1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የአሜሪካ ምርጫ ዉጤት በአዉሮጳ ላይ ያለዉ አንደምታ 

ማክሰኞ፣ ኅዳር 1 2013

ባለፉት አስር ዓመታት በአሜሪካ በተደረጉት ፕሬዚዳንታዊ ምርጫዎች እንደዘንድሮዉ የአዉሮጳዉያንን ቀልብ የሳበ አልነበረም። የጀርመንዋ መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ዩናይትድ ስቴትስ እና የአውሮጳ ሕብረት አካል የሆነችዉ ጀርመን በዘመናችን ያሉን ታላላቅ ተግዳሮቶችን ለመቋቋም በአንድነት መቆም ይኖርባቸዋል ብለዋል።

https://p.dw.com/p/3l6Eu
EU USA Joe Biden Martin Schultz
ምስል Virginia Mayo/AP Photo/picture alliance

የአዉሮጳ መንግሥታትና በርካታ ዜጎች በምርጫዉ ዉጤት ደስታቸዉን እየገለፁ ነዉ

ባለፉት አስር ዓመታት በአሜሪካ በተደረጉት ፕሬዚዳንታዊ ምርጫዎች እንደዘንድሮዉ የአዉሮጳዉያንን ቀልብ የሳበ አልነበረም። ባሳለፍነዉ ቅዳሜ ባ,ሜሪካ ምርጫ መሰረት ለአሸናፊነት የሚያበቃዉ 270 የተመራጭ  መራጮች ቁጥር ማለፉ እንደተሰማ ፤ ተመራጭ ምክትል ፕሬዚዳንት ወ/ሮ ካማላ ሃሪስ ወጥተዉ ጆ ባይደን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነዉ መመረጣቸዉን ሲያበስሩ ደስታ እፎይታዉ የሚሊዮኖች አሜሪካዉያን ብቻ ሳይሆን የብዙ አዉሮጳዉያን  መሪዎችና ጭምር ነበር። 

በያዝነዉ ሳምንት መጀመርያ የጀርመንዋ መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል 46ኛ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነዉ ለተመረጡት ለጆ ቢደን እና ምክትላቸው ፕሬዝዳንት ካማላ ሀሪስ በድጋሚ የእንኳን ደስ ያላችሁ መልክት አስተላልፈዋል። ሜርክል ከዋና መዲና በርሊን ባስተላለፉት የእንኳን ደስ ያላችሁ መልክት በተጨማሪ  ዩናይትድ ስቴትስ ከአትላንቲክ ባሻገር ግንኙነትዋን አጥብቃ እንድትቀጥል ጠይቀዋል። በአሁኑ ወቅት በዓለማችን የሚታዩትን ታላላቅ ተግዳሮቶችን ለመቋቋም አሜሪካ እና የአውሮጳ ሕብረት አካል የሆነችዉ ጀርመን በጋራ  መቆም ይኖርባቸዋል  ብለዋል።

DW Sendung Made in Germany | USA und EU
ምስል DW

«ዩናይትድ ስቴትስ እና የአውሮጳ ሕብረት አካል የሆነችዉ ጀርመን በዘመናችን ያሉን ታላላቅ ተግዳሮቶችን ለመቋቋም በአንድነት መቆም ይኖርባቸዋል። ሃገራቱ በዓለማችን የሚታየዉን የኮሮና ወረርሽኝ ቀውስ፣ የዓለም ሙቀት መጨመር እና የሚያስከትለውን አደጋ ብሎም ዓለም አቀፍ ሽብርተኝነትን ለመታገል  ጎን ለጎን  በመቆም በጋራ መጋፈጥ አለባቸዉ። ሁለቱ ሃገራት ክፍት ለሆነ ለዓለም ኢኮኖሚ እና ለነፃ ንግድ  መቆም ይኖርባቸዋል። ይህ ግንኙነት ለአትላንቲክ ባሻገርም ሆነ ለኛ የብልጽግና መሠረት ነው፡፡»

ሜርክል ዛሬ ከቀትር በፊት በይፋ ባስተላለፉት የእንኳን ደስ ያላችሁ መልክት የተመራጩን ፕሬዚደንት የጆ ባይደንን ከፍተኛ ልምድ ብሎም የምክትል ፕሬዝዳንትዋን የካሚላ ሀሪስን ምሳሌነት እንዲህ ጠቅሰዋል። 

« 46 ኛዉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ሆነዉ ለተመረጡት ለጆ ባይደን ልባዊ የእንኳን ደስ ያሎት መልክቴን ማስተላለፍ እወዳሉ።  ጆ ባይደን የዓመታት የሃገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ  የፖለቲካ  ልምድ ያላቸው ናቸው። ባይደን አውሮጳን ብሎም ጀርመንን ጠንቅቀው ያውቃሉ። ከባይደን ጋር ጥሩ ዉይይቶች ያደረኩባቸዉን ግዚያት አስታውሳለሁ። በሌላ በኩል ተመራጭዋን ምክትል ፕሬዚዳንት ካሚላ ሃሪስንም እንዲሁ ከልቤ እንኳን ደስ ያሎት ማለት እፈልጋለሁ። የፍልሰተኛ ልጅ ብሎም በዚህ ሥልጣን ላይ የመጀመርያዋ ሴት የሆኑት የሀሪስ፤ መመረጥ ስለ አሜሪካ ትልቅ ምሳሌ እንዲሆኑ ለብዙ ሰዎች ተነሳሽነትን የሚያጎናጽፉ አድርጎአቸዋል። አዲስዋን የአሜሪካ ምክክትል ፕሬዚዳንት መተዋወቁ ከልብ ያስደስተኛል።» 

ለአዲስ ተመራጮቹ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት እና ምክትል ፕሬዚዳንት የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የጀርመኑ ዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃይኮ ማስ በበኩላቸዉ፤ ሀገራቸዉ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋራ ያላትን ግንኙነት ማደስ እንደሚያስፈልግ  ተናግረዋል።  

US Wahl 2020 Deutschland Börse in Frankfurt
ምስል Frank Rumpenhorst/dpa/picture alliance

«በቅድምያ የአትላንቲክ ባሻገር ግንኙነታችንን ማደስ ያለብን ይመስለኛል። ወዳጅነታችን ማጠናከር ይኖርብናል። ትራምፕ ፤ ሩስያ፣ ቻይና እና አዉሮጳን የዩናይትድ ስቴትስ ተቀናቃኞች አድርገዉ ነበር የሚያቀርቡት። ነገሩ ግን እንደዚያ አይደለም፤ እኛ አጋሮች ነን ፤ ተባባሪዎች ነን ። በአጽናፋዊ ዓለም፤  ድንበር የማያግዳቸዉን ፈተናዎች ለምሳሌ የከባቢ አየር ለዉጥ፤ የሕዝብ ፍልሰት፤ መረጃን በቴክኖሎጂ መሰብሰብ የመሳሰሉት ሁሉ ነገሮች መፍትሄ ልናገኝ የምንችለዉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ስንቆም ብቻ ነዉ። ለዚህ ደግሞ ባለፉት አራት ዓመታት ከነበረን ግንኙነት በበለጠ የተጠናከረ የዩናይትድ ስቴትስን አጋርነት እንሻለን።» በጀርመን የተለያዩ ፖለቲከኞች በዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫና ዉጤቱ ደስታቸዉን እየገለፁ ነዉ። 

የአሜሪካ ምርጫ እና ዉጤቱ በአዉሮጳ እና አሜሪካ ቀጣይ ግንኙነት ላይ ያለዉ እንደምታ ምን ይሆን?

ሙሉ ዘገባዉን  የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ!

 

ገበያዉ ንጉሴ

ሸዋዬ ለገሰ