1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቀጠለው የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ሀገራት ውዝግብ

ሐሙስ፣ መስከረም 2 2017

የኢትዮጵያና ሶማሊላንድ የመግባቢያ ውል መደበኛ ሥምምነት ሆኖ እንደሚፈረም የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኢሳ ካይድ ለዲፕሎማቶች ተናግረዋል። ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የግብጽ ወታደሮች በሶማሊያ መሠማራት ለሶማሊላንድ አሳሳቢ ብለውታል። ሶማሊላንድ በሐርጌሳ የሚገኝ የግብጽ ባሕላዊ ቤተ-መጻህፍት ዘግታ ሠራተኞቹ በ72 ሰዓታት ለቀው እንዲወጡ አዛለች።

https://p.dw.com/p/4kY04
የሶማሊላንድ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
የሶማሊላንድ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በይፋዊ የ ኤክስ ገጹ ባወጣው አጭር መግለጫ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሀርጌሳ ውስጥ ላሉ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማቲክ ሚሲዮኖች ማብራሪያ መስጠታቸውን በመጥቀስ የሶማሊላንድ እና የኢትዮጵያ የባሕር በር ማስገኛ የመግባቢያ ስምምነት ወደ መጠናቀቁ መሆኑን እንዲሁም መደበኛ የሕግ ስምምነት መሆኑ አይቀሬ ስለመሆኑ አሳውቋል።ምስል Eshete Bekele/DW

የቀጠለው የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ሀገራት ውዝግብ

የሶማሊላንድ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በይፋዊ የ ኤክስ ገጹ ባወጣው አጭር መግለጫ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሀርጌሳ ውስጥ ላሉ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማቲክ ሚሲዮኖች ማብራሪያ መስጠታቸውን በመጥቀስ የሶማሊላንድ እና የኢትዮጵያ የባሕር በር ማስገኛ የመግባቢያ ስምምነት ወደ መጠናቀቁ መሆኑን እንዲሁም መደበኛ የሕግ ስምምነት መሆኑ አይቀሬ ስለመሆኑ አሳውቋል።

ሚኒስትሩ የሶማሊላንድ መንግሥት ጎረቤት ባላት ሶማሊያ ውስጥ ተሰማሩ ያላቸው የግብፅ ኃይሎች ላይ ከፍተኛ ሥጋት እንዳለውና ይህም በቀጠናው ለውክልና ግጭት አጋዥ ይሆናል የሚል ብርቱ ሥጋት እንደሆነበት በእዚያ ለሚገኙ ዲፕሎማቶች ማሳወቁን አመልክቷል።

በባለስልጣናት የቃላት ምልልስ የቀጠለው የኢትዮ ሶማሊያ ዲፕሎማሲ ውጥረት

የሶማሊላንድ መንግሥት ከዚህ መግለጫው አስቀድሞ ተጋርጦብኛል ባለው የፀጥታ ሥጋት ምክንያት ሀርጌሳ ውስጥ የሚገኘውን የግብፅ የባሕል ቤተ መጻሕፍት እስከመጨረሻው መዝጋቱን ይፋ አድርጓል። ሶማሊላንድ የዚህን ተቋም ሠራተኞች በ72 ሰዓታት ውስጥ ለቀው እንዲወጡ ማዘዟም አነጋጋሪ ሆኗል።

የግብጽ የጦር አውሮፕላኖች ሞቃዲሾ ውስጥ በታዩበት ያለፉት ሳምንታት ሶማሊላንድ ሁኔታው የአካባቢውን ሰላም እና መረጋጋት አደጋ ላይ ይጥላል በሚል ክስተቱን በብርቱ መቃወሟም ይታወሳል።

ከተፈረመ ስምንት ወራትን ያለፈው የኢትዮጵያ እና የሶማሊላንድ የባሕር በር የመግባቢያ ስምምነት ምን ደረጃ ላይ ደርሷል? በሚል ባለፈው ሳምንት አዲስ አበባ ውስጥ በጋዜጠኞች የተጠየቁት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀ ሥላሴ ተከታዩን ምላሽ ሰጥተው ነበር

"የመግባቢያ ስምምነቱ አሁንም አለ። የበለጠ ተጨማሪ የመግባቢያ ስምምነቶችን መትከል ያስፈልገናል። ከሌሎች ሀገሮች ጋር መፈረም እንፈልጋለን። ማንም ሰው በቅን ልቦና እና በጎ ፈቃድ የባህር ዳርቻን ሊሰጠን ይችላል ምክንያቱም እኛ መታፈን ስለማንፈልግ፣ እንደ ሰው ማደግ እንፈልጋለን"

ይህ በዚህ እንዳለ በካይሮ የሚገኘው የአረብ ሊግ ዋና መሥሪያ ቤት ላይ ትናንት የተሰበሰቡ የአረብ የሚኒስትሮች የሥራ ቡድን ለሶማሊያ ጠንካራ ድጋፍ እና አጋርነት እንዳላቸው አረጋግጠዋል ተብሏል። የውጭ ጣልቃ ገብነትን ውድቅ በማድረግ የሶማሊያን ሉዓላዊነት እንዲከበር የጠየቀው ይሄው ቡድን፣ የኢትዮጵያን እና የሶማሊላንድን የመግባቢያ ስምምነት ውድቅ ስለማድረጉም ተሰምቷል።

ማሕደረ ዜና፣ የአፍሪቃ ቀንድ የጦርነት ሥጋት

ሚኒስትሮቹ የሶማሊያ ጎረቤት ሀገራት በተለይም ኢትዮጵያ በስም ተጠቅሳ ሶማሊያን ከሚያናጉ ወይም ሉዓላዊነቷን ከሚያደፈርሱ ድርጊቶች እንድትታቀብ አሳስበዋል ተብሏል።

በስብሰባው ላይ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቻቸው በኩል የተወከሉት ሳዑዲ አረቢያ፣ ባህሬን፣ ሞሪታኒያ እና ግብፅ ሲሆኑ የጅቡቲ አምባሳደር እና የአረብ ሊግ ዋና ፀሐፊም መሳተፋቸውና የመግባቢያ ስምምነቱን (MoU) ውድቅ ስለማድረጋቸው ተዘግቧል።

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታዬ አጽቀ ሥላሴ
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታዬ አጽቀ ሥላሴ "በአንካራ ሂደት መሰረት ከሶማሊያ ጋር ስምምነት ላይ የመድረስ ተስፋ አለ" ብለው ነበር። ምስል Solomon Muchie/DW

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አፅቀ ሥላሴ በቱርክ አሸማጋይነት የተጀመረው የሰላም ጥረት ስኬታማ እንዲሆን የኢትዮጵያ ፍላጎትም ምርጫም መሆኑን ገልፀው ነበር።

"በአንካራ ሂደት መሰረት ከሶማሊያ ጋር ስምምነት ላይ የመድረስ ተስፋ አለ። የዚህ ምክንያቶች፣ በመጀመሪያ እንደ ሀገር በተለይ በመግባቢያ ስምምነቱ ምክንያት ከሶማሊያ ጋር  ያሉንን ልዩነቶች በሰላም ለመፍታት ዝግጁ መሆናችንን እንመርጣለን። በእርግጥም በዚህ እምነት ነው ሰላማዊ ንግግሮችን ለማድረግ ቆራጥነታችንን ያሳየነው"

ጎረቤት ሀገር ሶማሊያ ከግብጽ ጋር ልዩ ልዩ ወታደራዊ ስምምነቶችን ማድረጓ እንዳለ ሆኖ፣ የግብጽ ሠራዊት ለሰላም ማስከበር ተልዕኮ በቀጣይ ሶማሊያ ውስጥ እንዲሰማራ ጠይቃለች። ይህ ኢትዮጵያን በእጅጉ ያሳሰበ ሲሆን ሶማሊላንድም ሁኔታውን አበክራ ተቃውማለች።

  ግብጽን ያንደረደረው ውጥረት በሶማሊያና ኢትዮጵያ መካከል

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ "ፍላጎታችን ሰላም እና ሁለንተናዊ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ ነው። ማንም አካል ኢትዮጵያን ለመድፈር ሲፈልግ ግን አንዴ ሳይሆን ሥር ጊዜ ማሰብ ይኖርበታል" ሲሉ ባለፈው ሳምንት ተናግረዋል።

በቀጣናው ወቅታዊ የፖለቲካ ኑባሬ ላይ ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ተንታኞች እየተካረረ የመጣው የየሀገራቱ ሁኔታ ጦርነትን ሊያስከትል እንደሚችል ሥጋታቸውን ሲገልፁ፣ አካባቢው ካለው ዓለም አቀፍ ስልታዊ ጠቀሜታ አንፃር ጦርነት የሚታሰብ አይደለም ሲሉም የተለያዩ አስተያየቶችን  ያንፀባርቃሉ።

ሰለሞን ሙጬ

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ