ወጣቶቹን የሚያረግፈው ስደት፦ ከደቡብ ኢትዮጵያ ወደ ደቡብ አፍሪካ
ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 25 2015ባለፈው ጥቅምት በማላዊ የ29 ሰዎች አስከሬን መገኘቱ ተሰማ። በወቅቱ ፖሊስ እንዳለው ከሟቾቹ መካከል 25ቱ ኢትዮጵያውያን ነበሩ። ከወር ገደማ በኋላ እንደገና ተመሳሳይ አስደንጋጭ ክስተት ተፈጠረ። በህዳር የኢትዮጵያውያን ስደተኞች ሳይሆን አይቀርም የተባለ የ27 ወንዶች አስከሬኖች ማግኘቱን የዛምቢያ ፖሊስ አስታወቀ። አስከሬኖቹ የተገኙት ከዛምቢያ ዋና ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ አንድ የእርሻ ሥፍራ ተጥለው ነው።
እስካሁን የተደረጉ ምርመራዎች የሚጠቁሙት እነዚህ ኢትዮጵያውያን ሕይወታቸውን ያጡት ደቡብ አፍሪካ ለመግባት ሲጓዙ ነው። በዚህ የስደት መስመር ወደ ደቡብ አፍሪካ የሚያቀኑት አብዛኞቹ የደቡብ ኢትዮጵያ በተለይም የሐድያ እና የከምባታ አካባቢዎች ተወላጆች ናቸው። ከኢትዮጵያ ተነስተው የተለያዩ አገራት ድንበር፣ ጫካ እና ውቅያኖስ በማቋረጥ ደቡብ አፍሪካ እስኪደርሱ ከሚሞቱት ወጣቶች በተጨማሪ የሚከሰተው ስቃይ እና እንግልት ብርቱ ቢሆንም ስደቱ የመቀነስ አዝማሚያ አላሳየም።
ዓለም አቀፍ የፍልሰተኞች መርጃ ድርጅት (IOM) ባለፈው ግንቦት አንድ ጥናት ይፋ አድርጎ ነበር። ጥናቱ በታንዛኒያ አስር እስር ቤቶች ከሚገኙ 793 ኢትዮጵያውያንን 382ቱን ቃለ መጠይቅ በማድረግ የተከናወነ ነው። ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው 86 በመቶው ትዳር ያልመሰረቱ ናቸው። 99 በመቶው ወንዶች ናቸው። አማካኝ ዕድሜያቸው 20 ነው። 30 በመቶው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቀቁ ናቸው። ቃለ መጠይቅ ከተተደረገላቸው 99 በመቶው ከደቡብ ክልል በተለይ ከሐድያ እና ከከምባታ ዞኖች ስደት የገቡ ናቸው።
ይኸ የእንወያይ መሰናዶ የጉዞ መስመሩን ጠባይ፣ የስደቱን ገፊ ምክንያቶች እና የኢትዮጵያውያኑን መከራ የሚመረምር ነው። በውይይቱ ከተሳተፉት መካከል ኑሯቸውን በደቡብ አፍሪካዋ ጆሀንስበርግ ከተማ ያደረጉት አቶ ገዛኸኝ ሱማሞ አንዱ ናቸው። አቶ ገዛኸኝ የኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ አንቂ እና በደቡብ አፍሪካ በወንጀል መከላከል ጉዳይ ላይ ከአገሪቱ መንግሥት ጋር የሚሰሩ ናቸው።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰላም እና ደኅንነት ጥናት ተቋም ዳይሬክተር ዶክተር ፋና ገብረሰንበት ፍልሰት ለልማት እና እኩልነት ፕሮጀክት (the Migration for Equality and Development (MIDEQ) project) ከፍተኛ ተመራማሪ ናቸው። ከኢትዮጵያ ደቡብ አፍሪካ የተዘረጋውን የስደት መስመር የሚያጠኑት የማኅበራዊ ሳይንስ ባለሙያው አቶ ዮርዳኖስ አልማዝ ሰይፉ በውይይቱ ተሳትፈዋል።
ሙሉ ውይይቱን ለማድመድ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ፦
እሸቴ በቀለ