*የ2017 አዲስ ዓመት መለወጫ ርእሰ አውደ ዓመት ዛሬ በኢትዮጵያውያን እየተከበረ ነው ። በሀገር ቤት ውስጥ እና አሜሪካን ጨምሮ በተለያዩ የውጭ ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በዓሉን የተቸገሩን በማሰብ እና በመርዳት ጭምር አክብረዋል ።
*በምስራቅ አፍሪቃ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ማይክ ሃመር ዛሬ በኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚደንት ጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ ጋ ፊት ለፊት ተነጋገሩ ።
*የአማራ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት በክልሉ ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ 1430 እስረኞች በይቅርታ እንዲፈቱ መወሰኑን የክልሉ ፍትሕ ጽ/ቤት ዐሳወቀ ።
ዜናው በዝርዝር
አአ፥ የ2017 አዲስ ዓመት በኢትዮጵያውያን እየተከበረ ነው
የ2017 አዲስ ዓመት መለወጫ ርእሰ አውደ ዓመት ዛሬ በኢትዮጵያውያን እየተከበረ ነው ። በሀገር ቤት ውስጥ እና አሜሪካን ጨምሮ በተለያዩ የውጭ ሃገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በዓሉን የተቸገሩን በማሰብ እና በመርዳት ጭምር አክብረዋል ። በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ተፈናቃዮች ግን ለበዓሉ ምንም የተለየ ነገር አለማግኘታቸውን ገልጠዋል ። አዲሱ ዓመት በጾምና በሥራ ቀን በመዋሉ በአብዛኛው በአሉ በተለይ የሚከበረው ከነገ ጀምሮ በተለይም ቅዳሜና እሁድ መሆኑ ተገልጿል ። ከዋዜማው ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ በሚገኘው የዘመን መለወጫ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰላምን እንዲሰፍን በርካቶች ምኞታቸውን አንጸባርቀዋል ።
A በምስራቅ አፍሪቃ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ማይክ ሃመር ዛሬ በኢትዮጵያ አዲስ ዓመት ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚደንት ጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ ጋር ፊት ለፊት ተነጋገሩ ። በትግራይ ክልል ዘላቂ ሰላም ለማስፈንም የፕሪቶሪያ ስምምነት ሙሉ ለሙሉ በአፋጣኝ የመተግበሩ እጅግ አስፈላጊነት ላይ ሁለቱ መስማማታቸውን የአሜሪካ ኤምባሲ ገልጧል ። ሁሉም ኢትዮጵያውያን በሰላም መኖር ይገባቸዋል ከሚለው የኤምባሲው አጠር ያለ የፌስቡክ መልእክት ጋር ማይክ ሐመር እና ጄኔራል ጻድቃን ጎን ለጎን ቆመው የሚታዩበት ፎቶም ይታያል ። ማይክ ሃመር እስከ ፊታችን ቅዳሜ በአዲስ አበባ እንደሚቆዩ ተገልጧል ። ልዩ ልዑኩ በኢትዮጵያ ቆይታቸዉ፦ ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋርም እንደሚወያዩ ተጠቅሷል ። አምባሳደሩ በቆይታቸው በአማራ ክልል የሚካሄደዉን ጦርነት ብሎም በኦሮሚያ ክልል የሚታየዉን አመጽ በዉይይት ለማስቆም ጥረት ያደርጋሉ ተብሏል ። በሌላ በኩል፤ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርእሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ ከልዑካናታቸው ጋር አዲስ አበባ እንደሚገቡም ቀደም ሲል ተዘግቧል ።
ባሕር ዳር፥ በሺህዎች ለሚቆጠሩ እስረኞች ምሕረት
የአማራ ክልል መስተዳድር ምክር ቤት በክልሉ ማረሚያ ቤቶች የሚገኙ 1430 እስረኞች በይቅርታ እንዲፈቱ መወሰኑን የክልሉ ፍትሕ ጽ/ቤት ዐሳውቋል ። የክልሉ መንግስት በወሰነው መሰረት 1389 ወንዶችና 41 ሴቶች ከዛሬ መስከረም 1 ቀን፣ 2017 ዓ ም ጀምሮ ይቅርታ ተደርጎላቸዋል ተብሏል ። ይህንንም የጽ/ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ ወንዳቸው ሠራው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ገልጠዋል ።
«በ2017 ዓመት የአንደኛ ዙር የይቅርታ ምክንያት በማድረግ በክልሉ የይቅርታ መስፈርት አዋጅ 136/1998 እና ይህን ለማስፈጸም በወጣው መመሪያ ቁጥር 30/2010 መሠረት ለወንድ 1389፣ ለሴት 41 በድምር ለ1430 በክልሉ ማረሚያ ቤት ለሚገኙ ታራሚዎች ከመስከረም 1 ቀን ጀምሮ ከእስር እንዲለቀቁ ተወስኗል ።»
የይቅርታው ተጠቃሚዎች በሕግ ይቅርታ የማይከለክላቸው፣ የተፀፀቱ፣ ዝቅተኛውን የእስራት ጊዜ ያጠናቀቁ እና እረቅ የፈጠሙ መሆናቸውንም ኃላፊው ተናግረዋል ። የአማራ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ኮማንደር ዓባይ በላይ ይቅreታ የተደረገላቸው ታራሚዎች ከባህር ዳር ከሌሎች ማረሚያ ቤቶች ዛሬ ከጠዋት ጀምሮ እየወጡ ስለመሆናቸውም ተናግረዋል ሲል ዓለምነው መኮንን ዘግቧል ። በተያያዘ ዜና፦ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት «በክህደት ወንጀል» የጥፈተኝነት ብያኔ ተላልፎባቸው በእስር ላይ የነበሩ 178 የትግራይ ክልል ተወላጅ ወታደሮች በይቅርታ መለቀቃቸውን ትናንት ዐሳውቆ ነበር ።
ናይሮቢ፥ አድማ የመቱ የናይሮቢ አየር መንገድ ሠራተኞች ወደ ሥራ ገበታቸው ለመመለስ ተስማሙ
በኬንያ መዲና ናይሮቢ የሚገኘዉ ጆሞ ኬንያታ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ዛሬ አድማ የመቱ ሠራተኞች ወደ ሥራ ገበታቸው ለመመለስ ተስማሙ ። ይህንንም የኬንያ የሠራተኞች ማኅበር ማሳወቁን ሮይተርስ ዘግቧል ። ሠራተኞቹ ዛሬ በመቱት የሥራ ማቆም አድማ ወደ ኬንያ መዲና የሚደረጉ በረራዎችን አስተጓጉሏል ። የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ የተለያዩ አየር መንገዶች መነሻና መዳረሻቸውን ናይሮቢ ያደረጉ በረራዎች በጊዜያዊነት ማቋረጣቸውን ቀደም ሲል ገልጠዋል ። ሠራተኞቹ አድማዉን የመቱት የኬንያ መንግሥት ከማእድን ነጋዴው የህንዱ አዳኒ ኩባንያ ጋር ያቀደውን ስምምነት በመቃወም ነዉ ። ስምምነቱ የጆሞ ኬንያታ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን ማደስና አዲስ መተላለፊያና ማረፊያ መገንባትne ያካትታል ። በስምምነቱ መሠረት አዳኒ የተባለዉ የህንዱ ኩባንያ የኬንያ ዋና የአውሮፕላን ማረፊያን ለ30 ዓመታት ያስተዳድራልም ተብሏል ። አድማዉን የመቱት የጆሞ ኬንያታ አዉሮፕላን ማረፍያ ሠራተኞች ስምምነቱ ከሥራ መባረርን ያስከትላል የሥራ ሁኔታዉንም የከፋ ያደርጋል ሲሉ ስጋታቸዉን ገልጠዋል ።
ፊላዴልፊያ፥ የዩናይትድ ስቴትስ ኡጩ ፕሬዚደንቶች በቴሌቪዥን ተከራከሩ
የዩናይትድ ስቴትስ ሁለቱ የዘንድሮ እጩ ፕሬዚደንት ተፎካካሪዎች ፊላዴልፊያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት በአካል ተገኝተው በቴሌቭዥን ተከራከሩ ። የዴሞክራቶቹ ተወካይ ምክትል ፕሬዚደንት ካማላ ሐሪስ እና ሪፐብሊካኑ የቀድሞው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ለ90 ደቂቃ ብርቱ ክርክር አድርገዋል ። በውርጃ፤ በኤኮኖሚ፤ በፍልሰተኞች እና በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ በብርቱ ተሟግተዋል ። ካማላ ሐሪስ በማክሰኞው ምሽት ክርክር ተፎካካሪያቸው ዶናልድ ትራምፕ ተከላካይ እንዲሆኑ ማስገደዳቸውን ተንታኞች ገልጠዋል ። ከክርክሩ በኋላ መራጮች የተለያዩ አመለካከቶቻቸውን አንጸባርቀዋል ። ስማቸው ያልተጠቀሰ አንድ የሪፐብሊካን ደጋፊ የዶናልድ ትራምፕ አሸናፊነትን እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
«በዚህ ምርጫ ፕሬዚደናት ዶናልድ ትራምፕን ነው የምደግፈው ። ምክንያቱም በ2016 ያመጡልን እና ለአራት ዓመታት ያደረጉልን ራሱ እንዲደገም እንሻለን ። ጠንካራ ኤኮኖሚ ያስፈልገናል ። ለዓለም ሰላም፥ ለእያንዳንዱ ሰውም ብልጽግና ያሻናል ። »
የምርጫ ክርክሩን በቴሌቪዥን ያደመጡ የዴሞክራቶች ደጋፊ በበኩላቸው የካማላ ሐሪስ ወደፊት በፕሬዚደንትነት መመረጥ ትርጉሙ ላቅ ያለ እንደሆነ ገልጠዋል።
«የእሳቸው መታጨት እና ፕሬዚደንት መሆን ለአጠቃላዩ ትውልድ በሚገርም ሁኔታ አነቃቂ ይሆናል ። በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ መረጋጋትን ብሎም ለፖለቲካው ስክነት አምጥተዋል ።»
ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ዛሬ ማለዳ ከፎክስ ቴሌቪዥን ጋ ባደረጉት ቃለመጠይቅ በኤቢሲ (ABC)ቴሌቪዥን ምሽቱን የተላለፈው ክርክር እሳቸውን የተጫነ እና ለተፎካካሪያቸው ያደላ መሆኑን በመግለጥ አማreረዋል ። እሳቸው ሲናገሩ በጋዜጠኞቹ እርምት ሲሰጥ እንደነበር፤ ተፎካካሪያቸው ግን ችላ ተብለው እንደታለፉም በመግለጥ ወቅሰዋል ። ክርክሩን የታደሙ በርካቶች እንደሚሉት የሕግ አዋቂዋ ካማላ ሐሪስ ፖሊሲዎች ላይ ሲያተኩሩ ዶናልድ ትራምፕ አብዛኛውን ጊዜ በወቀሳ እና ያለፉ ጉዳዮችን በማንሳት ማማረራቸውን ጠቅሰዋል ። ክርክሩ ስምንት ሳምንት ግድም በቀረው የዩናይትድ ስቴትስ የፕሬዚደንት ምርጫ በተለይ ባልወሰኑ መራጮች ላይ ተጽእኖ እንደሚኖረው ተገልጧል ።
ሐኖይ፥ ቬትናም ውስጥ አውሎ ንፋስ በርካቶችን ገደለ
ቬትናም ውስጥ «ያጊ» የሚል ስያሜ የተሰጠው ብርቱ አውሎ ነፋስ ካለፈ በኋላ የሞቱ እና የጠፉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው ። የሀገሪቱ የአደጋ መቆጣጠሪያ እንዳለው ከሆነ በአውሎ ንፋሱ ጥፋት ቢያንስ 143 ሰዎች ሞተዋል ። 58 ሰዎች ደግሞ አሁንም ያሉበት ዐይታወቅም ። በዐሥርተ ዓመታት ውስጥ እጅግ በጣም ኃይለኛ የተባለለት ሞቃታማው አውሎ ንፋስ በሳምንቱ መጨረሻ በተለይም በደቡብ ምስራቅ እስያ ሰሜናዊ ክፍል ተቀስቅሷል ። አውሎ ንፋሱ ባደረሰው አደጋ ከ800 በላይ ሰዎች ቆስለዋል ። እንደ ሀገር ውስጥ የአደጋ መቆጣጠሪያ ጥበቃ ከሆነ፦ አውንፋሱ ከ100,000 በላይ ቤቶችን አውድሟል ። በርካቶች በውኃ ተከበው ይገኛሉ ። ብርቱው ዝናብ በቀጠለ ቁጥር ከ20 ዓመታት ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የወንዞች ሙሌት መጠንም እየጨመረ ነው ። በቀይ ወንዝ ሙሌት የተነሳም ዋና ከተማዋ ሐኖይ ውስጥ ያሉ ነዋሪዎች ለደኅንነታቸው ሲባል ወደ ሌሎች አጎራባች ቦታዎች ተወስደዋል ።