1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እሥር ፣ የሽብር ክስ እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተፈፃሚነት ጊዜ ማብቃት

ረቡዕ፣ ግንቦት 28 2016

በአማራ ክልል የተከሰተውን ቀውስ ተከትሎ ነሀሴ 2015 ዓ .ም ጀምሮ ከተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተያያዘ ታሥረውው የቆዩ ከ 80 በላይ ሰዎች ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡ። የሽብር ክስ የተመሰረተባቸው እነዚህ ሰዎች ዛሬ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ልደታ ምድብ ችሎት የቀረቡ ሲሆን በአዲስ አበባ እና በአዋሽ አርባ ታስረው የቆዩ ናቸው።

https://p.dw.com/p/4gfoY
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት
የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎትምስል Solomon Muchie/DW

የቤት ለቤት አሰሳው እና እስራቱ በቀጠለበት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጊዜ ሊያበቃ ነው

እሥር የሽብር ክስ እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተፈፃሚነት ጊዜ ማብቃት

በአማራ ክልል የተከሰተውን ቀውስ ተከትሎ ነሀሴ 2015 ዓ .ም  ጀምሮ ከተደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተያያዘ ታሥረውው የቆዩ ከ 80 በላይ ሰዎች ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡ።

የሽብር ክስ የተመሰረተባቸው እነዚህ ሰዎች ዛሬ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ልደታ ምድብ ችሎት የቀረቡ ሲሆን በአዲስ አበባ እና በአዋሽ አርባ ታስረው የቆዩ ናቸው።

ፍርድ ቤት ከቀረቡት ሰዎች መካከል ጋዜጠኞች፣ የሃይማኖት መሪዎች እና ፖለቲከኞች ይገኙበታል ተብሏል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተፈጻሚነት ጊዜ ማብቃቱን የገለፀው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፤ መንግሥት በእሥር የቆዩ ሰዎችን የመልቀቅ ሂደት እንዲቀጥል እና በተለያዩ አካባቢዎች የተጣሉ የእንቅስቃሴ ገደቦች እንዲነሱ፣ ሌሎች ማኅበረሰባዊ አገልግሎቶችም እንዲመለሱ ጥሪ አቅርቧል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንዲያነሳ ተጠየቀ

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያስከተለው እሥር እና እንግልት

በአማራ ክልል ነሀሴ 2015 ዓ. ም ለስድስት ወራት ተደንግጎ እንደገና ለአራት ወራት ተራዝሞ የማስፈፀሚያ ጊዜው አሁን ያበቃው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከተደነገገ ወዲህ ለብዙዎች ጠበቃ በመሆን የሚያገለግሉት ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ ዛሬ ጥዋት እና ከእኩለ ቀን በኋላ 82 ያህል ተጠርጣሪዎች ከፍተኛው ፍርድ ቤት መቅረባቸውን ገልፀዋል።

ለእሥር የተዳረጉት እነማን ናቸው ?

ከሁለት ወራት በፊት ወላጅ እናቱ በእድሜ መግፋት ምክንያት አርፈው ሀዘን ላይ የነበረ አንድ ጎልማሳ የአዲስ አበባ የኮተቤ አካባቢ ነዋሪ፣ በሁለተኛው ቀን ዘመድ ጥየቃ ከደቡብ ኢትዮጵያ የመጣ የነበረ ቤተሰባቸው በፖሊሶች ተጠርጥሮ ታስሮበት ይሄው እናቱን በሞት ያጣው ሰው ከሀዘን ላይ ተነስቶ ዘመዱን ለማስፈታት ወዲህ ወዲያ ሲል ውሎ አስፈትቶ መመለሱን ከሁለት ሳምንት በፊት አጫውቶኛል።

ይህ በአዋጅ በተለይም የፓርላማ አባላትን ጨምሮ ፖለቲከኞች ፣ ጋዜጠኞች፣ የበይነ መረብ የመገናኛ ዐውታር ሠራተኞች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች እና ሌሎችም ለእሥር የመዳርጋቸውን ሁኔታ የሚያሳይ ምሳሌ ነው።

እንዲህ ያሉ ክስተቶች እና የቤት ለቤት ፍተሻዎች ብሎም አሰሳዎች ከሰሞኑም መጠናከራቸው በተለያየ ሁኔታ እየተገለፀ ነው።

በአማራ ክልል የተራዘመው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እና አንድምታው

ከሰሞኑ ጋዜጠኛ አቤል ገብረ ኪዳን ለ 12 ቀናት ታስሮ ዛሬ ሲለቀቅ፣ ፖለቲከኛ የሺዋስ አሰፋ ትናንት ደግሞ የበጎ አድራጎት ተግባራት ላይ በመሳተፍ የምትታወቀው ሜላት ንጉሴ በፖሊስ የመታሰራቸው ነገር በስፋት ተነግሯል።

ሰሞኑን ተጠናክሯል የለተባለው እሥር እና የቤት ለቤት ፍተሻ ለምን እንደሚፈፀም የጠየቅናቸው የፌዴራል ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጄላን አብዲ "እየተጣራ" የሚያዙ ሰዎች መኖራቸውን ገልፀው ጉዳያቸው በምርመራ ላይ ስላለው ተጠርጣሩዎች ግን መናገር እንደማይችሉ ገልፀዋል።

ሕዳር 30 ቀን 2016 ዓ. ም ተጠርቶ የነበረውና ጦርነት ይቁም የሚል ዓላማ የነበረው ሰላማዊ ሰልፍ "እንደ ወንጀል ታይቷል" ሲሉ ሰሞኑን ለዶቼ ቬለ የተናገሩት የኢሕአፓ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት መጋቢ ብሉይ አብርሃም ሃይማኖት ፣ የፓርቲያቸው ሊቀ መንበርን ጨምሮ ብዙዎች መታደራቸውን ተናግረዋል።

ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ፤የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር
የተቃሙ ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ እሥርን ጨምሮ ለመብት ጥሰት ምክንያቱ ግጭት በመሆኑ መፍትሔው ግጭቶችን በሰላም ማስቆም መሆኑን ሰሞኑን ለዶቼ ቬለ ተናግረዋልምስል DW/S. Muchie

ከአዋጁ ጋር በተገናኘ ኢሰመኮ ዛሬ ያደረገው አዲስ ጥሪ 

ለተጨማሪ 4 ወራት የተራዘመው የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታ አዋጅ ተፈጻሚነት ማብቃቱን የገለፀው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን መንግሥት "በእስር የቆዩ ሰዎችን የመልቀቅ ሂደት እንዲቀጥል" አሳስቧል።

በተራዘመው የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች አስተያየት

ኮሚሽኑ ወደ መደበኛው የሕግ አተገባበር ሂደት መመለስን ጨምሮ በተለያዩ የክልል አካባቢዎች የተጣሉ የእንቅስቃሴ ገደቦች እንዲነሱ እና ሌሎች ማኅበረሰባዊ አገልግሎቶችም እንዲመለሱ ጥሪ አቅርቧል።

የተቃሙ ዋና ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ እሥርን ጨምሮ ለመብት ጥሰት ምክንያቱ ግጭት በመሆኑ መፍትሔው ግጭቶችን በሰላም ማስቆም መሆኑን ሰሞኑን ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።

የሲቪክ ድርጅቶች የመብት ይከበር ውትወታ 

የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ በጠየቀበት የባለፈው ሳምንት መግለጫው በትያትር እና ጥበብ መልኩ የሚቀርቡ ሥራዎችን የማገድ እንዲሁም የትያትር ባለሙያዎችን ለእሥር የመዳረግ እርምጃዎች በተደጋጋሚ እየተከሰቱ መሆኑን፣ ይህም እየሆነ ያለው ያለ አግባብ ከተለመደው ነገር ግን "ሕገ መንግሥታዊ ሀሳብን የመግለጽ ነፃነት ከሚጋፋው የጋዜጠኞች የዘፈቀደ እሥር ጎን ለጎን ነው" ማለቱ ይታወሳል።

ሰለሞን ሙጬ

ታምራት ዲንሳ 

ሸዋዬ ለገሰ