የታገቱት የ272 ሰዎች ጉዳይ
ሰኞ፣ መጋቢት 9 2016ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለቀን ሥራ ተመልምለው በጉዞ ላይ የነበሩ 272 ሰዎች ፋኖ በተባለው ታጣቂ ቡድን ከታገቱ ዛሬ 21 ቀናት ሆኗቸዋል ፡፡ ታጋቾቹ ከሦስት ሳምንታት በፊት ከክልሉ ጋርዱላ ፣ አሌ እና ኮንሶ ዞኖች ተመልመለው ወደ ህዳሴ ግድብ በጉዞ ላይ እንዳሉ የታገቱት ምሥራቅ ጎጃም ዞን ጎዛምን ወረዳ ውስጥ ነው ፡፡
ታጋቾቹ ለጉልበት ሥራ ወደ ህዳሴ ግድብ መሄዳቸውን እንደሚያውቁ በጋርዱላ ዞን የአጥያ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ሁለት የታጋች ቤተሰብ አባላት ገልጸዋል ፡፡ የቤተሰብ አባላቱ ከሳምንታት በፊት ተጋቾቹን በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከተመለከቱ በኋላ አሁን ላይ ያሉበትን ሁኔታ እንደማያውቁ በመጥቀስ በህይወት ይኖሩ ይሆን በሚል ጭንቀት ውስጥ እንደሚገኙ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል ፡፡ምዕራብ ጎንደር ዉስጥ የሰዎች መታገት ያሳደረዉ ስጋት
“ እኛ የምናውቀው ልጆቻችንን ለምንጣሮ ወደ ህዳሴ ግድብ እንደሚሄዱ ነው “ ያሉት የታጋች ቤተሰቦች “ በዞኑ በወጣው የስራ ማስታወቂያ ጥሪ መሠረት ነው የተመዘገቡት ፡፡ ከሥራ ውጭ ምንም አይነት የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው አይደሉም “ ብለዋል ፡፡
ዶቼ ቬለ በተጋቾቹ ሁኔታ ላይ ፋኖ የተባለውን ታጣቂ ቡድን አስተያየት ለማካተት ያደረገው ጥረት አልተሳካም ፡፡ ይሁንእንጂ ቡድኑ ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ ተጋቾቹ የተያዙት እንደተባለው ለደን ምንጣሮ ወደ ህዳሴ ግድብ ለመሄድ ሳይሆኑ ወታደራዊ ሥልጠና ለመውሰድ ነበር ሲል አስታውቋል ፡፡
የታጋች ቤተሰቦች አቤቱታ
በአሁኑወቅት በእገታ ላይ የሚገኙ ሠራተኞችን መልምሎ ለቀጣሪ ድርጅቶች ያስተላለፈው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮን በተደጋጋሚ መጠየቃቸውን የሚናገሩት የታጋች ቤተሰቦች “ ይሁንእንጂ ለጥያቄያችን ምላሽ ማግኘት አልቻልንም ፡፡ ቢያንስ የቢሮው አመራሮችን አግኝተን ማነጋገር አልቻልንም ፡፡በዚህም ምክንያት ልጆቻችንን በሕይወት ላናገኝ እንችላለን በሚል ሥጋት ውስጥ እንገኛለን ” ብለዋል ፡፡
ዶቼ ቬለ ታጋቾቹን መልምሎ ልኳል የተባለውን የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮን ለማነጋገር ጥረት ቢያደርግም ፤ የቢሮው ሃላፊ ዶክተር ዋኖ ዋሎ ምላሽ ለመስጠት የሥልክ ቀጠሮ ከያዙ በኋላ ሥልካቸው ዝግ በመሆኑ አስተያየታቸውን ማካተት አልተቻለም ፡፡እልባት የሚሹት የእገታ ወንጀሎች ነዋሪዉን እያማረሩ መሆኑ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በሠራተኞቹ እግታ ዙሪያ እስከአሁን ምንም ነገር አለማለቱን የጠቀሱት የታጋች ቤተሰቦች በበኩላቸው “ ይህም የሚመለከተው አካል ለጉዳዩ ትኩረት እንዳልሰጠው ያሳያል “ ሲሉ ወቅሰዋል ፡፡ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በአርባ ምንጭ ከተማ በተካሄደው የክልል ምክር ቤት ጉባዔ ላይ አንድ የምክር ቤት አባል “ በታጋቾቹ ደህንነተ ላይ ሥጋት አድሮብኛል “ በሚል ጥያቄያቸውን ለጉባዔው ቢያቀርቡም ከአስፈጻሚ አካላት ምላሽ ሳያገኙ ቀርተዋል ፡፡
በሽምግልና የማስለቀቅ ጥረት
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት አሁን በእገታ ላይ ይገኛሉ የተባሉትን 272 ሰዎች ከክልል ተረክቦ ወደ ህዳሴ ግድብ በማጓጓዝ ላይ የነበረው ኒኮትካ ኮንስትራክሽን የተባለ የግል ኩባንያ ነው ፡፡ ዶቼ ቬለ በሥልክ ያነጋገራቸው የኩባንያው ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙሉጌታ አለነ ኩባንያው በህዳሴ ግድብ ምንጣሮ ላይ የሚሠማሩ ሠራተኞችን ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በመመልመል ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲሰራ መቆየቱን አስታውቋል ፡፡ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የተመለመሉ 272 ሠራተኞቹም በተመሳሳይ መልኩ ወደ ህዳሴ ግድቡ በማቅናት ላይ እንዳሉ በፋኖ ታጣቂዎች እጅ መውደቃቸውን አቶ ሙሉጌታ ተናግረዋል ፡፡አሳሳቢዉ የሰዎች እገታ በኢትዮጵያ
በመሥመሩ የፀጥታ ችግር እንዳለ እየታወቀ ለምን በአማራጭ መንገዶችን አልተጠቀማችሁም ? አሁን ላይ ታጋቾቹ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ መረጃው አላችሁ ወይ ? በሚል በዶቼ ቬለ የተጠየቁት የኩባንያው የፕሮጀክት ሥራአስኪያጅ “ በአማራጭ መንገድ ርቀት ሥላለው ተጠቅመን አናውቅም ፡፡ ቀደምሲል ጀምሮ ሠራተኞችነ ስናጓጓዝ የነበረው በዚሁ የጎጃም መስመር ነበር ፡፡ የመንግሥት አካላትም በዚሁ መስመር ማለፍ እንደምንችል በነገሩን መሠረት ነው ጉዞው የተደረገው ፡፡ አሁን ኩባንያው ሃላፊነቱን ለመወጣት ችግሩ ወደተፈጠረበት አካባቢ በመሄድ ሠራተኞቹ በታጣቂዎቹ እጅ እንደሚገኙ አረጋግጧል ፡፡ ሠራተኞቹን በሰላም ለማስለቀቅ ጉዳዩን በባህላዊ የአገር ሽማግሌዎች ይዘን እንገኛለን “ ብለዋል ፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ኂሩት መለሰ
ታምራት ዲንሳ