1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስኢትዮጵያ

የሉሲ ወይም ድንቅነሽ ቅሪተ-አካል ግኝት 50ኛ ዓመት

ረቡዕ፣ መስከረም 8 2017

በጎርጎሪያኑ ህዳር 1974 ዓ.ም. በአፋር የአዋሽ ስምጥ ሸለቆ የተገኘው የሉሲ ወይም የድንቅነሽ ቅሪተ አካል እነሆ 50 ዓመቱን ይዟል። 3.2 ሚሊዮን ዓመት ዕድሜ ያለው የሉሲ ቅሪተ-አካል ስለ ሰው ልጆች አመጣጥ ለማጥናት ዓለም አቀፋዊ ፍላጎት የቀሰቀሰ እና ቀደም ሲል ስለሰው ልጆች አመጣጥ የነበረውን ታሪክ እና አመለካከት የለወጠ ሆኗል።

https://p.dw.com/p/4koCH
 ዶክተር ዶናልድ ጆንሰን
በአሜሪካው ክሊቭላንድ የተፈጥሮ ታሪክ ሙዚየም ፓሊዮአንትሮፖሎጂስት የሆኑት ዶክተር ዶናልድ ጆንሰን ፤ ከሉሲ ግኝት ጋር በጎርጎሪያኑ 1974 ዓ/ም ።ምስል picture-alliance/akg-images

የሉሲ ወይም ድንቅነሽ ቅሪተ-አካል ግኝት 50ኛ ዓመት

ቅሬተ አካሉ  «ሉሲ» የሚለውን ስያሜ እንዴት አገኘ?

በሰሜን ምሥራቅ ኢትዮጵያ በአፋር  የአዋሽ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ በዶናልድ ጆንሰን የሚመራው የሳይንስ ሊቃውንት ቡድን ከ50 ዓመት በፊት በጎርጎሪያኑ 1974 ዓ.ም. ቅሪተ አካላትን በማሰስ ላይ ነበሩ። በዚሁ ዓመት ኅዳር ወር ታዲያ ተመራማሪዎቹ  በቁፋሮ ያወጧቸው ከነበሩ ቁርጥራጭ ቅሬተ አካሎች እና የመገለገያ መሣሪያዎች በተለየ ሁኔታ በብዛትም በመጠኑም ከፍ ያለ እና ለምርምራቸው ፍንጭ የሚሰጥ ቅሬተ-አካል በቁፋሮ አገኙ። በበረሃማው የአፋር ዝቅተኛ ቦታ፤ ሐዳር ላይ በጣሉት ድንኳን ውስጥ ሊቃውንቱ ይህ ግኝት የፈጠረባቸውን ደስታ ያከበሩት ግን እንዲሁ አልነበረም። በዚያን ዘመን በገነኑት ዘቢትልስ በተባሉ ሙዚቀኞች የተቀነቀነውን «ሉሲ ኢን ዘስካይ ዊዝ ዘዲያመንድ/Lucy in the Sky with Diamonds/  በሚለው ሙዚቃ አጅበው ነበር።
እናም ይህ ሚሊዮን ዓመታትን  የተሻገረ  ቅሪተ-አካል  ስያሜ ከዚህ ሙዚቃ ጋር ተቆራኘ። ኢትዮጵያዊ ስያሜዋ ግን ድንቅነሽ ሆነ። ሉሲ ወይም በኢትዮጵያዊ ስሟ ድንቅነሽ 3.2 ሚሊዮን ዓመታትን ተሻግራ የኖረች  በመካከለኛ ዕድሜ ያለች ሴት መሆኗንም ተመራማሪዎቹ  ለዓለም ይፋ አደረጉ።  

ከዚህ ባሻገር  ቅድመ አያቶቻችን ቢያንስ ከ3.2 ሚሊዮን ዓመታት በፊት በሁለት እግራቸው መራመድ ይችሉ እንደነበር ለመጀመሪያ ጊዜ የተረጋገጠው በ ሉሲ አስደናቂ ግኝት ነው። 
በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ ተመራማሪ እና መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ሙሉጌታ ፍስሐ እንደሚሉት፤ የሉሲ መገኘት በዘርፉ ለሚደረገው ምርምር  ትልቅ ግብዓት ሆኗል። 
«እንደሚታወቀው በሰው ልጅ ዝግመታዊ ለውጥ በተመለከተ በአብዛኛው ከሉሲ መገኘት በፊት በቲዎሪ የተመሰረተ ነበር። ያው እነ ዳርዊን ቀደም ብለው ስለ ሰው ዘር አመጣጥ ሀሳባዊ የሆኑ ጽሑፎች በማሳተም ብዙ የምሁር ክፍልን በማሳመን ላይ ነበሩ። ግን ሉሲ በ1974 እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ስትገኝ፤ የመጀመሪያው እውነትኛ የሰው ዘር አመጣጥን የሚያሳይ የቅሬተ-አካል «ፎርም» መገኘቱ ፤ ከመገኘቱም በላይ ደግሞ 40 በመቶ ሙሉ በመሆኑ፤ ቅሬተ-አካሉ በዚህ «በሂውማን ኢቮሎሽን» ወይም በሰው ዘር ዝግመታዊ አመጣጥ ላይ ትልቅ የሆነ ዕውቀት እና ለሳይንሱ በማስረጃ የተደገፈ ትልቅ ግብዓት ሆኖ አገልግሏል ማለት ነው።» 

የሉሲ ወይም የድንቅነሽ ቅሪተ አካል  3.2 ሚሊዮን እድሜ አለው
በጎርጎሪያኑ ህዳር 1974 ዓ.ም. በአፋር የአዋሽ ስምጥ ሸለቆ የተገኘው የሉሲ ወይም የድንቅነሽ ቅሪተ አካል 3.2 ሚሊዮን ዓመት ዕድሜ ያለው ነው።ምስል Dave Einsel/Getty Images

የሉሲ ቅሬተ አካል የዚያን ዘመን ሰው ይራመድ እንደነበር አሳይቷል 

በአሜሪካው ክሊቭላንድ የተፈጥሮ ታሪክ ሙዚየም ፓሊዮአንትሮፖሎጂስት በሆኑት ዶናልድ ጆንሰን የተገኘው የሉሲ ቅሬተ-አካል አውስትራሎፒቲከስ ከሚባለው ቀደምት ዝርያ የሚመደብ ሆኖ ተገኝቷል። እንደ ተመራማሪዎቹ ሉሲ 27 ኪሎ ግራም ክብደት እና  1.1 ሜትር ቁመት የነበራት ሲሆን፤ ከዝንጀሮዎች ጋር ተመሳሳይ የሆነ ትንሽ የራስ ቅል የነበራት። ነገር ግን የዳሌ እና የእግር አጥንቶቿ ከዘመናዊው ሰው ተመሳሳይነት ያላቸው በመሆኑ፤ የሉሲ ዝርያዎች ቀጥ ብለው መቆም እና መራመድ የሚችሉ መሆናቸውን አረጋግጧል። ከዚህ አንፃር በተለያዩ ሀገራት ቅረተ-አካሎች ቢገኙም ሉሲ ከሌሎቹ ስትነፃጸር በዚያን ዘመን ይኖር የነበረውን ጥንታዊ ሰው አካላዊ ሁኔታ እና እንቅስቃሴን በማብራራት ረገድ የበለጠ ገላጭ መሆኗን ፕርፌሰሩ ያስረዳሉ። 

«አንደኛው መሠረቱን ነው ያስተካከለው። በአጠቃላይ  በሰው ልጅ አመጣጥ በተለይ 3.2 ሚሊዮን ዓመት አካባቢ በነበረው የሰው ዘር አመጣጥ መሠረቱን ነው ያደላደለው። ምክንያቱም የመጀመሪያው 40 በመቶ ሙሉ የሆነቅሬተ-አካልመገኘቱ ብዙ ስለ ሰውነት አካላቱ የብሬን/የአንጎል/ ግዝፈቱ ቁመናው ወዘተ የተሟሉ ነገሮች በመኖሩ ከሌላው ዓለም ግኝቶች የበለጠ አድርጎታል። ምክንያቱም ሃሳቦች አሉ። ሰዎች የሚያስቀምጧቸው መላ ምቶች አሉ። ለምሳሌ በ3 .2 ሚሊዮን ዓመት አካባቢ የሰው ልጅ ይህን ይመስል ይሆናል። ይባላል ግን አንዳንድ ጊዜ የተደረጉት ሀሳቦች ልክ አይሆኑም።በብዙ ምክንያቶች። በአካል ወይም ቅሬተ- አካሉ። ፊዚካሊ የመገኘቱ ጉዳይ ግን ለምሳሌ የ«ብሬን ሳይዙ» ምን ያህል ነው የሚለው ላይ ሙሉ እውቀት ይሰጣል።ወይስ በሁለቱ ትገለገል ነበር? ምናልባት አንዳንድ ያልተመለሱ ነገሮች ቢኖሩም ለምሳሌ ሉሲ በሁለት እግሯ ትራመድ ነበር ወይ በሁለት እግሯ ዛፍ ላይ ትወጣ ነበረ? ወይስ በሁለቱ ትገለገል ነበር? » ብለዋል። 

ፕሮፌሰር ሙሉጌታ ፍስሐ
ፕሮፌሰር ሙሉጌታ ፍስሐ ፤በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ ተመራማሪ እና መምህር ምስል privat

የሉሲ ቅሬተ አካል 40 በመቶ መሆን ለበለጠ ምርምር አነሳስቷል

ከዚህ በተጨማሪ ፕሮፌሰር ሙሉጌታ እንደሚሉት ከሦስት ሚሊዮን ዓመት በኋላ የአካሏ 40 በመቶ መገኘትም ተመራማሪዎችን ለበለጠ ምርምር የሚጋብዝ ሆኗል። 
«ሌላው 40 በመቶ መገኘቱ ደግሞ ሌላ አዲስ ነገርም እንድናስብ አድርጎናል። ለምሳሌ እንዴት ቢሆን ነው 40 ፐርሰንት ልትገኝ የቻለችው፤ የሚለው ሌላው ደግሞ እንደዚሁ በምን አይነት ሁኔታ ሞተች የሚለውን ሌላ ጥያቄ ሁሉ እስከ 2016 ዓ.ም. ሳይመለስ ቆይቷል። በአጠቃላይ ሲታይ ግን የቅሬተ-አካሉ ሙሉነት በሰው ልጅ ዝግመተ ለውጥ የነበሩ ጥያቄዎች እንዲመለሱ እና የ«ሂውማን ኢቮሉሽን»ን የሚያሳዩ ቅሬተ አካላት  በእርግጠኝነት በተለያዩ ዓለም ክፍሎች ሊኖሩ ይችላሉ የሚለው ሃሳብ  በአብዛኛው ደግሞ በኢትዮጵያ ከ1974 ወዲህ እንደ ትልቅ ሪቮሊሽን ነው። ብዙ ሃሳብ እንዲመነጭ ብዙ ተመራማሪዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ብዙ ግኝቶችን ለማግኘት መሠረት የጣለ ነው።» 

እንደ ሰው ልጆች ትራመድ ነበር የሚል ግምት አለ
እንደ ሰው ልጆች ትራመድ ነበር የሚል ግምት ቢኖርም ከጦጣዎች የምትጋራዉ ገጽታ፣ የእጆቿ መጉበጥና ከእግሮቿ ረዝሞ መገኘት ዛፍ ላይ ትንጠላጠል ነበር የሚል መላምት አሳድሯል።ምስል AP/picture alliance

ሉሲእንደ ሰው ልጆች ትራመድ ነበር የሚል ግምት ቢኖርም ከጦጣዎች የምትጋራዉ ገጽታ፣ የእጆቿ መጉበጥና ከእግሮቿ ረዝሞ መገኘት ዛፍ ላይ ትንጠላጠል ነበር የሚል መላምት አሳድሯል። እንደ ተመራማሪዎቹ ደፍጣጣ አፍንጫዋ ሰፋ ያለው አገጯ ሉሲን መሠረታቸዉ አፍሪቃ ከሆኑት ችንፓዚ ከተባሉ የዝንጀሮ ዝርያወች ጋር ያመሳስላታል። ይህም ሉሲ ከሌሎች ቀደምት የሰው ዘር ግኝቶች በበለጠ አፍሪቃ የሰዉ ዘር መሠረት መሆኗን አሳይቷል። ስለ አሟሟቷም የተለያየ መላምት እንዲሰጥ አድርጓል። ተመራማሪው ፕሮፌሰር ሙሉጌታ ፍስሐ «ኔቸር» በተባለው የሳይንስ መጽሔት የታተመው ጽሑፋቸው በአሟሟቷ ላይ አዲስ መንገድ ከፍቷል።

«በነሉሲ ጊዜ እንግዲህ «ሞደርን ሁውማን» ወይም ዘመናዊ ሰው  አልነበረም።በ«ሂውማን ኢቮሊዩሽን»ወይም በሰው ዘር ዝግመተ ለውጥ  ቋንቋ ።አሁን ባለው ጊዜ ግን ሰዎች ከትልቅ ግንብ ወይም ደግሞ ተራራ የሚወጡ ሆነው ከላይ ሲወድቁ ወይም ከትልቅ ዛፍ ሲወድቁ ያው ኮንሸስ ሆነው ሆዳቸው መሬት እንዳይነካ በእጃቸው ነው በተቻለ መጠን ሲወድቁ ለመከላከል የሚፈልጉት ያ ሲሆን ክብደቱ ሲበዛ እና ከፍታው ሲበዛ ወደ መሬት እጃቸውን ረግጠው ሲወድቁ በዚያን ጊዜ ነው ያ «ኮምፕሬሽን»  የሚፈጠረው።ትከሻ እንደዚያ የሚሆነው በዚህ አይነት የ«ፕሬዠር»ወይም ግፊት  ሁኔታ ሲወድቁ ነው።ይህንን ካየን በዘመነ ሉሲ ከፍተኛ ተራራ የለም ሀዳር ላይ ሜዳ ነው።ከተራራ መውጣት አይቻልም።ሌላ ብዙ «ሴናርዮዎች» ተፈጥረው አንድ ሊሆን የሚችለው አጋጣሚ ከትልቅ ዛፍ መውደቅ ብቻ ነው።ሊሆን የሚችለው የሚል ሳብ ነበረ እና።ይህንን መሰረት አድርገን ሶስት ጥያቄዎችን መመለስ ነበረብን።የዚህ አይነት ምልክት ከታዬ ሉሲ መሬት ላይ ሂያጅ ነበረች ወይስ ዛፍ ላይ ትወጣ ነበር? 40 በመቶ መገኘቱስ ከዚጅ ጋር የተያያዘ ይሆን?በምን አይነት ሁኔታስ ሞታ ይሆን?የሚለው ብዙ ጥያቄዎች ነበሩ እና እነዚህ ጥያቄዎችን መሰረት አድርገን ጥናቶቹ ተደርገው የተገኙት አጥንቶች በሙሉ በሲቲ ስካን የሉሲ አጥንቶች ሲታዩ ከላይ ከጭንቅላቷ ጀምሮ እስከ መንጋጋዋ፣ ትከሻዋ፣ እጇ እና የእግር አጥንቶቿ እስከታች ድረስ ተመሳሳይ የሆነ «ፍራክቸር»ወይም የአጥንት ስብራት ነበራቸው።» በማለት ከዛፍ ወድቃ ሞታ ሊሆን ይችላል የሚለውን ፍንጭ በመስጠት ጥናታቸው ስለ አሟሟቷ መረጃ  መስጠቱን አስረድተዋል። 

የሉሲ መገኘት ለሌሎች ቅሬተ አካሎች መገኘት መሠረት ጥሏል

በአጠቃላይ የሉሲ መገኘት ወደ ኋላ በኢትዮጵያ ለተጘኑት እንደ «አርዲ» እና «ሰላም» ያሉ ቅሬተ-አካላት መሠረት ጥሏል። ኬንያ፣ ታንዛኒያ እንዲሁም ቻድን በመሳሰሉ ሃገራትም ቅሬተ-አካልን መሠረት በማድረግ በሰው ልጆች አመጣጥ ላይ የሚደረገው የምርምር ቀጥሏል። 
ስለሰው ልጅ አመጣጥ ፍንጭ የሚሰጡ ቅሪተ-አካሎች ከዘጠና በመቶ በላይ በኢትዮጵያ መገኘታቸውን የገለፁት ፕሮፌሰር ሙሉጌታ፤ ያም ሆኖ የቅሪተ-አካል መገኛ ሀገር የመሆኗን ያህል ዓለም አቀፍ ተመራማሪዎችን በመሳብ ረገድ አልተጠቀመችም ይላሉ።

በዚህ ሁኔታ 50 ዓመታትን ያስቆጠረው የሉሲ ቅሪተ-አካል ስለ ሰው ልጆች አመጣጥለማጥናት ዓለም አቀፋዊ ፍላጎት የቀሰቀሰ እና ቀደም ሲል ስለሰው ልጆች ታሪክ የነበረውን አመለካከት የለወጠ ሆኗል።አፍሪቃ ብሎም ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ መሆናቸውንም ለመላው ዓለም አሳውቋል።  
የሉሲ 50ኛ ዓመትም ካለፈው ከጎርጎሪያኑ 2023 ኅዳር ወር ጀምሮ በሰው ዘር አመጣጥ ላይ ምርምር በሚያደርጉ ዩንቨርሲቲዎች፣ ተቋማት እና ግለሰቦች ዘንድ በመላው ዓለም እየተከበረ ይገኛል። በዘርፉ ምሁራን ዓመቱም «የሉሲ ዓመት» ተብሎ ተሰይሟል። 
በኢትዮጵያም በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የአንትሮፖሎጂ ትምህርት ክፍል አማካኝነት እስከ መጭው ኅዳር ወር የሚዘልቅ የተለያዩ ዝግጅቶች እየተከናውኑ ነው።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሐይ ጫኔ
ሽዋዬ ለገሠ