1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰብዓዊ መብት ጥሰት በኦሮሚያ ክልል

ቅዳሜ፣ የካቲት 16 2016

በኦሮሚያ ግጭት የሚሳተፉ ሁሉም አካላት “ሲቪል ሰዎች ላይ ሆን ተብሎ እና በተስፋፋ ሁኔታ ከሕግ ውጪ ግድያዎችን” መፈጸማቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አስታውቋል። የኮሚሽኑ ምርመራ የመንግሥት የጸጥታ አስከባሪዎች እና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ብርቱ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እንደፈጸሙ አጋልጧል።

https://p.dw.com/p/4cpmL
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሎጎ
በኦሮሚያ ግጭት የሚሳተፉ ሁሉም አካላት “ሲቪል ሰዎች ላይ ሆን ተብሎ እና በተስፋፋ ሁኔታ ከሕግ ውጪ ግድያዎችን” መፈጸማቸውን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አስታውቋል።ምስል Ethiopian Human Rights Commission

የሰብዓዊ መብት ጥሰት በኦሮሚያ ክልል

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በኦሮሚያ ክልል ከመስከረም 1 ቀን 2014 ዓ.ም. እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ባሉት ሁለት ዓመታት ባደረገው ክትትል እና ምርመራ ከሕግ ከፍርድ ውጪ የሆኑ እና በሲቪል ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ግድያዎች በከፍተኛ ደረጃ አሳሳቢ መሆናቸውን አመልክቷል።

ኮሚሽኑ ከተጎጂዎች፣ ከተጎጂዎች ቤተሰቦች፣ ከዐይን ምስክሮች፣ ከሕክምና ባለሙያዎች በአጠቃላይ 158 ሰዎችን በማነጋገር ባገኘው መረጃ በ9 ዞኖች የሚንቀሳቀሱ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች፣ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት እና ኢ-መደበኛ የአማራ ታጣቂዎች ዓለም አቀፍ እና ሀገር አቀፍ የሰብአዊ መብቶች እና የሰብአዊነት ሕጎችን በመጣስ "በርካታ ሲቪል ሰዎችን ከሕግ ወይም ከፍርድ ውጪ" መግደላቸውን ኮሚሽኑ ማረጋገጡን ገልጿል። በኮሚሽኑ የሰብዓዊ መብቶች ክትትል እና ምርመራ ሬጅናል ዳይሬክተር አቶ ይበቃል ግዛውን ተጨማሪ ማብራሪያ ጠይቀናቸዋል።

«በኦሮሚያ መንግሥት በሚያካሂዳቸው ዘመቻዎች ንጹሃን ዜጎች የጥቃት ሰለባ እየሆኑ ነው»

በተጨማሪም "በርካታ ሲቪል ሰዎች ለከባድ እና ቀላል የአካል ጉዳት፣ ለተስፋፋ እገታ፣ መፈናቃል እና ዝርፊያ ተዳርገዋል" ተብሏል። የደረሱ ጉዳቶች “እጅግ ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች” ናቸው።

በኦሮሚያ ክልል በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ተገድለዋል የተባሉት ወይዘሮ ኩሊ ሃዋስ
ወይዘሮ ኩሊ ሃዋስ በቦሰት ወረዳ “ልጆችሽ ጫካ ገብተው ይዋጉናል” በሚል ሰበብ ባለፈው ጥቅምት 2016 በመንግሥት ጸጥታ ኃይሎች መገደላቸውን ለደሕንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የቤተሰብ አባል ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።ምስል Privat

ተጠያቂነት እንዲሰፍን መጠየቁ

ብሔራዊው  የመብት ተቋም - ኢሰመኮ በግጭቱ ተሳታፊ የሆኑ አካላት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተኩስ አቁም አድርገው ለሰላማዊ መፍትሔ በቁርጠኝነት እንዲንቀሳቀሱ፣ "መንግሥት በዚህ ላይ ተሳትፎ ያላቸውን ተጠያቂ ለማድረግ፣ ነፃ፣ ግልጽ እና የሰብዓዊ መብቶችን ደረጃ የሚያሟላ የወንጀል ምርመራ እና የክስ ሂደት እንዲጀምር፣ ተጎጅዎችም እንዲካሱ" እንዲያደርግ ጠይቋል።

የዝቋላ ገዳም መነኮሳት ግድያ

ግድያዎች የተፈፀሙባቸው ዘጠኝ ዞኖች

ኢሰመኮ በኦሮሚያ ክልል በመንግሥት እና በታጣቂ ቡድኖች በሲቪል ሰዎች ላይ ግድያዎች የተፈፀሙት በቄለም ወለጋ፣ ምሥራቅ ወለጋ፣ ሆሮ ጉድሩ ወለጋ፣ ጉጂ፣ ምዕራብ ጉጂ፣ አርሲ፣ ደቡብ ምዕራብ ሸዋ፣ ሰሜን ሸዋ እና ምሥራቅ ሸዋ ዞኖች መሆኑን አስታውቋል። 

በኦሮሚያ ክልል ለሚፈፀም ግድያና እስራት የባለስልጣናት ትዕዛዝ አለበት መባሉ

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በክልሉ ለሚፈፀም ከሕግ  ውጭ የሆነ ግድያ እና እሥራት አንድ ከፍተኛ የባለሥልጣናት ሚስጥራዊ ኮሚቴ ትዕዛዝ ሲሰጥ መቆየቱን እንዳረጋገጠ ሬውተርስ ትናንት ይፋ ያደረገው የምርመራ ዘገባ ያመለክታል።

አማጽያንን ለመደምሰስ በሚል ከሕግ አግባብ ውጭ ግድያ እና ሕገወጥ እስራት እንዲፈፀም ትዕዛዝ ይሰጥ የነበረው  "ኮሬ ነጌኛ" - የደኅንነት ኮሚቴ  በሚባል አካል መሆኑንም ጠቅሷል።

ሰለሞን ሙጬ

እሸቴ በቀለ