ዉይይት፤ የፕሪቶርያዉ ስምምነት በርግጥ ተፈጻሚ እየሆነ ነዉ?
ሰኞ፣ መጋቢት 11 2015የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና ህዝባዊ ወያነ ሐርነት ትግራይ «ህወሓት» ለሁለት ዓመት ያደረጉት ጦርነት ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም ደቡብ አፍሪቃ ፕሪቶርያ ላይ በሰላም ስምምነት ከተቋጨ አራት ወር ሆኖታል። ይህ አስከፊ ሰብዓዊ መብት ጥሰት የተፈፀመበት ጦርነት ቢያበቃም ብዙዎች የፕሪቶርያዉ የሰላም ስምምነት ተግባራዊነቱ አጠያያቂ ሆንዋል ሲሉ አስተያየት ይሰጣሉ። አንዳንዶች የፕሪቶርያዉ ስምምነት ከርዕስነት ወጥቷል ብለዉ የሚያስቡ እንዳሉ ሁሉ አንዳንዶች ስምምነቱ በከፊል ነዉ የተሟላዉ ብለዉ ያምናሉ።
በዚህ ሳምንት ለሁለት ቀናት ኢትዮጵያን የጎበኙት የአሜሪካዉ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ፕሪቶርያ ላይ የተፈረመው የሰላም ስምምነት ግጭትን በዘላቂነት በማስቆም አፈሙዝን ጸጥ የተደረገበትን ሂደት አድንቀዋል። ለዚህም አገራቸው አሜሪካ ድጋፏን እንደምትቀጥል ነዉ ቃል የገቡት። ሆኖም በትግራይ ተከስቶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች በተዛመተው የእርስ በርስ ጦርነት ተሳታፊ በሆኑ አካላት በተፈጸሙ ጥሰቶች ዙሪያ ተጠያቂነት ሊኖር እንደሚገባ የአሜሪካዉ የዉች ጉዳይ ሚኒስትር አሳስበዋል።
በሌላ በኩል መንግሥት ተለስላስሷል፤ የፕሪቶርያዉን የሰላም ስምምነት እያስፈጸመ አይደለም፤ የሚሉ እንዳሉ ሁሉ ህወሓት እየሄደበት ያለዉ መንገድ ትክክል አይደለም፤ እንደ ስምምነቱ ሁሉን አካታች የሆነ ሽግግር መንግሥት በትግራይ መመስረት አልቻለም፤ ስልጣንን የማካፈል ፍላጎት የለዉም የሚሉ ብዙዎች ናቸዉ። የፌደራሉ መንግሥት ከህወሓት ጋር ደቡብ ኢትዮጵያ ላይ ሲገናኝ በምን ጉዳይ ላይ እንደተነጋገረ እና እንደተስማማ የታወቀ ነገር የለም የሚሉ ትችቶችም ይሰማሉ። የፕሪቶርያዉ ስምምነት ምን ያህል ተግባራዊ ሆንዋል ተብሎ ይታመናል? ወደፊትስ ምን ያህል ተግባራዊ ይደረጋል ?
በእነዚህ ነጥቦች ላይ ሃሳቦቻቸዉን ያካፈሉን የዉይይቱ ተሳታፊዎች፤
አቶ ግርማ ሰይፉ፤ የኢዜማ ስራ አስፈፃሚ አባል እና የአ/አ ከተማ ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ
ዶ/ር ምዑዝ ግደይ፤ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር እና የትግራይ ፖሊሲ ጥናት ተቅዋም ተመራማሪ
ዶ/ር ደጀን መዝገብ፤ የትግራይ ነጻነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ
አቶ ዓምዶም ገብረስላሴ፤ የዓረና ትግራይ ለዲሞክራሲ እና ሉዓላዊነት የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ እንዲሁም
አቶ ያሬድ ኃይለማርያም፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ናቸዉ።
ሙሉ ዉይይቱን የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን። አስተያየቶትንም ያካፍሉን!
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሐመድ