የተሳሳተ የፈተና ውጤት ያስከተለው ቅሬታ
ሰኞ፣ መጋቢት 12 2014
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ከ12ኛ ክፍል ፈተና ውጤት ጋር ተያይዞ የሚነሳው የተማሪዎች ቅሬታ መፍትሔ እስኪያገኝ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ጊዜ እንዲራዘም ጠየቀ፡፡ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት ብዙ ችግሮች ያሉበት በመሆኑ ፈተናው እንደገና እንዲታረም፣ አሊያም ተማሪዎቹ እንደገና እንዲፈተኑ ደግሞ በአማራ ክልል የሚገኙ የከፍተኛ ተቋማት ፎረም አመልክቷል፡፡
የ2013 ዓም የ12ኛ ክፍል ፈተና ውጤትና የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ነጥብ አሁንም በአማራ ክልል ውዝግብ እንዳስከተለ ነው፡፡ በአማራ ክልል እስካሁን ከፍተኛውን ውጤት ያስመዘገበው የአማኑኤል ፀሐይ ወላጅ አባት አቶ ፀሐይ ወንድም በልጃቸው ላይ ተፈጥሮ የነበረው የውጤት ስህተት በቤተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ መረበሽ ፈጥሮ ነበር ይላሉ፡፡
አማኑኤል መጀመሪያ 162 እንዳስመዘገበ የተነገረው ሲሆን ከምርመራ በኋላ የተማሪው ውጤት 647 ሆኖ ተገኝቷል፣ ይህ ደግሞ እስካሁን ባለው መረጃ በአማራ ክልል ከፍተኛው ነው ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል በአማራ ክልል የከሚሴ መሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪ “በጦርነት ውስጥ ሆነን ተፈትነን ከሌሎች ሰላማዊ ከሆኑ አካባቢዎች ከተፈተኑት እኩል የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት መወሰኑ በእጅጉ የጎዳን ነው” ትላለች፡፡
አንድ የወልዲያ ከተማ የተማሪ ወላጅም የተማሪዋን ሀሳብ ይጋሩታል፡፡
በአማራ ክልል የሚገኙ የከፍተኛ ተቋማት ፎረም ዋና ፀሓፊ ዶ/ር አስማረ ደጀን በክልሉ የተመዘገበው የ12ኛ ክፍል ውጤት ችግር ያለበት በመሆኑ ፈተናው እንደገና መታረም አለበት አለዚያ ተማሪዎቹ ሌላ ፈተና ሊፈተኑ ይገባል ብለዋል፡፡
የአገርአቀፍ ፈተናዎች ኤጀንሲ ተደጋጋሚ ስህተቶችን እየፈፀመ በመሆኑ ሊፈተሸ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ማተቤ ታፈረ በበኩላቸው የተማሪዎች ቅሬታ መልስ እስኪያገኝ ድረስ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ጊዜ እንዲራዘም ትምህርት ሚኒስቴርን መጠየቃቸውን አመልክተዋል፡፡
በጦርነት ውስጥ ስለነበሩ ተማሪዎች የዩኒቨርሲቲ መግቢያ የተጠየቁት ዶ/ር ማተቤ ትምህርት ሚኒስቴርም ሆነ የአማራ ክልል ቢሮ እንዳረጋገጠው በአካባቢው የተመዘገበው ውጤት እንዲያውም በምዕራብ አማራ ከነበረው በአማካይ የተሻለ እንደነበረ ነው ያስረዱት፡፡
የአገር አቀፍ ፈተናዎች አጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ፈይሳ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ የ20ሺህ ተማሪዎችን ቅሬታ ኤጀንሲያቸው መመልከቱንና ችግር የነበረበት የ559 ተማሪዎች ውጤት እንዲሰተካከል ተደርጓል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ኂሩት መለሰ
አዜብ ታደሰ