1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዉይይት፣ የኢትዮጵያ፣ የሶማሊያና የግብፅ መዛዛት እንደቀጠለ ነዉ።ከእንግዲሕስ?

እሑድ፣ መስከረም 5 2017

ቱርክ ሁለቱን ሐገራት ለማስታረቅ እየጣረች ነዉ።የሶማሊያና የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በቱርክ ሸምጋይነት የሚያደርጉት ድርድር ለሶስተኛ ዞር እንደሚደረግ ሲጠበቅ፣በዐባይ ዉኃ አጠቃቀም ሰበብ ለምዕተ አመታት ከኢትዮጵያ ጋር የምትወዛገበዉ ግብፅ ባለፈዉ ነሐሴ ለሶማሊያ ጦር መሳሪያ ማስታጠቅ ጀምራለች።ሶማሊያ ዉስጥ 10ሺሕ ወታደር ለማስፈር አቅዳለችም።

https://p.dw.com/p/4kcBZ
በቀይ ባሕርና በአደን ባሕረ ሠላጤ አካባቢዎች የተለያዩ ኃያላን መንግሥታት ጦር ኃይሎች ሠፍረዋል
የቀይ ባሕርና የአደን ባሕረ ሠላጤ ባሕሮችና አካባቢ የኃያላን መንግሥታት ጦር ኃይሎች የሚተራመሱባቸዉ አካባቢዎች ናቸዉምስል Italian Navy/ZUMA/picture alliance

ዉይይት፣የኢትዮጵያ፣ የሶማሊያና የግብፅ መዛዛት እንደቀጠለ ነዉ።ከእንግዲሕስ?

 

ለዛሬዉ ዉይይታችን «የኢትዮጵያ፣ ሶማሊያና ግብፅ ፍጥጫ» የሚል ርዕስ ሰጥተዋል።የኢትዮጵያ መንግስት ዓለም አቀፍ የመንግሥትነት ዕዉቅና ከሌላት ሶማሊላንድ ጋር ወደብ ለመኮናተር ባለፈዉ ታሕሳስ ማብቂያ የመግባቢያ ሥምምነት መፈራረሙ የቆሰቆሰዉ መዘዝ ወትሮም ያልተረጋጋዉን የአፍሪቃ ቀንድ ወደ ከፋ ግጭትና ጦርነት ይከተዋል የሚል ሥጋት አሳድሯል።

የሞቃዲሾ ባለሥልጣናት የአዲስ አበባና የሐርጌሳ መሪዎችን ሥምምነት ለመቀልበስ እስከ ፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ድረስ ከፍተኛ ግፊትና ጫና አድርገዋል።ከኢትዮጵያ ጋር የነበራቸዉን ግንኙነት አቋርጠዋል፤የኢትዮጵያ አየር መንገድ አዉሮፕላኖች በሶማሊያ የአየር ክልል ላይ እንዳይበሩ አግደዋል፤ሶማሊያ የሠፈረዉ የኢትዮጵያ ሠራዊት እንዲወጣ አዝዘዋል፤ከቱርክና ከግብፅ ጋር  ወታደራዊ ስምምነት ተፈራርመዋልም።

ቱርክ ሁለቱን ሐገራት ለማስታረቅ አሁንም ድረስ እየጣረች ነዉ።ይሁንና የሶማሊያና የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በቱርክ ሸምጋይነት የሚያደርጉት የስማበለዉ ድርድር ለሶስተኛ ዞር እንደሚደረግ ሲጠበቅ፣ በዐባይ ዉኃ አጠቃቀም ሰበብ ለብዙ ምዕተ አመታት ከኢትዮጵያ ጋር የምትወዛገበዉ  ግብፅ ባለፈዉ ነሐሴ  ለሶማሊያ ጦር መሳሪያ ማስታጠቅ ጀምራለች።ሶማሊያ ዉስጥ 10ሺሕ ወታደር ለማስፈር አቅዳለችም።

የኢትዮጵያ መሪዎች የሶማሊያና የግብፅ መሪዎችን እርምጃ አዉግዘዉ «አደብ እንዲገዙ» እያሰጠነቀቁ ነዉ።የኢትዮጵያ የጦር ጄኔራሎችም ሁለቱ ሐገራት ኢትዮጵያዉን ለማጥቃት ከቃጡ «ጠንካራ አፀፋ» እንደሚገጥማቸዉ እየዛቱ ነዉ።

ከግራ ወደ ቀኝ የኤርትራ ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ፣ የሶማሊያ ፕሬዝደደንት መሐመድ አብዱላሒ (ፎርማጆ)ና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አሕመድ 2010።የሶስቱ መሪዎች ሚስጥራዊ ወዳጅነት ሚስጥሩ ሳይፈታ ፈረሰ
ከግራ ወደ ቀኝ የኤርትራ ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ፣ የሶማሊያ ፕሬዝደደንት መሐመድ አብዱላሒ (ፎርማጆ)ና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አሕመድ 2010።የሶስቱ መሪዎች ሚስጥራዊ ወዳጅነት ሚስጥሩ ሳይፈታ ፈረሰምስል Office of the Prime Minister-Ethiopia

የሶማሊያ ባለሥልጣናት ሕዝባቸዉnnን «እራሱን እንዲከላከል» ላሉት እርምጃ እያዘጋጁት ነዉ።የኢትዮጵያ ጦርን ለመመከት በቂ ኃይል እንዳላቸዉም እስታዉቀዋል። የኢትዮጵያ ጦር ኃይል በበኩሉ  ከሶማሊያ ጋር በሚያዋስኑ አካባቢዎች ተጨማሪ ወታደሮች ማስፈሩ ተዘግቧል።ሶማሊላንድ የግብፅ የባሕል ቤተ መፀሐፍትን ዘግታ፣ ሠራተኞቹ ከሐገሯ እንዲወጡ አዝዛለች።ከኢትዮጵያ ጋር የተፈራረመችዉ ሥምምነት በቅርቡ ሕጋዊ ይሆናል ብላለች።

ጅቡቲ ዉጥረቱን ለማርገብ ለኢትዮጵያ ያቀረበችዉ የወደብ አማራጭም እስካሁን ተቀባይነት ማግኘት አለማግኘቱ ግልፅ አይደለም።ዉጥረቱ አይሏል።ከእንግዲሕስ? ሶስት እንግዶች አሉን።

1.አቶ ጀማል ድርዬ ኸሊፋ---የቀድሞ የምክር ቤት አባል፣ የሶማሊ ክልል ፕሬዝደንት አማካሪና የሕግ ባለሙያ ናቸዉ።

2.አቶ ባይሳ ዋቅ ወያ-----የቀድሞ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዲፕሎማትና የሕግ ባለሙያ

3.ዶክተር ሙከረም ሚፍታሕ--------የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ ረዳት ፕሮፌሰርና የፖለቲካ ተንታኝ ናቸዉ

ነጋሽ መሐመድ