1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የምዕራብ ወለጋ ተፈናቃዮች ተማጽኖ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 9 2015

ከተለያዩ ስፍራዎች ተፈናቅለው በምዕራብ ወለጋ ዞን መንዲ ከተማ የሚገኙ ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ ለአራት ወራት ያህል ባለማግኘታቸው ለችግር መጋለጣቸውን ተናገሩ፡፡ ለተፈናቀሉ ዜጎች ከሶስት ወራት በፊት የቀረበው ድጋፍ ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ መዳረሱን ገልጸዋል፡፡ በየወሩ ሰብአዊ ድጋፍ ይመጣል ቢባልም ለወራት ድጋፍ እንደላገኙ ጠቁሟል፡

https://p.dw.com/p/4VCse
የመንዲ ከተማ ከፊል ገጽታ፦ ፎቶ ከማኅደር
ከተለያዩ ስፍራዎች ተፈናቅለው በምዕራብ ወለጋ ዞን መንዲ ከተማ የሚገኙ ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ ለአራት ወራት ያህል ባለማግኘታቸው ለችግር መጋለጣቸውን ተናገሩ፡፡ ፎቶ ከማኅደርምስል Negassa Deslagen/DW

ዜጎች ለወራት በቂ ድጋፍ አለማግኘታቸውን ተፈናቃዮች ተናግረዋል

ከተለያዩ ስፍራዎች ተፈናቅለው በምዕራብ ወለጋ ዞን መንዲ ከተማ የሚገኙ ዜጎች ሰብአዊ ድጋፍ ለአራት ወራት ያህል ባለማግኘታቸው ለችግር መጋለጣቸውን ተናገሩ፡፡ ለተፈናቀሉ ዜጎች ከሶስት ወራት በፊት የቀረበው ድጋፍ ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ መዳረሱን ገልጸዋል፡፡ በየወሩ ሰብአዊ ድጋፍ ይመጣል ቢባልም ለወራት ድጋፍ እንደላገኙ ጠቁሟል፡፡ የምዕራብ ወለጋ ዞን አደጋ ስጋት ስራ አመራር ወይም ቡሳ ጎኖፋ ጽ/ቤት በተለያዩ ምክንያት ሰብአዊ ድጋፍ ዘግተው እንደነበር ገልጸው በቅርቡ ወደ መንዲ፣ቅልጡ ካራ የተባለ ወረዳ እና ነጆ ለሚገኙ ተፈናቃዩች ድጋፍ መላኩን አመልክተዋል፡፡  

በምዕራብ ወለጋ ዞን የተለያዩ ስፍራዎች በልዩ ልዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉከ100ሺ በላይ ዜጎችእንደሚገኙ የዞኑ አደጋ ስጋት ስራ አመራር/ ቡሳ ጎኖፋ ጽ/ቤት አመልክተዋል፡፡ የተፈናቀሉ ሰዎች በዞኑ ሌታ ስቡ ወረዳ፣ ነጆ፣ መንዲ ከተማና ሌሎች ቦታዎች እንደሚገኙ ተገልጸዋል፡፡ በ2013 ዓ.ም ከምዕራብ ወለጋ ዞን እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አዋሳኝ ከሆነችው ሴዳል የሚትባል የካማሺ ዞን ወረዳ  መፈናቀላቸውን የነገሩን አንድ ስመ አይገለጽ ያሉ ነዋሪ በሰብአዊ ድጋፍ እጥረት ምክንየት ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን ተናግረዋል፡፡ አልፎ አልፎ ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚላከው ሰብአዊ ድጋፍ ለሁሉም በበቂ በሆነ መልኩ ተደራሽ እየሆነ አይደለም ብሏል፡፡ ቀድሞ ከነበሩበት ወረዳ የነበራቸው ቤት መውደሙን ገልጸው ወደ ቀድሞ ቀያአቸው ለመመለስ በስፍራው የጸጥታ ስጋት መኖሩን ተናግረዋል፡፡  

በኦሮሚያ ክልል የነቀምት ከተማ፤ ፎቶ ከማኅደር
ከመንዲ አቅራቢያ እና ከአጎራባች ቤኒሻንጉል ጉሙዝ አዋሳኝ ስፍራዎች የተፈናቀሉ ከ7ሺ የሚደርሱ ሰዎች በከተማዋ እንደሚገኙ የዞኑ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ሮ መረጃ ያመለክታል፡፡ በኦሮሚያ ክልል የነቀምት ከተማ፤ ፎቶ ከማኅደር

በመንዲ ከተማ መኖር ከጀመሩ ሁለት ዓመታትን እንዳስቆጠሩ የነገሩን አቶ ቶለራ ኩመራ በከተማዋ ከ2ሺ በላይ የተፈናቀሉ አባወራዎች እንደሚገኙ አብራርተዋል፡፡ ለተፈናቀሉ ዜጎች  ከሶስት ወራት በፊት የእህልና የገንዘብ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል፡፡ ሆኖም የመጣው ድጋፍ ለሁሉም የተፈናቀሉ ኅበረተሰብ ከፍሎች አለመዳረሱን አክለዋል፡፡ የሰብአዊ ድጋፍ ለወራት መቋረጥ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የኅብሰረተሰብ ክፍሎች ላይ አሉታዊ ተጽህኖ ማሳደሩን ተናግረዋል፡፡   

የምዕራብ ወለጋ ዞን የአደጋ ስጋት ስራ አመራር/ቡሳ ጎኖፋ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ነጻነት አለማየሁ ሰብአዊ ድጋፍ በተሽከርካሪ እጥረትና ጸጥታ ችግር ሳቢያ ለተወሰነ ጊዜ ዘግይቶ እንደነበር አስረድተዋል፡፡ ከነሐሴ ወር መጀመረያ አንስቶ ለሁሉም አካባቢዎች ሰብአዊ ድጋፍ መላኩን ተናግረዋል፡፡ ሴቭ ዘ ችልድረን የተባለ የግል ተቋም በመንዲ ለሚገኙ የተፈናቀሉ ዜጎች የተለያዩ ድጋፎች ለማድረግ በስፋራው እንደሚገኝም አክለዋል፡፡ 

‹‹ እንደተባለው ድጋፍ ዘግቶ ነበር፡፡ ከዚህ ወር መጀመሪያ አንስቶ ድጋፍ  ተልኮላቸዋል፡፡ ተፈናቃዮቹ በመንዲ ከተማ ውስጥ ስለሚገኙ በቅርቡ ከመንግስትም በተጨማሪ ሰቪ. ዘ.ችልዲረን ወደ ስፍራው ተልዕኮ የተለያዩ ድጋፎችን ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡ ከዚህ ቀደምም ከ2000 በላይ ለሚደርሱ አባዎራዎች የገንዘብም፣ የእህልም ድጋፍ አድርገናል፡፡  ተጨማሪ ድጋፍም እንዲገባ ተደርገዋል፡፡ የሚሰጡ ድጋፎች ሰዎች የሚፈልጉት ያህል ላይሆን ይችላል» ብለዋል፡፡ 

ከመንዲ አቅራቢያ እና ከአጎራባች ቤኒሻንጉል ጉሙዝ አዋሳኝ ስፍራዎች የተፈናቀሉ ከ7ሺ የሚደርሱ ሰዎች በከተማዋ እንደሚገኙ የዞኑ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ወይም በአዲሱ የተቋሙ አጠራር "ቡሳ ጎኖፋ"  ቢሮ መረጃ ያመለክታል፡፡ በዞኑ በሰው ሰራሽ እና ተፈጥሮ አደጋዎች የተፈናቀሉ ከ100ሺ በላይ ዜጎች በአራት ወረዳዎች ማለትም በለታ ስቡ ወረዳ፣በቅልቱ ካራ ወረዳ፣በነጆ እና በመንዲ ውስጥ ይገኛሉ፡፡

ነጋሣ ደሳለኝ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሠ