1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከአዉሮጳ ለኢትዮጵያ እና ኤርትራ የቀረበ ጥሪ

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 12 2013

ኤርትራ ከትግራይ ክልል ወታደሮቿን ለማስወጣት የገባችውን ቃል ተግባራዊ ልታደርግ ይገባል ሲሉ የአውሮጳ ህብረት የውጭ እና የደህንነት ጉዳይ ኃላፊ ጆሴፍ ቦሬል ጥሪ አቀረቡ። ቦሬል በመግለጫቸው  ኢትዮጵያ ለምታካሂደው ሀገር አቀፍ ምርጫ የታዛቢ ቡድን ለመላክ ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል። 

https://p.dw.com/p/3sH5D
Josep Borrell
ምስል Aris Oikonomou/AP Photo/picture alliance

የአውሮጳ ሕብረት ጠየቀ ለኤርትራ እና ኢትዮጵያ ያቀረበው ጥሪ

ኤርትራ ከትግራይ ክልል ወታደሮቿን ለማስወጣት የገባችውን ቃል ተግባራዊ ልታደርግ ይገባል ሲሉ የአውሮጳ ህብረት የውጭ እና የደህንነት ጉዳይ ኃላፊ ጆሴፍ ቦሬል ጥሪ አቀረቡ። የአውሮጳ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ትናንት በብራሰልስ ያደረጉት ስብሰባ ሲጠናቀቅ ጄሴፍ ቦሬል በሰጡት መግለጫ  ኢትዮጵያ ለምታካሂደው ሀገር አቀፍ ምርጫ የታዛቢ ቡድን ለመላክ ፍላጎት እንዳላቸው ተናግረዋል። 
የአውሮፓ ኅብረት የውጭ ጉዳይ ምኒስትሮች በትናንትናው ዕለት ባደረጉት ስብሰባ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ የተጓዙት የኅብረቱ ልዩ ልዑክ ፔካ ሐቪስቶን ሪፖርት አዳምጠዋል። ከስብሰባው በኋላ የአውሮጳ ህብረት የውጭ እና የደህንነት ጉዳይ ኃላፊ ጆሴፍ ቦሬል በሰጡት እንዳሉት በትግራይ ክልል ያለው ግጭት መቀጠሉ ሁኔታዎች አለመሻሻላቸው አሳሳቢ ሆኗል።  በተለይ ኤርትራ በቅርቡ ወታደሮቿን ከክክልሉ ለማስወጣት ለማስወጣት የገባችውን ቃል በፍጥነት ተግባራዊ ማድረግ ይገባታል ብለዋል።
«በትግራይ ያለው ሁኔታ መሻሻል እየታየበት አይደለም። ውግያው እንደቀጠለ ነው። የሰብአዊ እርዳታ ተደራሽነቱ አሁንም ክልከላ አለበት። የኤርትራ ወታደሮች አሁንም ድረስ አልወጡም። የሰብአዊ መብት ጥሰቱ አሁንም ተባብሶ እንደቀጠለ ነው። በተደጋጋሚ የሚነገረው የኤርትራ ወታደሮች ከክልሉ የመውጣት ጉዳይ ተጨባጭ እና በፍጥነት ተግባራዊ መደረግ ያለበት ነው።» 
ኤርትራ በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ወታደሮቿ መሰማራታቸውን ለመጀመሪያ ጊዜ ያመነችው በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኤርትራ አምባሳደር ሶፍያ ተስፋማርያም ለጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት ፕሬዝዳንት በፃፉት ደብዳቤ በኩል ባለፈው አርብ ነው። አምባሳደር ሶፍያ ተስፋ ማርያም ኤርትራ ትግራይ ክልል የሚገኙ ወታደሮቿን እንደምታስወጣ «በኤርትራ እና ኢትዮጵያ በከፍተኛ መሪዎች ደረጃ ከስምምነት ተደርሷል» ብለው ነበር።
ነገር ግን አሁንም ድረስ ተግባራዊ ያልተደረገው የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ ክልል አለመውጣት በክልሉ ለሚጠበቁ ለውጦች አለመታየት አንዱ እና ዋነኛው ምክንያት መሆኑን ጆሴፍ ቦሬል  ጠቅሰዋል።
ከአውሮጳ ህብረት በተጨማሪ ዩናይትድ ስቴትስ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኤርትራ ወታደሮች ትግራይን ለቀው እንዲወጡ ጠይቀዋል።
በቅርቡ ወደ ትግራይ ክልል ተጉዞ የነበረው የህብረቱ የልዑካን ቡድን በመቀሌ ከተማ በነበረው ቆይታ በትግራይ ክልል የጸጥታ ሁኔታ እንዲሻሻሻል እና የሰብአዊ አገልግሎት ተደራሽነት እውን ለማድረግ የተኩስ አቁም ስምምነት እጅጉን አስፈላጊ እንደሆነ አረጋግጦ መመለሱን  ቦሬል ገልጸዋል። 
በክልሉ በተፈጠሩ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ተጠያቂ የሆኑ አካላትን ለህግ ማቅረብ እንደሚገባም አሳስበዋል።
«እኛ አሁን አንድ ልንሆንበት የሚገባው በክልሉ በሰብአዊ መብት ጥሰቶች ፣ በጦር ወንጀሎች ፣ እና በጾታዊ ጥቃቶች መመርመር እና ለጥፋቱ ተጠያቂ የሆኑ ተጠያቂ መሆን አለባቸው ።»
በክልሉ የተፈጠሩትን እነዚህኑ ሰብአዊ ቀውሶች የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽን ከኢትዮጵያ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ጋር በጋራ ምርመራውን እንዲያካሂዱ አበረታታለሁም ብለዋል። 
የህብረቱ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ጆሴፍ ቦሬል ከትግራይ ክልል ወጣ ብለው በኢትዮጵያ የፊታችን ግንቦት ወር ሊካሄድ ቀጠሮ ስለተያዘለት አጠቃላይ ምርጫም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። በሀገሪቱ የሚታየው የጸጥታ ችግር ተባብሶ እስካልቀጠለ ድረስ የምርጫ ታዛቢ ልዑካንን ለመላክ መወሰናቸውን ለህብረቱ ምክር ቤት መግለጻቸውን አስረድተዋል። ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግስት ከምርጫው በፊት ሀገራዊ ንግግር ለማድረግ ቁርጠኝነቱን ማሳየት አለበት ብለዋል።
« እናም በመጨረሻ መንግስት ምርጫው እስኪደርስ ድረስ ብሄራዊ ውይይት ለማድረግ ቁርጠኝነቱን ማሳየት ይኖርበታል። እኔም በሀገሪቱ መጥፎ ሁኔታ እስካልተፈጠረ ድረስ የምርጫ ታዛቢ ቡድን ለመላክ መወሰኔን ለምክር ቤቱ አሳውቄአለሁ። »
ነገር ግን የታዛቢ ቡድኑ ወደ አዲስ አበባ የሚጓዘው ሕብረቱ በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ በቅርበት ከተከታተለ በኋላ መሆኑን ቦሬል በመግለጫቸው ማጠቃለያ ገልጸዋል።
 
ታምራት ዲንሳ

እሸቴ በቀለ