት አስተያየታቸውን በፌስቡክ አጋርተዋል።

ሌላው የበርካቶች መነጋገሪያ የሆነው የህወሃትን ከአሸባሪ ቡድንነት መሰረዝ። ውሳኔው ረቡዕ መጋቢት 13 ቀን 2015 ዓ,ም ልዩ ጉባኤ ያካሄደው የኢትዮጵያ ፓርላማ በ61 ተቃውሞ፤ በአምስት ድምጸ ተአቅቦ እና በዕለቱ ለስብሰባ ከተኙት የምክር ቤቱ አባላት የአብላጫውን ድጋፍ አግኝቷል። እንድሽ እንደሻው የተባሉት የፌስ ቡክ ተጠቃሚ፤ «ውሳኔው የተወሰነው ከመሰብሰብባቸው በፊት ነው ።ለቆጠራ እና ለካሜራ ነው የገቡት» ባይ ናቸው። ተወልደ ተኩበት የተባሉት የፌስቡክ ተጠቃሚ፤ «የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ላሳለፈው የብልህ ውሳኔ እናመሰግናለን» ሲሉ ሀሰን ጀቢቾም እንዲሁ፤ «እኛ ጦርነት ሰልችቶናል ። ከጦርነቱ ያተረፍነው ውድቀት ብቻ ነው ። የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ለማሳለጥ ከሽብርተኝነት መሰረዝ ተገቢ ነው ። ለሌሎችም ይህ ዕድል መሰጠት አለበት ።» ብለዋል። ግራዝ ላዝ የሚል የፌስቡክ ስም ያላቸው ሌላው አስተያየት ሰጪም፤ «ሸኔ ተብሎ እንዲጠላ የተሞከረው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ኦነግ ያልተገባ ብያኔ ሊቀለበስ ይገባል::» ነው የሚሉት።

Emblem der Tigray People's Libration Font (TPLF)
የህወሃት አርማ

ወንድማገኝ አንጀሎ ደግሞ ጥያቄ ነው ያቀረቡት፤ «አሸባሪ ማለት ራሱ ግራ ገባኝ፤ ምን ማለት ነው? መልኩና ጸባዩ ይለዋወጣ? ኃጢያተኛ የነበረው ጻድቅ ሆኖ ተለውጦ ነው ወይ ጻድቅ የነበረው ኃጢያተኛ ተብሎ ነው?» ሀብቶም ብርሃኔም፤ «ሲፈረጅስ ድንገት አይደል?» ሲሉ ሽመልስ ሽፈራው ግን፤ «ምንም አይደንቀኝም ፖለቲካ ነው።» ነው ያሉት። ሃብታሙ ካሣም፤ «አንችው ታመጭው አንችው ታሮጭው» የሚለውን አባባል ነው ለአስተያየት የተጠቀሙት።

አብዱልባር ቡሽራ ውሳኔ ግራ ያጋባቸው ይመስላል፤ «ግራ የገባው መንግስት፤ ቆይ ግን ጥቅምት 24ትን ምን ብላችሁ ልታከብሩት ይሆን??!!»  በማለትም ይጠይቃሉ። ሰይድ ላቭ የተባሉት ሌላኛው የፌስቡክ ተጠቃሚም የእሳቸውን ጥያቄ ደግመውታል፤ «እረ በጣም ግራ የገባው መንግሥት ነው ትናንት ስትሉን የነበረውን እንኳን አታስታውሱም? የጥቅምት 24ቱን ምን ብላችሁ ነው የምታከብሩት? ነዉ ከዚህ በኋላ ማክበር ቀረ? እንደው ህዝብ እንኳን ይታዘበናል አትሉም?»

Äthiopien Parlament Addis Abeba
የኢትዮጵያ ፓርላማ አዲስ አበባ አራት ኪሎምስል Solomon Muche/DW

ያያሙሌ ሀገር ነኝ የሚል የፌስ ቤክ ስም ያላቸው አስተያየት ሰጪ ደግሞ፤ «የኔን ወንድም ጨምሮ ጥቅምት 24 ታርደው ቀሩ፤ የሥልጣን ሽሚያ መሆኑን ሳይገባቸው ፈጣሪ ይፍረደን።» ሲሉ፤ ገረመው ዋሴ መለስም፤ «ይኽ ምስኪን ወታደር ያሳዝናል።» ሲሉ አስተያየታቸውን በአጭሩ አጋርተዋል።

ዮሐንስ መኮንንም በትዊተር፤ «ህወሃት በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ለፈጸመው ክህደት ተጠያቂ ሳይሆን፤ እና የጦርነቱ ገፈት ቀማሽ ለሆኑት በትግራይ፣ ለአማራ እና አፋር ለሚገኙ ወገኖቻችን ፍትህ ሳይሰጥ ቡድኑን ከሽብርተኝነት እንዲሰረዝ መወሰኑ ታሪክ ይቅር የማይለው ፍረደ ገምድልነት ነው።» ሲሉ፤ መልካሙ በቀለ ደግሞ በፌስቡክ «በአስከፊው የእርስ በርስ ጦርነት የሞቱን ሁሉ ነፍስ ይማር» ብለዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ