1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሩሲያ ፕሬዝደንት የአገራቸው የኑክሌር ኃይሎች "በተጠንቀቅ" እንዲጠባበቁ ትዕዛዝ ሰጡ

እሑድ፣ የካቲት 20 2014

የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን የአገራቸው የኑክሌር ኃይሎች "በተጠንቀቅ" እንዲጠባበቁ ትዕዛዝ ሰጡ። የኔቶ ዋና ጸሐፊ የንስ ስቶልተንበርግ ትዕዛዙን "ኃላፊነት የጎደለው" ብለውታል። የፑቲን ትዕዛዝ የተደመጠው የዩክሬን እና የሩሲያ ባለሥልጣናት ከቤላሩስ ድንበር ተገናኝተው ሊነጋገሩ መሆኑን ፕሬዝደንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ ካስታወቁ በኋላ ነው

https://p.dw.com/p/47gQA
Russland | Treffen Putins mit Militärvertretern | Sergej Schoigu & Valery Gerasimov
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌይ ሾይጉ እና የጦሩ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ቫለሪ ጌራሲሞቭ ከፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በስብሰባ ላይ ምስል Alexei Nikolsky/imago images/ITAR-TASS

የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን የአገራቸው የኑክሌር ኃይሎች "በተጠንቀቅ" እንዲጠባበቁ ትዕዛዝ ሰጡ። ፕሬዝደንቱ ትዕዛዙን የሰጡት "የኔቶ አገራት ከፍተኛ መሪዎች" ያወጧቸዋል ባሏቸው "ጠበኛ መግለጫዎች" ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል።

የሩሲያ የመከላከያ ምኒስትር ሰርጌይ ሾይጉን ጨምሮ ከአገራቸው ከፍተኛ ወታደራዊ ሹማምንት ጋር ሲነጋገሩ ቭላድሚር ፑቲን ምዕራባውያን አገሮች በሩሲያ ላይ "የወዳጅ ያልሆነ እርምጃ" ወስደዋል፤ "ኢፍትሐዊ ማዕቀብ ጥለዋል" ብለዋል።

በዚህም "የመከላከያ ሚኒስትሩ እና የጦሩ ጠቅላይ አዛዥ የሩሲያ ጦር የመከላከያ ኃይሎችን በልዩ ተጠንቀቅ እንዲጠባበቁ" እንዲያደርጉ ማዘዛቸውን ገልጸዋል።

Russland | Treffen Putins mit Militärvertretern | Sergej Schoigu & Valery Gerasimov
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌይ ሾይጉ እና የጦሩ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ቫለሪ ጌራሲሞቭ ከፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በስብሰባ ላይ ምስል Sputnik/Aleksey Nikolskyi/Kremlin via REUTERS

የኔቶ ዋና ጸሐፊ የንስ ስቶልተንበርግ የፑቲንን ትዕዛዝ "ኃላፊነት የጎደለው" ብለውታል። "ዋና ጸሐፊው ይኸ አደገኛ ንግግር ነው። ይኸ ኃላፊነት የጎደለው ነው" ሲሉ ለአሜሪካው ሲኤንኤን ቴሌቭዥን ጣቢያ ተናግረዋል።

የፑቲን ትዕዛዝ ሩሲያ የኑክሌር ጦር መሳሪያዎቿ ለጥቃት ዝግጁ እንዲሆኑ መፈለጓን ያሳያል ሲል አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል። የሩሲያ የዩክሬን ወረራ እና የምዕራባውያኑ ምላሽ ወደ ኑክሌር ጦርነት ሊያድግ ይችላል የሚል ሥጋት አጭሯል።

የአሜሪካው ዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ ጄን ፕሳኪ ፕሬዝደንት ፑቲን ዩክሬንን ሲወሩ እንዳደረጉት ሁሉ "የሌለ ሥጋት በመፍጠር ለተጨማሪ እርምጃ ማመካኛ እያበጁ ነው" ሲሉ ከሰዋል። ቃል አቀባይቱ ለአሜሪካው ኤቢሲ ቴሌቭዥን ጣቢያ ሲናገሩ "ሩሲያ ከኔቶም ሆነ ከዩክሬን ሥጋት አልነበረባትም" ብለዋል።

የፑቲን ትዕዛዝ የተደመጠው የዩክሬን እና የሩሲያ ባለሥልጣናት ከቤላሩስ ድንበር ተገናኝተው ሊነጋገሩ መሆኑን የፕሬዝደንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ ጽህፈት ቤት ካስታወቀ በኋላ ነው። ሩሲያ በዩክሬን ወረራ ከጀመረች ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ይደረጋል የተባለው ንግግር ያለ ምንም ቅድመ-ሁኔታ እንደሚካሔድ የገለጹት ፕሬዝደንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ ከቤላሩስ አቻቸው ያደረጉት የስልክ ውይይት ውጤት መሆኑን ዛሬ እሁድ ባወጡት መግለጫ ጠቁመዋል።

Der ukrainische Präsident Selenskyj gibt in Kiew eine Erklärung ab
የዩክሬን እና የሩሲያ ባለሥልጣናት ከቤላሩስ ድንበር ተገናኝተው ሊነጋገሩ መሆኑን የፕሬዝደንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።ምስል Ukrainian Presidential Press Service/REUTERS

የዩክሬን ፕሬዝደንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ እና የቤላሩስ ፕሬዝደንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ በስልክ የተነጋገሩት ዛሬ እሁድ ነው።ዜሌንስኪ ያወጡት መግለጫ "የዩክሬን ልዑካን ከሩሲያ ልዑካን ጋር በዩክሬን እና ቤላሩስ ድንበር ከፕሪፕያት ወንዝ አቅራቢያ ያለ ቅድመ ሁኔታ እንደሚገናኙ ተስማምተናል" ብሏል።

ቀደም ሲል የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ናፍታሊ ቤኔት በዩክሬን የተቀሰቀሰውን ውጊያ ለማስቆም ሁለቱን ወገኖች ለማደራደር ለሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ግብዣ ማቅረባቸውን ክሬምሊን አስታውቋል። ቤኔት ከፑቲን ከተነጋገሩ በኋላ አንድ የእስራኤል ባለሥልጣን የማደራደሩን ግብዣ በተመለከተ አሜሪካ መረጃ እንደተሰጣት ተናግረዋል። የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ከዩክሬን ፕሬዝደንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ ጋር ባለፈው አርብ ተነጋግረው ነበር። ስማቸው ያልተገለጸው ባለሥልጣን "ፑቲን ለእስራኤል ግብዣ ክፍት ነበሩ" ሲሉ ለሬውተርስ ተናግረዋል።

አራተኛ ቀኑን ባስቆጠረው ውጊያ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ለደሕንነታቸው በመስጋት ለስደት ሲዳረጉ በአውሮፓ አገሮች የሚኖሩ ዩክሬናውያን ለአገራቸው ለመዋጋት መመለስ መጀመራቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል።