1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሰላም ተስፋ፣ስጋቱና እንቅፋቱ

ሰኞ፣ ኅዳር 12 2015

ስምምነቱ፣ ለገቢራዊነቱ የተገባዉ ቃልም በትንሹም ቢሆን ገቢር ሆነ።ጠቅላይ ሚንስትሩ አዲስ አበባ ላይ ለምክር ቤት እንደራሴዎች ማብራሪያ ሲሰጡ የርዳታ መድሐኒትና የሕክምና ቁሳቁስ የጫኑ መኪኖች መቀሌ መግባታቸዉን የዓለም ቀይ መስቀል ኮሚቴ አስታወቀ።በማግስቱ ሮብ የዓለም ምግብ ድርጅት (WFP) የላከዉ የርዳታ እሕል ትግራይ ገባ

https://p.dw.com/p/4JpnN
Tigray-Krise in Äthiopien
ምስል Eduardo Soteras/AFP

«የኤርትራ ጦር በሚንቀሳቀስባቸዉ አካባቢዎች የሕዝባችን ስቃይ አልቆመም» ጌታቸዉ ረዳ

የኢትዮጵያ መንግስትና የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ለተፋረሙት የሰላም ስምምነት፣ ከዉጪም ከዉስጥም የሚሰጠዉ ድጋፍ፣አድናቆትና ዉንዳሴ  እንደቀጠለ ነዉ።ተፈራራሚዎች ስምምነቱን ገቢር ለማድረግ ቃል እየገቡ፣ገቢር የማድረጋቸዉ ጅምርንም እያስመሰከሩ ነዉ።የዚያኑ ያክል ስምምነቱ እንቅፋት ይገጥመዋል የሚለዉ ስጋት እያየለ፣ የገቢራዊነቱ ሒደት  ከተፈራራሚዎች ፍላጎትና አቅም ዉጪ ሊጨናጎል ይችላል የሚለዉ ግምት እየጠነከረ፣ የኃያላን ዛቻም እየተደጋጋመ ነዉ።ለስምምነቱ የሚንቆረቆረዉ ድጋፍ፣አድናቆትና ቃልን፣ስምምነቱን አቃርጠዉ ከያዙት ተስፋና ቀቢፀ ተስፋ  ጋር አሰባጥረን እንቃኛለን።ላፍታ  አብራችሁን ቆዩ።
 ጠቅይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ-ማክሰኞ፤«እኛ አንድ ርምጃ ሔደናል።ተወያይተናል፣ ተስማምተናል ፈርመናል።ቀጥሎ የሚጠበቅብን የገባነዉን ቃል በታማኝነት በመፈፀም ሰላሙን ጠላቂ ማድረግ ነዉ»
ስምምነቱ፣ ለገቢራዊነቱ የተገባዉ ቃልም በትንሹም ቢሆን ገቢር ሆነ።ጠቅላይ ሚንስትሩ አዲስ አበባ ላይ ለምክር ቤት እንደራሴዎች ማብራሪያ ሲሰጡ የርዳታ መድሐኒትና የሕክምና ቁሳቁስ የጫኑ መኪኖች  መቀሌ መግባታቸዉን የዓለም ቀይ መስቀል ኮሚቴ አስታወቀ።በማግስቱ ሮብ  የዓለም ምግብ ድርጅት (WFP) የላከዉ የርዳታ እሕል ትግራይ ገባ።የድርጅቱ የበላይ ኃላፊ ዴቪድ ባስሌይ በትዊተር የርዳታ እሕል ትግራይ መግባቱን አቀደነቁ ግን አሳሰቡም።«የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ ወዲሕ ይሕ የመጀመሪያዉ እንቅስሴ ነዉ---ጥሩዉ ጅምር መጠናከር አለበት።ሁሉም ወገኖች ስምምነቱን ማክበር አለባቸዉ።»እያሉ ቀጠሉ።የጠቅላይ ሚንሥትር ዐቢይ አህመድ የምክር ቤት ማብራሪያ
ለስምምነቱ ገቢራዊነት የሚገባዉ ቃልም ቀጠለ።የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ዋና ተደራዳሪ ጌታቸዉ ረዳ-ትናንት ዕሁድ።«የሰላም ዕድሉ ሙሉ ለሙሉ እንዲያድግ ፣ ወደ ተሻለ ደረጃ እንዲደርስ ሁላችንም በተቻለን ሁሉ መንቀሳቀስ አለብን።``»
ድጋፍ አድናቆቱም አላባራም።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የቀድሞ ዲፕሎማትና የሕግ ባለሙያ ባይሳ ዋቅ ወያ ባለፈዉ ሳምንት።«እኔ ገና ተደራድረዉ አጀንዳ ወስደዉ ለድርድሩ ይዘጋጃሉ ብለን ስንል ተስማምተናል ብለዉ መግለጫ አወጡ፣እጅግ በጣም አስደሳች ነዉ»
                               
የቀድሞ ፖለቲከኛና የፖለቲካ ተንታኝ ያሬድ ጥበቡ ትናንት-ዕሁድ።«እጅግ እጅግ በጣም ተደስቻለሁ።አልጠበቅሁም፤ በዚሕ ስፋትና ጥልቀት መግባባት ላይ በዚሕ አጭር ጊዜ ዉስጥ ይደርሳሉ ብዬ፣ እዚያ መግባባት ላይ በመድረሳቸዉ በጣም ደስ ብሎኛል።»
ደስታ ያጫረዉ፣ ድጋፍ፣ አድናቆት የሚንቆረቆርለት የሰላም ስምምነት ሙሉ ገቢራዊነቱ ጥርጣሬ፣ሥጋት እንቅፋትም ተጋርጦበታል።የዓለም ምግብ ድርጅት የበላይ ኃላፊ ዴቪድ ቤስሌይ «ሁሉም ወገኖች» ሲሉ ስምምነቱን ከፈረሙት ዉጪ ያሉ ግን አስከፊ ጥፋት፣ ዘግናኝ የሰብዊ መብት ጥሰት በተፈፀመበት ጦርነት የተካፈሉትን ወገኖች በሙሉ ማለታቸዉ መሆኑ አያጠራርም።
የቤስሌይም ሆነ የሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና መንግስታት ባለስልጣናት ማሳሰቢያ፣ስጋትና ጥርጥርጣሬ ምንጮች በሰላም ስምምነቱ ተፈራራሚዎች መካከል ካለዉ አለመተማመን እኩል በናይሮቢዉ ስምምነት «የዉጪ ኃይል» ተብሎ የተጠቀሰዉ የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ ግዛት መልቅ-አለመልቀቁ አንዱ ነዉ።
ስምምነቱን «እጅግ አስደሳች» ያሉት የፖለቲካ ተንታኝ ያሬድ ጥበቡም ኤርትራ ጦሯን ፈቀድና ፈጥና ከኢትዮጵያ ማስወጣትዋን ይጠራጠራሉ።ለጥርጣሬያቸዉ መሰረት የኤርትራን መንግስትን መርህ፣የመሪዎቹን ያለፈ ድርጊትና ያሁን ፍላጎትን ይጠቅሳሉ።
«---ኤርትራ በኢትዮጵያ ዉስጥ እጇን ለማስገባት ያላት ፍላጎት፣የኤርትራ የኤኮኖሚ ሁኔታ፣ የኢትዮጵያን ኤኮኖሚ ለመጠቀም፣ ከዚሕ በፊትም ከ20 ዓመት በፊትም ወደ ጦርነት የገባነዉ---»
የህወሓት ዋና ተደራዳሪ ጌታቸዉ ረዳ ትናንት ለትግራይ ክልል ጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ከታዛቢ፣ተንታኞቹ ስጋትና ጥርጣሬም አልፈዉ የኤርትራ ጦር አሁንም የትግራይ ሰላማዊ ሕዝብን እያሰቃየ ነዉ ብለዋል።የኢትዮጵያ የሰላም ስምምነት ገቢራዊነቱ
«የኤርትራ ጦር በሚንቀሳቀስባቸዉ አካባቢዎች የሕዝባችን ስቃይ አልቆመም።የተፈናቀለዉ ህዝብ ወደቀየዉ አልተመለሰም።»
በስምምነቱ መሰረት የህወሓት ተዋጊዎች ትጥቅ መፍታት ያለባቸዉ ካለፈዉ ሳምንት ማክሰኞች ጀምሮ ነዉ።ከባድ የጦር መሳሪያዎችን ለኢትዮጵያ ፌደራዊ መንግስት የመከላከያ ሠራዊት የሚያስረክቡት ደግሞ የዉጪ ኃይል የተባለዉ የኤርትራ ጦርና ከፈደራሉ መንግስት ሠራዊት ዉጪ ያሉ ተዋጊዎች የትግራይ ክልልን ለቅቀዉ ሲዉጡ ነዉ።
የህወሓት ታጣቂዎች ትጥቅ መፍታት ሰለመጀመር አለመጀመራቸዉ እስካሁን በግልፅ የሚታወቅ ነገር የለም።ከባድ መሳሪያ የማስረከቡ ጉዳይ ግን ስምምነቱ «ከትግራይ መዉጣት አለባቸዉ» ያላቸዉ ኃይላት ሳይወጡ ይጀመራል ብሎ መጠበቅ ጅልነት ነዉ።አቶ ጌታቸዉ እንዳሉት ደግሞ የትግራይ ሕዝብ የደሕንነት ዋስትና ሳያገኝ «ትጥቅ መፍታት» ብሎ ነገር የለም።
«ትጥቅ የማውረድ ሐሳብ ዝም ብሎ ጠብመንጃ የማራገፍ ብቻ ተደርጎ መወሰድ የለበትም። የትግራይ ሕዝብ ደሕንነትን በማያረጋግጥ መንገድ የሚፈጸም ነገር እኔ ብፈልግ እንኳ፣  እኔ ብቀበለው፣ ጻድቃን ቢቀበለው እንኳን የትኛው ሰው ነው ሕይወቱ አደጋ ውስጥ እያለ፣ የሕዝቡ ደሕንነት አደጋ ውስጥ ወድቆ እያለ ትጥቁን የሚያስረክበው? ይህ ግልጽ መሆን አለበት። 
የኤርትራ ሰራዊት ሕዝባችን በሚያርድበት፣ ሁሉም ዓይነት የአካባቢ ሚሊሻና ታጣቂ እየመጣ እየመጣ ሕዝባችን ላይ ግፍ በሚፈጽምበት ሁኔታ፣ ንብረቱን በሚያወድምበት ሁኔታ፣ ጻታዊ ዓመጽ በሚያደርግበት ሁኔታ ምን አምነን ነው ትጥቃችንን የምናራግፈው የሚል ጥያቄ ማንሳት ባሕሪያዊ ብቻ ሳይሆን የሆነ ጤናማ አእምሮ ያለው ሰው ዋስትና ሳያረጋግጥ ትጥቅ የማራገፍ ሐሳብ ሊኖረው አይችልም።» የመቐለ ድባብ በስምምነቱ ማግስት

የቀይ መስቀል ርዳታ የጫነ ካሚዮን
የቀይ መስቀል ርዳታ የጫነ ካሚዮንምስል ICRC
የፕሪቶሪያዉ ስምምነት
የፕሪቶሪያዉ ስምምነትምስል SIPHIWE SIBEKO/REUTERS

ሁለቱ ወገኖች እንዲስማሙ ከፍተኛ ጥረት፣ግፊትና ጫና ያደጉት የዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣናትም ኤርትራ ጦርዋን ከኢትዮጵያ አለማስወጣትዋ ስምምነቱን ሊያደናቅፈዉ እንደሚችል እያስጠነቀቁ ነዉ።የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ከፍተኛ ባለስልጣን ከሚል ማዕረጋቸዉ ዉጪ ስማቸዉ እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ ባለስልጣን ባለፈዉ ሳምንት እንዳሉት አስመራ ስምምነቱን ካደናቀፈች ዩናይትድ ስቴትስ ኤርትራን በተጨማሪ ማዕቀብ ለመቅጣት አታመነታም።
የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር  የአፍሪቃ ጉዳይ ረዳት ሚንስትር ወይዘሮ ሞሌይ ፌሊም ኤርትራ ስምምነቱን ካወከች መንግስታቸዉ ኤርትራ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ትጥላለች።የፖለቲካ ተንታኝ ያሬድ ጥበቡ ግን ዩናይትድ ስቴትስም ሆነች ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ኤርትራን መቅጣት የሚችለዉ ኤርትራ ጦርዋን ከኢትዮጵያ እንድታስወጣ የኢትዮጵያ መንግስት በይፋ ጠይቆ የኤርትራ መንግስት እንቢተኝነት ሲረጋገጥ ነዉ።
«አስገዳጅ ሁኔታ መፍጠር የሚቻለዉ የኢትዮጵያ መንግስት በፊት ለፊት የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ ግዛቶች እንዲወጣ መግለጫ ካወጣ ብቻ ነዉ የሚመስለኝ---»                                                       
የአሜሪካኖች የማዕቀብ ዛቻ ኤርትራን ማስገደዱን አቶ ያሬድ ይጠራጠራሉ።ማዕቀቡን የኤርትራ ባለስልጣናት «ያደጉበት ነዉ» -እንደ አቶ ያሬድ
                                                
ከኤርትራ በኩል እስካሁን በይፋ የተባለ ነገር የለም።የኢትዮጵያ መንግስትም ኤርትራ ጦሯን እንድታስወጣ ስለመጠየቅ አለመጠየቁ በግልፅ የሚታወቅ ነገር የለም።ስምምነቱ የተጋረጠበትን እንቅፋት አልፎ  ሙሉ በሙሉ  ገቢር መሆን አለመሆኑም በጊዜ ሒደት የሚታይ ነዉ።

የዓለም ቀይ መስቀል ኮሚቴ አዉሮፕላን ሽሬ
የዓለም ቀይ መስቀል ኮሚቴ አዉሮፕላን ሽሬምስል Solomon Muchie/DW

ነጋሽ መሐመድ