1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማክሰኞ ኅዳር 03 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የዓለም ዜና

ማክሰኞ፣ ኅዳር 3 2017

*አራት የመገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎችን ጨምሮ በእነ ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ መዝገብ በሽብር ወንጀል ክስ የቀረበባቸው 51 ተከሳሾች የእምነት ክህደት ቃላቸውን ለመስጠት ለሕዳር 5 እንዲቀርቡ ቀጠሮ መስጠቱ ተገለጠ ። ​*የጋዜጠኛ ዜናነህ መኮንን ሥርዓተ-ቀብር ማክሰኞ ኅዳር 03 ቀን፣ 2017 ዓ.ም በእስራኤል ቴል አቪቭ ከተማ ያልሚና ያል ኮን በተባለ ሥፍራ ተፈጸመ ። *በቅርቡ ጥምረቱ የፈረሰበት የጀርመን መንግሥትን ለመተካት ዋነኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ሀገር አቀፍ ምርጫ ለማካሄድ ስምምነት ላይ ደረሱ ።

https://p.dw.com/p/4mw2z

አርዕስተ ዜና

*አራት የመገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎችን ጨምሮ በእነ ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ መዝገብ በሽብር ወንጀል ክስ የቀረበባቸው 51 ተከሳሾች የእምነት ክህደት ቃላቸውን ለመስጠት ለሕዳር 5 እንዲቀርቡ ቀጠሮ መስጠቱ ተገለጠ ።

​*የጋዜጠኛ ዜናነህ መኮንን ሥርዓተ-ቀብር ማክሰኞ ኅዳር 03 ቀን፣ 2017 ዓ.ም በእስራኤል ቴል አቪቭ ከተማ ያልሚና ያል ኮን በተባለ ሥፍራ ተፈጸመ ።

*በቅርቡ ጥምረቱ የፈረሰበት የጀርመን መንግሥትን ለመተካት ዋነኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ሀገር አቀፍ ምርጫ ለማካሄድ ስምምነት ላይ ደረሱ  ።

ዜናው በዝርዝር

አ.አ፥ የእነ ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ ጉዳይ ለኅዳር 5 ተቀጠረ 

የመገናኛ ብዙኃን ባለሞያዎችን ጨምሮ በእነ ዶ/ር ወንድወሰን አሰፋ መዝገብ በሽብር ወንጀል ክስ የቀረበባቸው 51 ተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃል ለመቀበል ያልተሟሉ ተከሳሾች ሊሟሉ ይገባል ተባለ ። ዛሬ ሕዳር 3 ቀን 2017 ዓ.ም በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሦስተኛ የፀረ ሽብር እና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች  የተሰየመውችሎት ከተከሳሾች መካከል አራቱ በሕመም ምክንያት ባለመቅረባቸው ተሻሽሎ በቀረበው ክስ ላይ ሁሉም ተከሳሾች የእምነት ክህደት ቃላቸውን ለመስጠት ለሕዳር 5 እንዲቀርቡ ቀጠሮ መስጠቱን ጠበቃ ሔኖክ ተናግረዋል ።

«ለፍርድ ቤቱ የተሻሻለው ክስ ከቀረበ በኋላ ተከሳሾቹ ክሱን ዐይተነዋል፤ በታዘዘው ትእዛዝ መሠረት የተፈጸመ ስለሆነ የእምነት ክህደት ቃላችንን መስጠት እንፈልጋለን ይህን ክስ በተመለከተ ብለዋል ። ፍርድ ቤቱም፦ ያልተሟሉ ተከሳሾች ስላሉ እነሱ ይሟሉ እና ቃላችሁን ትሰጣላችሁ በሚል ለኅዳር 5 ቀን፤ 2017 ዓም ተከሳሾች ተሟልተው ሲቀርቡ እያንዳንዳቸው ክሱን የሚያምኑ ከሆነ ወይንም የሚክዱ ከሆነ ያንን ለመሥራት ቀጠሮ ሰጥቶበታል ። »

በዛሬው ችሎት ሰበሩ ሰሚ ላይ የቀረበው ጉዳይ ውሳኔ ወይም መቋጫ ሳያገኝ ዐቃቤ ሕግ ክሱን ወደ 68 ገጽ የሚጠጋ አሻሽሎ ማቅረቡን ጠበቃ ሔኖክ ተናግረዋል ። በዛሬው ችሎት በማረሚያ ቤት ከሚገኙት ተከሳሾች መካከል መምህርት መስከረም አበራ፣ ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይን ጨምሮ አራት ተከሳሾች አልቀረቡም ። በዜና መጽሄት ተጨማሪ ይኖረናል ።  

ቴል አቪቭ፥የጋዜጠኛ ዜናነህ መኮንን ሥርዓተ-ቀብር ዛሬ ተፈጸመ

የጋዜጠኛ ዜናነህ መኮንን ሥርዓተ-ቀብር ዛሬ (ማክሰኞ ኅዳር 03 ቀን፣ 2017 ዓ.ም) በእስራኤል ቴል አቪቭ ከተማ ያልሚና ያል ኮን በተባለ ሥፍራ ተፈጸመ ። በሥርዓተ ቀብሩ ልጆቹ፣ ወዳጅ ዘመዶቹ እና በእስራኤል የሚኖሩ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ አባላት ተገኝተዋል ። ለረዥም ዓመታት በኖረባት እሥራኤል ኅዳር 1 ቀን፣ 2017 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ዜናነህ ከ1968 ዓ.ም ጀምሮ በጋዜጠኝነት ሲሠራ ቆይቷል ። በኢትዮጵያ ራዲዮ እና ቴሌቭዥን በዜና አንባቢነትም አገልግሏል ። ከጎርጎሮሳዊው 2013 ጀምሮ የዶይቸ ቬለ የአማርኛው ክፍል የጣቢያ መክፈቻ እና በዝግጅቶች መግቢያነት የሚጠቀምባቸው ማስተዋወቂያዎች አንባቢም ነዉ ። የዶቼ ቬለ የአማርኛው ክፍል ኃላፊ ሉድገር ሻዶምስኪ «እኔና ባልደረቦቼ ድንገት በሰማነው ኅልፈቱ ጥልቅ ሐዘን ተሰምቶናል» ብለዋል ። ዜናነህ ኑሮውን በእስራኤል ካደረገ በኋላ በተለያዩ የራዲዮ እና የቴሌቭዥን ጣቢያዎች እንዲሁም በኢንተርኔት ዝግጅቶች ያቀርብ ነበር ። በኅብር ራዲዮ ዘወትር ቅዳሜ በሚሰጠው አስተያየት በቅርበት እንደሚያውቀው የተናገረው ጋዜጠኛ ሐብታሙ አሠፋ ስለጋዜጠኛ ዜናነህ ቀጣዩን ብሏል ።

«ዜናነህ እውነት ለመናገር ተዝቆ የማያልቅ ዕውቀት ያለው ሰው ነው እጅግ በጣም፤ በአጠቃላይ አማራ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ኢትዮጵያውያን ተከብረው የሚኖሩበት ሥርዓት እንዲመጣ፥ በተለይ ደግሞ እሱ 30 ዓመት በላይ እሥራኤል ኑሯል፤ ኖርዌይ በትምህርት ኑሯል እነዚያ ልምዶች ኢትዮጵያውያንም ይኸኛው ሥርዓት፥ የአዲዙ ዘመን ሥርዓት ሰዎች በማንነታቸው ተለይተው የማይሳደዱበት፣ የማይገደሉበት፤ ሕግ እና ሥርዓት የበላይ የሚሆኑበት፤ የፖለቲካ ሥርዓቱ ዴሞክራሴያዊ መሆን ያለበት፤ ነፃ ምርጫ የሚደረግበት ሥርዓት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲመጣ በጣም ይፈልግ ነበር »

ዜናነህ ከጋዜጠኝነቱ ባሻገር «ነጻነት» እና «ከጣራው ስር» የተሰኙ ሁለት ልቦለዶች ለኅትመት አብቅቷል ። «በረከተ ራዕይ» በሚል ርእስ በድምፅ የተቀረጹ የግጥም ስብስቦችም አሉት ። ዜናነህ ባለትዳር እና የሦስት ሴቶች ልጆች አባት ነበር ።

ቤርሊን፥ ጀርመን የፈረሰውን ጥምር መንግሥት ለመተካት ምርጫ ሊካሄድ ነው 

በቅርቡ ጥምረቱ የፈረሰበት የጀርመን መንግሥትን ለመተካት ዋነኞቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ሀገር አቀፍ ምርጫ ለማካሄድ ስምምነት ላይ ደረሱ  ። ስምምነቱ እንዲደረግ የጀርመን መራኄ-መንግሥት ዖላፍ ሾልትስ ሚና መጫወታቸው ተዘግቧል ። ሀገር አቀፍ ምርጫው ከመካሄዱ በፊት ግን የሶሻል ዴሞክራቶቹ ፓርቲ መሪ መራኄ-መንግሥት ዖላፍ ሾልትስ የመተማመኛ ድምፅ እንዲሰጣቸው ታኅሣስ 7 ቀን የፌዴራል ጀርመን ታዕታይ ምክር ቤትን (Bundestag)ይጠይቃሉ ተብሏል ። በምክር ቤት የሶሻል ዴሞክራቶቹ (SPD)እና  የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት(CDU)ቡድኖች ምርጫው እሁድ፤ የካቲት 16 ቀን፤ 2017 ዓ.ም እንዲካሄድ ወስነዋል ። ይህንንም የጀርመን ዜና አገልግሎት (dpa)ከሁለቱም ፓርቲዎች ማረጋገጡን ዘግቧል ። የአረንጓዴ ፓርቲዎቹም በተቆረጠው የምርጫ ቀን ተስማምተዋል ። በምክር ቤቱ የክርስቲያን ዴሞክራት ኅብረት/ክርስቲያን ሶሻል ኅብረት  ቡድን ዳግም ሀገር አቀፍ ምርጫው ጥር 11 ቀን እንዲካሄድ ቀደም ሲል ጠይቀው ነበር ።

ባኩ፥ደጉ ሃገራት መሪዎች የአየር ንብረት ለውጥን ለመታደግ ኃላፊነታቸውን በቅጡ እንዲወጡ ተጠየቀ

የአውሮጳ ምክር ቤት ፕሬዚደንት ሻርል ሚሼል፦ ያደጉ ሃገራት መሪዎች የአየር ንብረት ለውጥን ለመታደግ ፍትኃዊ በሆነ መልኩ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳሰቡ ። ፕሬዚደንቱ ይህን ያሉት ዛሬ (ማክሰኞ ኅዳር 03 ቀን፣ 2017 ዓ.ም)አዘርባጃን ባኩ ውስጥ በሚካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የከባቢ አየር ንግግር ላይ ነው ። COP29 በተባለው የከባቢ አየር ጉዳይ ጉባኤ ላይ ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ወደ 200 የሚጠጉ ሃገራት ተካፋይ መሆናቸውን ሮይተርስ የዜና ምንጭ ዘግቧል ። ሻርል ሚሼል ያደጉ ሃገራት የአውሮጳ ኅብረትን አብነት በማድረግ የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ በጉባኤው አሳስበዋል። 

በየሳምንቱ፣ በዓለማችን የሆነ ቦታ፣ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያመጣውን አስከፊ ውጤት መጋፈጥ ይኖርብናል ። ይህ የአየር ንብረት ስጋት ለሰው ልጅ የኅልውና ስጋት ነው፥ እናም በዚህ ተፈጥሮን በተጋረጠው አደጋ ላይ እንደ የሰው ልጅነታችን ጦርነት የማወጅ ኃላፊነት አለብን ። አንዳንዶቻችን ደግሞ ከሌሎቹ የበለጠ ተጠያቂዎች ነን፦ ያደጉት ሃገራት ። »

የአውሮጳ ምክር ቤት ፕሬዚደንቱ ንግግር ያሰሙት የአውሮጳ ኮሚሽን ፕሬዚደንትን ኡርዙላ ፎን ደር ላየንን ወክለው መሆኑም ተገልጧል ። ፕሬዚደንቷ ቤልጂየም ብራስልስ ውስጥ ባለው አስቸኳይ የፖለቲካ ጉዳይ የተነሳ በጉባኤው አልታደሙም ። ከኡርዙላ ፎን ደር ላየን በተጨማሪ በጉባኤው ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ ማሳደር የሚችሉ የብዙ ሃገራት መሪዎች በየብዙ ሃገራት አልተገኙም ።

ብራስልስ፥የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንሥትር በዩክሬን ጉዳይ ከአውሮጳ መሪዎች ጋር በአስቸኳይ ሊመክሩ ነው

የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን በዩክሬን ጉዳይ ከአውሮጳ መሪዎች ጋር ነገ ብራስልስ ውስጥ አስቸኳይ ውይይት ሊያደርጉ ነው ። በዘንድሮ የአሜሪካ ምርጫ ያሸነፉት ዶናልድ ትራምፕ የፕሬዚደንትነት መንበረ-ሥልጣኑን ከመረከባቸው በፊት ውጭ ጉዳይ ሚንሥትሩ ከአውሮጳ ተባባሪዎቻቸው ጋር ዩክሬንን እንዴት መደገፍ እንደሚቻል አስቸኳይ ንግግር ያደርጋሉ ተብሏል ።  በተሰናባቹ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን  ስር የሚያገለግሉት አንቶኒ ብሊንከን በነገው ዕለት ከናቶ እና የአውሮፓ ኅብረት ተባባሪዎቻቸው ጋር አስቸኳይ ውይይት እንደሚያደርጉ የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት (AFP) ዘግቧል ። በአንድ ወቅት ለሩስያ ፕሬዚደንት ብላድሚር ፑቲን አድናቆት እንዳላቸው የተናገሩት ዶናልድ ትራምፕ ዳግም መመረጥ ለወደፊት የዩክሬን ድጋፍ ላይ ብርቱ ሥጋት ጋርጧል ።

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።