1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እንወያይ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በአማራ ክልል ሰላምን ያመጣ ይሆን?

ሰኞ፣ ነሐሴ 15 2015

ተወያዮች፤የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተፈጥሮዉ መብት ገዳቢ ነዉ፤ኢትዮጵያም ተሞክሮ ይህንኑ ያሳያል። መንግሥትን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት እንዲሁም ዝም ያለዉ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ሁሉ ለሰላም ወደ ድርድር እንዲመጡ፤ጦርነትም ይቁም ሲሉ ጥሪ አሰምተዋል።መንግሥት የጅምላ እስሩን ያቁም፤የአማራ ክልልን ጥያቄዎች ይመልስ ብለዋል። እርሶስ? አስተያየት አሎት?

https://p.dw.com/p/4VMRg
ኢትዮጵያ፤ በሰሜን አማራ ክልል ላሊበላ የፋኖ ሚሊሻ
ፎቶ ከማህደር፤ የፋኖ ሚሊሻ እሸቴ ዘዉዱ ህዳር 28 ቀን 2014 ዓ.ም ላሊቤላ በሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን ምስል Solan Kolli/AFP/Getty Images

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በአማራ ክልል ሰላምን ያሰፍን ይሆን? የክልሉን ጥያቄዎችስ ይፈታ ይሆን?

ኢትዮጵያ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሰላምን ያመጣ ይሆን? የክልሉን ጥያቄዎችስ ይፈታ ይሆን? ፋይዳዉ ምን ይሆን? 

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት እና ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ለሁለት ዓመታት ያካሄዱትና አስከፊ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ውድመት ያስከተለው የሰሜን ኢትዮጵያዉ ጦርነት ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ.ም በደቡብ አፍሪቃ ፕሪቶርያ ላይ ሲቋጭ፤ በኢትዮጵያ ሰላም ይሰፍናል የሚል ተስፋን አሰንቆ ነበር። ይሁንና የፕሬቶርያዉ ስምምነት ፊርማ ሳይደርቅ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የመንግስት አጋር የነበሩ የአማራ ክልል (የፋኖ ታጣቂዎች) ከአገር መከላከያ ሰራዊት ጋር አሁን ወደ ለየለት ጦርነት ከገቡ ወራቶችን አስቆጥረዋል

መንግሥት ባለፈው መጋቢት ወር በክልሎች የሚታዘዙ ልዩ ኃይል አባላት "ወደ ተለያዩ የፌዴራሉ ምንግስት የጸጥታ መዋቅሮች አሊያም ወደ ክልል መደበኛ ፖሊስ እንዲገቡ" መወሰኑን ተከትሎ በአማራ ክልል የልዩ ኃይል መልሶ መዋቀር እና የፋኖ ታጣቂዎችን ለመቆጣጠር የተካሄደዉ የህግ ማስከበር ዘመቻ፤በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የጎላ ግጭትን ፈጥሯል። ችግሩ በሀገሪቱ አማራን መሰረት አድርገው የሚደርሱ ጥቃቶች ፤ መፈናቀሎች፤ የጅምላ እስሮች፤ በአማራ እና ትግራይ ክልሎች አሁንም ድረስ ምላሽ ያላገኙ እና የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸው የአስተዳደር ወሰኖች ጉዳይ፤ በአማራ ክልል ብሔርተኝነት እንዲያይል እና ወደ የክልሉ ነዋሪዎች ወደ እንቢተኝነት እንዲያመሩ ማድረጉን ብዙዎች ይናገራሉ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነሐሴ 8 ቀን 2015 ዓ.ም፤ በአማራ ክልል እና እንደ አስፈላጊነቱ በተለያዩ አካባቢዎች ተግባራዊ ይሆናል የተባለዉን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአብላጫ ድምፅ አጽድቋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት - ነሐሴ 8 ቀን 2015 ዓ.ምምስል Ethiopian Press Agency

በክልሉ የከፍተኛ ባለስልጣናት ግድያን ተከትሎ፤ ከወራቶች በፊት የመከላከያ ሰራዊት፤ በክልሉ ተሰማርቷል። በሰሜን ሸዋ እና በራያ ቆቦ አካባቢዎች ከፍተኛ ግጭት ለወራቶች ተካሂደዋል። በጎጃም በደብረኤልያስ ገዳም አካባቢ በተቀሰቀሰ ግጭት ህጻናትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ተገድለዋል። ጉዳዩ ወደ ግጭት ከማምራቱ በፊት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ህዝብ ጥያቄዎቹ ይዞ ሰላማዊ ሰልፎች ሲያካሂድ መቆየቱም ይታወቃል፡፡

የአማራ ክልል ምክር ቤት ችግሩ በሰላም እንዲፈታ ዉሳኔ ቢያሳልፍም በመከላከያ እና በፋኖ ታጣቂዎች መካከል በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ግጭቶች በማየላቸዉ የክልሉ መንግስት ችግሩ ከአቅሜ በላይ ነዉ ሲል ፌደራል መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ በደብዳቤ በጠየቀዉ መሰረት መከላከያ ቢገባም፤ ግጭቱ አሁንም ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው። ከዝያም በመለጠቅ ነዉ"በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የሚታየውን በትጥቅ የተደገፈ ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴ "በመደበኛ የሕግ ማስክበር ስርዓትን ለመቆጣጠር ወደ ማይቻልበት ደረጃ የተሸጋገረ በመሆኑ" የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲደነገግ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሐምሌ 28 ቀን 2015 የወሰነዉ።"

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነሐሴ 8 ቀን 2015 ዓ.ም፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ካጸደቀ በኋላ ሰባት የመርማሪ ቦርድ አባላትንም ሰይሟል። አባላቱ፤አቶ አዝመራው አንዴሞ ሰብሳቢ፤ ወ/ሮ ነጃት ግርማ ዶ/ር ምክትል ሰብሳቢ፤ አቶ ሣዲቅ አደም አባል፤ አቶ መስፍን እርካቤ አባል፤ ዶ/ር አብርሃም በርታ አባል ወ/ሮ ፍሬህይወት ተሾመ አባል፤ አቶ ወንድሙ ግዛው ናቸዉ።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሰባት የመርማሪ ቦርድ አባላትምስል Ethiopian Press Agency

በአማራ ክልል በተቀሰቀሰዉ ጦርነት እስካሁን ቁጥሩ በዉል ያልታዎቁ ግን በርካታ ሰዎች መገደላቸዉን ነዋሪዎች እየተናገሩ ነዉ። የሃገሪቱ መከላከያ ሰራዊት እና የፋኖ ታጣቂዎች በሚደርጉት ግጭት በፍኖተ ሰላም በደረሰ የአየር ጥቃት በርካቶች ህይወት ማለፉንም የአካባቢዉ የሆስፒታል ምንጮች ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በኢትዮጵያ መንግሥት እና በአማራ ክልል ኃይላት መካከል ያለዉን ችግር ኢጋድ፤ የአፍሪቃ ህብረት፤ የተመድ ብሎም አለማቀፉ ማህበረሰብ እንዲያጠነዉ ጥይቋል። በሁለቱ ወገኖች መካከል ድርድር ለማስቻል ተቋማቱ ያስችላቸዉ ይሆን?  

በያዝነዉ ሳምንት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በአብላጫ ድምፅ ደንግጓል። በአማራ ክልል እና እንደ አስፈላጊነቱ በተለያዩ አካባቢዎች ተግባራዊ የሚሆን የተባለው ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፤ ለአማራ ክልል ብሎም ለሃገሪቱ ሰላም ያመጣ ይሆን? የአማራ ክልል የማንነት ጥያቄ፣ የወሰን ጥያቄ፣ የመልማት ጥያቄ የመልካም አስተዳደር ጥያቄን ጨምሮ ሌሎች የክልሉን ዘርፈ ብዙ ጥያቄዎችስ ይፈታ ይሆን? -በአስቸኳይ ጊዜ ሊከሰት የሚችለውን ጥሰት ለመቀነስ ምን መደረግ አለበት? አወቃቀሮቹስ ምን መሆን አለባቸዉ?  

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዴት ይገመገማል? የኢትዮጵያን ሰላም ይመልስ ይሆን?

በዉይይቱ ሃሳባቸዉን ሊያካፍሉን፤

አቶ ባይሳ ዋቆያ፤ የዓለም አቀፍ የሕግ ጉዳይ ባለሙያ

አቶ ያሬድ ኃይለማርያም፤ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል ዋና ዳይሬክተር

አቶ አዲሱ ጌታነህ፤ ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ ፤እንዲሁም

የሽዋስ አሰፋ ታዋቂ ፖለቲከኛ ናቸዉ።

ተወያዮች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በተፈጥሮዉ መብት ገዳቢ ነዉ፤ ኢትዮጵያም ተሞክሮ ይህንኑ ያሳያል። መንግሥትን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት እንዲሁም ዝም ያለዉ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ሁሉ ለሰላም ወደ ድርድር እንዲመጡ፤ ጦርነትም ይቁም ሲሉ ጥሪ አሰምተዋል። መንግሥት የጅምላ እስሩን ያቁም፤ ያሰራቸዉን ሁሉ ይልቅ ብለዋል። እርሶስ? ምን አስተያየት አሎት? 

ሙሉ ዉይይቱን የድምጽ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን!  

አዜብ ታደሰ