1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የብልጽግና እና የህወሓት ልዩነት እንዴት ከረረ?

ረቡዕ፣ ጳጉሜን 4 2012

ዛሬ የሚወነጃጀሉት የህወሓት እና የብልጽግና ፓርቲ ሰዎች ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት የአንድ ግንባር አባል ነበሩ።አብዮታዊ ዴሞክራሲን ያቀነቅን በነበረው ግንባር መሪነት ኢትዮጵያን ከሁለት አስርት አመታት በላይ ጸጥ ለጥ አድርገው ገዝተዋል። ልሒቃኑ ኢሕአዴግ ፈርሶ ህወሓትን ሳይጨምር ብልጽግና ከተመሰረተ ወዲህ የሚስማሙባቸው ጉዳዮች ማግኘት ያስቸግራል

https://p.dw.com/p/3iElk
Äthiopien Regierungsvertreter
ምስል DW/Tesfalem Waldyes

የብልጽግና እና የህወሓት ልዩነት እንዴት ከረረ?

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ የትግራይን ምርጫ "ከዕድር" አመሳሰሉት። «ምርጫ አይደለም ይሔ። ምርጫ የሚሆነው የምርጫ ቦርድ ሲመራው ብቻ ነው። ይሔን ልክ እንደ ጉባኤ፤ ልክ እንደ ዕድር ስብስብ አድርገህ መውሰድ ነው።» ያሉት ዐቢይ በመንግሥት ከሚተዳደረው ብሔራዊው የቴሌቭዥን ጣቢያ ጋር ባደረጉት ቃለ-መጠይቅ «ሕገ -ወጥ» ያሉት ምርጫ በትግራይ የሥልጣን ክፍፍል የሚያመጣው ለውጥ እንደማይኖር ፈርጠም ብለው ተናግረዋል። «አሁንም ህወሓት ነው እየመራ ያለው። ይኸ የሚባለው የጨረቃ ጨዋታም ቢያልፍ ህወሓት ነው የሚመራው» ነበር ያሉት።

ጠቅላይ ምኒስትሩ «የጨረቃ ጨዋታ» ሲሉ ባጣጣሉት ምርጫ 2.7 ሚሊዮን ዜጎች የትግራይ ክልል ምክር ቤት አባላትን ለመምረጥ ተመዝግበዋል። ድምጽ ሲሰጡም ውለዋል። የፌዴሬሽን ምክር ቤት «የማይፀና እና ተፈፃሚነት የሌለው» ይሆናል ባለው በዛሬው ምርጫ ከሚሳተፉ አምስት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል አንዱ «ነፃ አገረ ትግራይ» ለማቆም ያቀደ ነው።

የመቐለ ዩኒቨርሲቲው መምህር እና የትግራይ ነጻነት ፓርቲ ሊቀ-መንበር አቶ ግርማይ በርኸ «በርካታ ሰዎች ኢትዮጵያን ራሷን ማጠየቅ ጀምረዋል። ልሒቃኑ እና ወጣቶች እኛ በሠራንው ትንታኔ መሥማማት ጀምረዋል። በዚህ ወቅት ያገኘንው ተቀባይነት ከጠበቅንው በላይ ነው» ሲሉ ተናግረዋል። ከዛሬው ምርጫ በፊት አምስቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ባደረጉት ክርክር አቶ ግርማይ «የትግራይ ሕዝብ ሙሉ ሉዓላዊነት፤ ሙሉ ነፃነት» ይገባዋል ሲሉ ተደምጠዋል።

አቶ ግርማይ በትግራይ ልሒቃን እና በወጣቶች ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝቷል ያሉት ይኸንኑ አገረ ትግራይ የማቆም ሐሳብ ነው። ይኸ ሐሳብ በክልሉ እንዲበረታ ካደረጉት ምክንያቶች በትግራይ ተወላጆች ላይ በርትቷል የሚባለው ጥቃት እና ውንጀላ ይገኝበታል። በተለይ በአገሪቱ ተፈጽመዋል ለሚባሉ ጥፋቶች የትግራይ ሰዎችን ለይቶ መወንጀል በርትቷል የሚለውን ክስ ከሚጋሩት መካከል አንዱ የሆኑት የሰርከስ ትግራይ ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ገብረዮሐንስ «የሆነ ነገር ሲሆን ትግራይ…ትግራይ…ለምን እንደዚህ እንደሆነ ግራ ነው የሚያጋባው። ይኼ ሕዝብ እኮ ለኢትዮጵያ ሞቷል። እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ለኢትዮጵያ አንድነት ሕይወት ከፍሏል» ብለዋል። 

የትግራይ ልሒቃን እና የፌድራል መንግሥቱ ውዝግብ በኮሮና ምክንያት የኢትዮጵያ ምርጫ በመራዘሙ ይበርታ እንጂ ዐቢይ ሥልጣን ከያዙ ጀምሮ ሲፋፋም የቆየ ነው። በታላቁ የኅዳሴ ግድብ ግንባታ ውስጥ ነበር ለተባለው ሙስናም ይሁን ለመጓተቱ ጠቅላይ ምኒስትሩን ጨምሮ የፌድራል መንግሥቱ ባለሥልጣናት ጣታቸውን በገደምዳሜም ቢሆን የህወሓት ሹማምንት ላይ ሲጠቁሙ ታይቷል። ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ዕርቅ አወረዱ ከተባለ ወዲህ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የፈጠሩትን «ምስጢራዊ» የተባለ ወዳጅነት በርካታ የትግራይ ልሒቃን ዛሬም ድረስ በጥርጣሬ ይመለከቱታል። ግንኙነቱንም ትግራይን ለመጉዳት የሚደረግ የከበባ ሥልት አድርገው የሚያቀርቡት በርካቶች ናቸው። 

የብልጽግና እና የህወሓት፣ የትግራይ እና የፌድራል መንግሥቱ መቃቃር ዛሬ በተካሔደው ምርጫ ወደ አዲስ ደረጃ ተሸጋግሯል። የምርጫው ውጤት ምንም ይሁን ምን በሁለቱ ኃይሎች መካከል ያደገው ቅራኔ እንዲህ በቀላሉ ይፈታ ይሆን? 

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ