ከኦሮሚያ ክልል ተፈናቅለው ጃራ አካባቢ የተጠለሉ ወገኖች አቤቱታ
ሰኞ፣ መጋቢት 11 2015
ከኦሮሚያ ክልል ወለጋ ዞኖች በየአካባቢዎች በነበሩ ግጭቶች ምክንያት በተለያዩ ጊዜዎች ተፈናቅለው በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ጃራ የመጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮች በቂ ድጋፍ አላገኘንም አሉ። የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት ችግሩ መኖሩን አረጋግጧል። ሆኖም በርሀብ ምክንያት የአንድ ሰው ህይወት አልፏል የመባሉን አስመልክቶ ግን ጽሕፈት ቤቱ ግለሰቡ በህመም ሕይወቱ አልፏል ነው ያለው።
የአማራ ክልል በርካታ በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎችን ከሚያስተናግዱ ክልሎች መካከል አንዱ ነው። ባለፉት አራት ዓመታት በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ከማንነት ጋር በተያያዘ በተፈጠሩ ግጭቶች ተፈናቅለው አማራ ክልል ከገቡት መካከል የጃራ መጠለያ ጣቢያ ተፈናቃዮች የሚጠቀሱ ሲሆን እርዳታ እያገኙ እንዳልሆነ ለዶይቼ ቬሌ አመልክተዋል። በችግር ላይ ከሚገኙት መካከል የ10 ወር ሕጻን እናት የሆኑ ተፈናቃይ ይገኙበታል።
«በቅርብ ነው የመጣሁት፣ የ10 ወራት ሕጻን ልጅ አለችኝ፣ ምንም የማቀምሳት ነገር የለኝም፣ የምንተኛው መሬት ላይ ነው፣ ጡቴን ብቻ ነው የምትስበው፣ ጡቴም ባዶ ነው፣ ምንም ነገር ላቀምሳት አልቻልሁም።»
ሌለው ተፈናቃይ በበኩላቸው ርሀቡ ህዝቡን በከፍተኛ ደረጃ እየጎዳው መሆኑን ጠቅሰው በዚሁ ምክንያት የአንድ ሰው ህይወት ማለፉን ይናገራሉ።የአማራ ክልል ተፈናቃዮች አቤቱታ
«ሦስት ወር ሊሞላን ነው፣ የሚበላ የለም፣ መንግሥት ጭራሽ እያየን አይደለም፣ ሜዳ ላይ ነው የጣለን፣ እርዳታ ካገኘን 20 ቀን አልፎናል፣ አንድ ሰው በርሀብ ሞቶ በቅርቡ ቀብረናል።»
ወደ መጠለያ ጣቢያው ከመጣች ሦስት ዓመታትን እንዳስቆጠረች የምትናገረው ሌላዋ ተፈናቃይም ችግሩ በሴቶች ላይ የበረታ እንደሆነ አስረድታለች።
«ሴቶች በተለይ ምግብ የላቸውም መተኛ የላቸውም፣ ህክምናን ጨምሮ ምንም ነገር የለም፣ መጠለያ አለኝ፣ ግን በቂ አይደለም እርዳታ የለም ዛሬም ነገም ኑ ይላሉ ግን የለም።»
በቅርብ ተፈናቅለው የመጡ ወገኖች ምንም እርዳታ እንዳላገኙ ነው ተፈናቃዮቹ በምሬት የሚናገሩት። «እርዳታ ካለፋቸው ወር ሆኗቸዋል፣ እርዳታውን የአማራ መልሶ መቋቋምና ልማት ድርጅት ነበር ያቀረበላቸው 15 ኪሎ፤ ለአንድ ወር ከ20 ቀን ምንም አልቀረበም፣ በጣም እየተንገላቱ፣ እየተጎዱ ነው፣ ተፈናቃይ እየጨመረ ነው ሰሞኑን እንኳ 300 የሚጠጋ ተፈናቃይ መጥቷል።»
በአማራ ክልል የሰሜን ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዓለሙ ይመር የእርዳታ አቅርቦት ችግር መኖሩን አመልክተው ሆኖም በርሀብ የሰው ሕይወት አልፏል የተባለውን አይቀበሉትም። ግለሰቡ በህመም መሞቱን ነው ያስረዱት።
የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ዳይሬክተር አቶ ብርሀኑ ዘውዱ፣ መደበኛው እርዳታ መዘግየቱን አረጋግጠው ሆኖም ከሌሎች አካላት እርዳታ ተጠይቆ በዚህ ሳምንት ወደ ቦታው እርዳታ ይላካል ብለዋል። ከዚህ በፊት ለተፈናቃዮቹ የአማራ መልሶ ማቋቋምና ልማት ድርጅት (አመልድ) እርዳታ ሲያቀርብ እንደነበር ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
ከአመልድ የሚመለከተውን አካል በስልክ ለማነጋገር ያደረግሁት ጥረት ስልክ ባለመነሳቱ አልተሳካም። በጃራ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ በዋናነት ከኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ 10 ሺህ ያህል ተፈናቃዮች ይገኛሉ።
ዓለምነው መኮንን
ሸዋዬ ለገሠ
እሸቴ በቀለ