የሶማሊያ እና የቱርክ ስምምነት አንድምታዎች
ሐሙስ፣ የካቲት 21 2016
ቱርክ እና ሶማሊያ ባለፈው ሳምንት ከፍተኛ የመከላከያ እና የኢኮኖሚ ትብብር ስምምነት ተፈራርመዋል። በ10 አመቱ ስምምነት መሰረት ቱርክ የሶማሊያን ረጅም የባህር ዳርቻ ለመጠበቅ እና ደካማውን የአፍሪካ ቀንድ የባህር ሃይል እንደገና ለመገንባት ታግዛለች። የቱርክ መከላከያ ሚኒስቴር ባለስልጣን እንደገለፁት «ሶማሊያ በግዛቷ የባህር በር ላይ የሚደረጉ ህገወጥ እና መደበኛ ያልሆኑ ተግባራትን ለመዋጋት አቅም እንዲኖራት እናግዛለን»ብለዋል። በአንካራ የሃቺ ባይራም ቬሊ ዩኒቨርሲቲ የቱርክ አፍሪካ ግንኙነት ተንታኝ ዩኑስ ቱርሃን እንደሚሉት ፤
ስምምነቱ በሶማሊያ አልሸባብን ለማዳከም ያግዛል።
«ስምምነቱ ሶማሊያ ከአልሸባብ እና ከአሸባሪዎች ለገጠማት ጥቃት እና የውስጥ ፈተና መልዕክት አለው።በስምነቱ የሶማሊያ መንግስት ደስተኛ ነው። እንዲህ አይነት ስምምነት እየቀነሰ እና አልሸባብን በማዳከም እና በማጥፋት፣ በድንበር አካባቢ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴም ይቀርፋል።»
የሶማሊያ መንግስት በበኩሉ ስምምነቱ እንደ የባህር ላይ ወንበዴ እና ሽብርተኝነት ያሉ ስጋቶችን የመዋጋት አቅሙን ለማጠናከር እና በይበልጡኑ ደግሞ «የውጭ ጣልቃገብነት» ለመመከት ያግዛል የሚል ተስፋ አለው።
አንዳንድ ባለሙያዎች ይህንን ሀሳብ በሌላ መንገድ ይመለከቱታል።የራድ የሰላም ምርምር ኢንስቲትዩት ኃላፊ እና ተንታኝ ሞሃመድ ጋስ አንዱ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት በአዲሱ ስምምነት ቱርክ በሶማሊያ የምታደርገው ቁጥጥር ሰፊ እና ያልተገደበ ያደርግና ብዙ አለመግባባቶችን ይፈጥራል። መሀመድ ጋስ አያይዘውም አፍሪካውያን እንደመሆናችን መጠን አንዲት የአውሮፓ ሀገር በአፍሪካ ቀንድ ላይ እንዲህ ያለ ተፅዕኖ ወይም ወታደራዊ ኃይል ሲኖራት ያሳስበናል ብለዋል።
ያሉትን ውጥረቶች ማባባስ
የቱርክ እና የሶማሊያ ስምምነት የተደረገው ኢትዮጵያ ከሱማሌላንድ ጋር ባደረገችው የባህር ላይ ስምምነት ሳቢያ በሁለቱ ሀገራት መካከል ውጥረት በጨመረበት ወቅት ነው።
በስምምነቱም ኢትዮጵያ እንደሀገር እውቅና ላላገኘችው ለሶማሌላንድ እውቅና ልትሰጥ ነው በሚል ፤ሶማሊያ ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር የገባችውን ስምምነት በፅኑ ተቃውማለች።“ህገ-ወጥ ነው” ስትልም የሶማሊያን የባህር ላይ መብት እንደምታስጠብቅ ቀደም ሲል ገልፃለች።
ነገር ግን የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ ሞሃሙድ ከቱርክ ጋር ያለው ስምምነት የሶማሊያን የባህር ላይ ደህንነትን የሚመለከት ነው ሲሉ አፅንዖት ሰጥተዋል።
«ለሶማሊያ ህዝብ የምንናገረው ዛሬ ለፓርላማ ያቀረብነው ስምምነት በሶማሊያ እና በቱርክ መካከል በባህር መከላከያ እና ኢኮኖሚ ትብብር ላይ ብቻ ነው።. በምንም መልኩ ከሌላ ሀገር ወይም መንግስት ጋር ጥላቻ ወይም ጠብ ለመፍጠር ያለመ አይደለም» ብለዋል
የደህንነት አማካሪው ፊዴል አማኪ ኦውሱ ግን ከኢትዮጵያ አንፃር እንደዚህ አይነቶቹ ማረጋገጫዎች በቂ ላይሆኑ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
ነገር ግን የባህር መዳረሻ ሀሳብ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ተወዳጅ በመሆኑ፤ የቱርክ በአካባቢው መገኘት እንደ ስጋት ከታመነ መላው የሀገሪቱ ህዝብ ከመንግስት ጎን ሊሰሰለፍ ይችላል።የሚል ግምትም አላቸው።
በኢትዮጵያ ካለው የውስጥ ግጭት አንፃርም የቱርክ በዚያ አካባቢ መገኘት በኢትዮጵያ አቋም ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ኦውሱ ጠቁመዋል።
«ከትግራይ፣ ከአማራ እና ከኦሮሚያ ጋር የሚደረጉ የውስጥ ጦርነቶች የውጭ ጠላትን ከማሳደድ በፊት መፍትሄ ሊያገኙ ይችላሉ» ሲሉም ነበር ሃሳባቸውን የገለጹት።
ተንታኞች እንደሚሉት ሶማሊያ ከቱርክ ጋር ያላት ስምምነት ተለዋዋጩን የኢትዮጵያ ውስጥ ሃይል ሊያወሳስብ እና በቀጣይም በግጭቶች ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር ይችላል።
ክልላዊ አንድምታ
ክልላዊ አንድምታው ሲታይም፤ ስምምነቱ ቱርክ በሶማሊያ ዋና ተዋናይ መሆኗን የበለጠ ያጠናክራል። ቀደም ሲል ግንባር ቀደም የኢኮኖሚ አጋሯ ቱርክ በሀገሪቱ ትልቅ የጦር ሰፈር ያላት ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ የሶማሊያ የፀጥታ ሃይሎችን አሰልጥናለች። ይህ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚሄደው ተፅእኖ በአንዳንድ ወገኖች ዘንድ አሳሳቢ ነው።ምክንያቱም ለአካባቢው አለመረጋጋት እና ለሌሎች ዓለም አቀፍ ተዋናዮች መንገድ ይከፍታል።
አንዳንድ ባለሙያዎች ግን በሶማሊያ እና በቱርክ መካከል የረጅም ጊዜ ወታደራዊ ትብብር ስለነበረ እነዚህ ስጋቶች መሠረተ ቢስ ናቸው ብለው ያስባሉ።
ተርሃን እንደሚሉት በጎርጎሪያኑ 2017 ዓ.ም ቱርክ የመጀመሪያውን የባህር ማዶ ወታደራዊ ማሰልጠኛ በሞቃዲሾ ከፍታለች ። ይህ ወታደራዊ ጣቢያ ሳይሆን ወታደራዊ ማሰልጠኛ ነው ።ስለዚህ አልሸባብን በመዋጋት የሶማሊያ የመከላከያ አቅም የጀርባ አጥንት ነው ብለዋል ተርሃን። ጉዳዩ ያሳሰባቸው የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ከፍተኛ ዲፕሎማት ሞሊ ፒ በአዲስ አበባ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር በሞቃዲሾ ደግሞ ከፕሬዝዳንት ሀሰን ሼክ መሀሙድ ጋር በግል ተወያይተዋል።
ዩናይትድ ስቴትስ ሁለቱ ሀገራት ግንኙነታቸውን እንዲያሻሽሉ ለመርዳት ፈቃደኛ መሆኗን ገልፃለች።ኦውሱ ግን ፈተናው ከሶማሊያ እና ከኢትዮጵያሊያልፍ ይችላል የሚል ስጋት አላቸው።
የወደፊት መንገድ ፍለጋ
በአፍሪካ ቀንድ የወደፊት የባህር ደህንነት እጣ ፈንታ ህጋዊ ጥቅሞችን በማስጠበቅ እና የግዛት አንድነትን በማክበር መካከል ባለው ስስ ሚዛን ላይ ነው። ይህንን ውዝግብ ለመፍታትም ለውይይት እና ለክልላዊ ትብብር ቁርጠኛ መሆን ወሳኝ ነው ሲሉ ባለሙያዎች ገልፀዋል።
ተንታኞች እንደሚሉት የሶማሌ ላንድ የይዞታ ጉዳይ ከውጪ አካላት ይልቅ በሶማሌላንድ ያሉትን ጨምሮ በሶማሊያ ህዝብ መወሰን እንዳለበት አሳስበዋል። ቱርሃን ይህ ስምምነት አንዳንድ አወንታዊ ውጤቶች ሊኖረው እንደሚችል ያለቸውን ተስፋ ገልፀዋል።
«ምናልባት የቱርክ ስምምነት በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል በጠረጴዛ ላይ ውይይት እንዲደረግ ሊያደርግ ይችላል ምክንያቱም ችግሩን ለመፍታት ዲፕሎማሲው ብቸኛው መፍትሄ ነው» ብለዋል።
ኦውሱ በበኩላቸው ለክልላዊ ትብብር እና ስምምነት አስፈላጊነት ላይ አፅንዖት ሰጥተዋል። ሁሉም ወገኖች ለውይይት ቅድሚያ እንዲሰጡም አሳስበዋል።
«የአፍሪካ ህብረት አቋም ቱርክ ጠንካራ ሀይልን ከመጠቀም ይልቅ ድርድርን እንድትደግፍ የተወሰነ ጫና ሊፈጥር ይችላል...ሌላው ነገር በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የተወሰነ እርምጃ ከተወሰደ ሁለቱ በጠረጴዛ ዙሪያ መጥተው መነጋገር ይችላሉ» በማለት ተናግረዋል።
እናም "የወደፊቱ መንገድ መነጋገር ነው." ።ብለዋል።
ፀሀይ ጫኔ
ማንተጋፍቶት ስለሺ