የላሊበላ ውቅር ዐብያተ ክርስቲያናት ጥበቃ
ሐሙስ፣ ሐምሌ 28 2014የላሊበላ ውቅር ዐብያተ ክርስቲያናት በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት በምህጻሩ ዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ሆነው የተመዘገቡት እንደ ጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር በ1978 ዓ.ም.ነበር። ይህ ሃይማኖታዊ ታሪካዊና ስነጥበባዊ ፋይዳው እጅግ ከፍ ያለ ዋጋ የሚሰጠው በዚህ ቅዱስ ስፍራ የሰፈሩት ቅርሶች በተፈጥሮና እንዲሁም በጊዜያዊነት ቅርሱን ለመጠበቅ በሚል የተሰሩት የብረት መጠለያዎች በቅርሱ ላይ ስጋት ደቅነው መቆየታቸው ይታወቃል። ባለፈው ዓመት ደግሞ በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰው ጦርነት የቅርሱን ደኅንነት ለአደጋ ያጋለጠ ሌላው ስጋት እንደነበረም ይታወሳል።በርግጥ በላሊበላ ቅርሶች ላይ የተጋረጡትን አደጋዎች በመከላከል ረገድ የኢትዮጵያ መንግሥትን ፈረንሳይንና ዩኔስኮን ጨምሮ መሰል ሌሎች አጋዥ አካላት የተካተቱበት እንቅስቃሴዎች ቢጀመሩም፤የታቀዱት ፕሮጀክቶች ግን በታሰበላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ባለመከናወናቸው የቅርሶቹ ለአደጋ ተጋላጭነት ስጋት እንዲጨምር ማድረጉ ይነገራል። ሆኖም ሰሞኑን የቅርሱን ጥገና በማስጀመር ሂደት ጉልህ ሚና አለው የተባለው ከኢትዮጵያ ቱሪዝም ቢሮ፣የቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣናንመስሪያ ቤት እንዲሁም ከላሊበላ ዐብያተ ክርስቲያናትና ከቅርሱ እድሳትና ጥበቃ ፕሮጀክት የተውጣጡ የልዑካን ቡድን አባላት የላሊበላ ቅርስ ፕሮጀክት ከሚመለከታቸው የፈረንሳይ የመንግሥት ሃላፊዎችና ተቋማት ጋር ለመነጋገር ፓሪስ ነበሩ።
ሃይማኖት ጥሩነህ
እሸቴ በቀለ