የታጣቂዎች ግድያ ያላባራበት የወለጋ ወረዳዎች
ሰኞ፣ ኅዳር 26 2015የምዕራብ ኦሮሚያ ዞኖች ሰላም ርቋቸው የጦር አውድማ ከሆኑ ዋል አደር ማለቱ እየተነገረ ነው። የአካባቢው ነዋሪዎች የአሁኑ ግድያ እና መፈናቀል ከምን ጊዜውም የባሰበት ነው ይላሉ። ሰሞኑን ምሥራቅ ወለጋ ዞን ውስጥ በሚገኙ ኪረሙ እና ጊዳ አያና ወረዳዎች ውስጥ አንደኛው ሌላኛውን የሚከስበት የማፈናቀልና ግድያ ተግባራት እየተፈጸመ መሆኑን የደረሰን ዘገባ ያመለክታል። ባለፈው ሳምንት በኪረሙ እና ጊዳ አያና ወረዳ ጉቲን ከተማ የተጀመረው ጥቃት እስከ ሳምንቱ መጨረሻ ቀጥሎ በተለይም ከኪረሙ ወረዳ ነዋሪዎችን ሙሉ በሙሉ ማፈናቀሉ ተነግሯል። በጊዳ አያና ወረዳ ጉቲን ከተማም በታጣቂዎች ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጭምር ያነጣጠረው ጥቃት በተለይም ከቅዳሜ ጠዋት ጀምሮ ተባብሷል። በዚህም የበርካቶች ሕይወት ሲቀጠፍ ብዙሃኑን አፈናቅሏል እየተባለ ነው።
ቅዳሜ ጠዋት ምሥራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ ጉቲን ከተማ ውስጥ ድንገት ሳይጠበቅ ከማለዳው ጀምሮ ደርሷል የተባለውን ጥቃት ሸሽተው አሁን ነቀምቴ ከተማ ውስጥ እንደሚገኙ የገለጹት ነዋሪ ማኅበረሰቡ ንጋቱን የተቀበለው እንደ ውርጅብኝ በሚወርድ ጥይት ነው ይላሉ።
«የፀጥታ ስጋቱ አዲስ አይደለም። ኅብረተሰቡ ምላሽ በማጣቱ ነው እንጂ አቤት ማለት ከጀመረ ውሎ አድሯል። የቅዳሜ ጠዋቱ ጥቃት ደግሞ ኅበረተሰቡ በዚሁ ጭንቀት ተቀጦ ሳለ ነው ድንገት በታጣቂዎቹ የተከፈተው። እነዚህ ታጣቂዎች በአከባቢው ላሉ የአማራ ተወላጆች ጥበቃ እንዲያደርጉ የታጠቁ ነበር። ከመንግሥት ጋር በተለይም ከኦሮሚያ ልዩ ኃይል ጋርም ተናብበው የፀጥታ ስምሪት የሚያደርጉ ነበር። በኋላ ግን እነዚህ ታጣቂዎች በሰላማዊ ዜጎች ላይም እርምጃ መውሰድ ሲጀምሩ ሁለቱ አካላት ግጭት ውስጥ ገቡ። ቅዳሜ ጠዋትም የኦሮሚያ ልዩ ኃይል፤ ኃይሉን ወደ ኪረሙ ከተማ ሲያሰማራ ነው ንጹሐንም ላይ ጥቃት የከፈቱ።»
በዚሁ ቅዳሜ በተባባሰው የጉቲን ግጭት ተፈናቅለው አሁን ቤተሰቦቻቸውን ይዘው በየጫካው እየተንከራተቱ መሆኑን የሚገልጹት የአማራ ተወላጅ ደግሞ ከዚህ የሚቃረን አስተያየት ነው የሚሰጡት። እንደ እኚህ አስተያየት ሰጪ በቅዳሜው ጥቃት ብቻ በጉቲን ከ34 በላይ ንጹሐን ተቀብረዋል። ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ የመከላከያ ሠራዊት በስፍራው ቢደርስም አሁንም ድረስ ግን መረጋጋት ባለመፍጠሩ በየጢሻው የተገደሉትንም ማንሳት አዳጋች ሆኗል። እኚሁ ነዋሪ የአማራ ተወላጆችን ያሳድዳል ሲሉ የሚከሱት አካል «በበርካታ ኦራል መኪና የሚንቀሳቀሱና የክልሉን ልዩ ኃይል መለዮ የሚለብሱ ናቸው» ይላሉ።በምስራቅ ወለጋ ጉትን ከተማና አካባቢው የጸጥታ ችግር
የጉቲን 01 ቀበሌ ተፈናቃዩ ግን ሌላኛውን ተቃራኒ አስተያየት ሰጥተዋል። «መሳሪያ ታጥቀው፤ ከተማውን የሚጠብቁ፣ ከመንግሥት ጦር ጋራ ሸኔ እናድናለን ብለው እስከ ሳሲጋ የሚዘልቁት እነሱ ናቸው፤ እንዴት ይነካሉ እነሱ፤ አስቀድመው በመኪና ቤተሰቦቻቸውን አጅበው ሲያሸሹ አልነበረም ወይ ወደ ነቀምቴ እና አዲስ አበባ። እንደውም የኅብረተሰቡ ጥያቄ የመንግሥት አካል የተለየ ድጋፍ ለነሱ ለምን ደረጋል የሚል ነበር። ልዩ ኃይሉም እያሰለጠነ አብሮያቸው እየሠራ ነበር አሁን አፈሙዙን ያዞሩባቸው» ይላሉ ነዋሪው።
በወለጋ በተለያዩ ዞኖች በአማራ ላይ ይደረጋት ያሉትን ጥቃት ሸሽተው ከተለያዩ አከባቢዎች አንጻራዊ ሰላም ይስተዋልባት ነበር ወዳሉት ጉቲን መፈናቀላቸውን የሚገልጹት የአማራ ተወላጅ አስተያየት ሰጪ ግን ህዝቡ ከአንድም ሁለቴ መፈናቀሉን አንስተዋል። ከአከባቢው ሰላም በመራቁ ከምን ጊዜውም የከፋ ግጭት እንዳፈጠር መንግሥት ከአከባቢው ሊያስወጣን ይገባል ሲሉም ጠይቀዋል።
ሰሞኑን በምሥራቅ ወለጋው ሁለቱ ወረዳዎች ተባብሶ ስለቀጠለው ጥቃት ከፌዴራልም ሆነ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት የተባለ ነገር የለም። አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የኪረሙ ወረዳ ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ከፍያለው ገመዳ እንዳሉት ግን በሰመሞነኛው ግጭት ከኪረሙ ወረዳ ማኅበረሰቡ ሙሉ በሙሉ ተፈናቅሏል። «የአከባቢው ህዝብ በፀጥታው ችግር የተነሳ ወደ አጎራባች ወረዳዎች ተፈናቅሏል። በዚሁ ወረዳ ሀሮ በምትባል ቀበሌ ውስጥ የተደራጁ ፋኖ የተባሉ ጽንፈኛ ኃይሎች መጥተው ቢሮ እና የነዋሪዎችን ቤት አጋዩብን። ንብረትም ዘርፈው ህዝብን ሙሉ በሙሉ ኪረሙ ከተማ ሳትቀር ተፈናቀሉ። የህዝብ ደህንነት ለማስጠበቅ የተሰማራውን የመንግሥት ኃይልም መጥተው ከአቅም በላይ ሆነዋል። አሁን ሠራዊቱ ወደ ካምፕ ተመልሶ ነው እራሱን እየተከላከለ የሚገኘው። እዚህ ያለው ኃይል ህዝብ ማዳን ስላልቻለ ነው መፈናቀሉ ግድ የሆነው» ብለዋል። የፖሊስ አዛዡ ተጨማሪ ኃይል ወደ ስፍራው እንዳይደርስ ፅንፈኛ ያሉት የታጠቀው የፋኖ ኃይል በየቦታው ተደራጅቶ ይከላከላል ብለዋል። መንግሥት በራሱ ባደራጀው ኃይል ተኩስ ተከፍቶበታል በሚል ስለሚነሳው አስተያየትም የተጠየቁት የወረዳው ፖሊስ አዛዥ፤ «ይሄ እውነት አይደለም። መንግሥት ሌላ ጠላት ለማጥፋት ብሎ አላደራጃቸውም። ሕገወጥ የጦር መሳሪያ ከአጎራባች ክልል ስለሚገባለት ነው ተጠናክረው አከባቢውን የተቆጣጠሩት እንጂ፤ እንዴት መንግሥት በራሱ ዜጋ ላይ ሕገወት ቡድን ያደራጃል ብላችሁ ታስባላችሁ?» ሲሉ መልሰዋል።
ሥዩም ጌቱ
ሸዋዬ ለገሠ
ታምራት ዲንሳ