1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ ለሠፈሩ ስደተኞች ርዳታ

ረቡዕ፣ ጥቅምት 7 2016

ርዳታዉ ተሰርቋል ወይም ላልተፈለገ ዓላማ ዉሏል በሚል ድርጅቶቹ ርዳታ መስጠታቸዉን አቁመዉ ነበር።የኢትዮጵያ የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ኃላፊ ጠይባ ሐሰን ዛሬ እንዳሉት ከዚሕ በኋላ ርዳታዉን የሚያሰራጩት ስድስት አለም አቀፍ እና ብሔራዊ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ናቸዉ።

https://p.dw.com/p/4XhTG
ወይዘሮ ጠይባ ሐሰን ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ
የኢትዮጵያ የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ኃላፊ ጠይባ ሐሰንምስል Solomon Muchie/DW

ርዳታዉ ይቀጥላል፤ መንግስት ግን አያከፋፍልም

ኢትዮጵያ ውስጥ ለተጠለሉ ስደተኞች የሚሰጠዉ ሰብአዊ ርዳታ ሙሉ በሙሉ ከኢትዮጵያ መንግሥት ውጪ በሆኑ አካላት እንደሚሰራጭ ተነገረ።የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት (USAID )ና የአለም ምግብ ድርጅት (WFP) የሚሰጡትን ርዳታ እስካለፈዉ ዓመት አጋማሽ  ድረስ የሚያከፋፍለዉ የኢትዮጵያ መንግስት ነበር።ይሁንና ርዳታዉ ተሰርቋል ወይም ላልተፈለገ ዓላማ ዉሏል በሚል ድርጅቶቹ ርዳታ መስጠታቸዉን አቁመዉ ነበር።የኢትዮጵያ የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ኃላፊ ጠይባ ሐሰን ዛሬ እንዳሉት ከዚሕ በኋላ ርዳታዉን  የሚያሰራጩት ስድስት አለም አቀፍ እና ብሔራዊ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ናቸዉ።ወይዘሮ ጠይባ የድርጅቶቹን ስም አልጠቀሱም።ኢትዮጵያ ዉስጥ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ስደተኞች ሠፍረዋል።
በኢትዮጵያ ለተጠለሉት ስደተኞች ይቀርብ የነበረው የሰብዓዊ ድጋፍ ለስድስት ወራት ተቋርጦ ሲቆይ በረሃብ እና ያንን ተከትሎ በተከሰቱ በሽታዎች ሞት እንደነበርም የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት አስታውቃል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች "የስደተኞች እና ተፈናቃዮች ሰብዓዊ ሁኔታ እያሽቆለቆለ መምጣቱ" በእጅጉ እንዳሳሰበው ገልጾ "በስደተኞች ካምፖች ውስጥ የከፋ ሰብዓዊ ሁኔታ እና የምግብ አቅርቦት እጥረት እየጨመረ መምጣቱን" ከዚህ በፊት ባወጣው መግለጫ መጥቀሱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት
የኢትዮጵያ የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት ምስል Solomon Muchie/DW

ከዓለም አቀፍ የተራድዖ ድርጅቶች በዋናነት ከ ዩ ኤስ ኤይድ ለስደተኞች ይቀርብ የነበረው የሰብዓዊ ድጋፍ ለስድስት ወራት ተቋርጦ በመቆየቱ ኢትዮጵያ በስድስት ክልሎች ውስጥ ባሏት የመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ያሉት ስደተኞች ከካምፕ እየወጡ ለችግር እንዲጋለጡ አድርጎ ነበር። ድጋፉ አሁን የጀመረው መንግሥት ከተራድኦ ድርጅቶች ጋር በምን ተስማምቶ ነው የተባሉት የስደተኞች እና ተመላሾች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ጠይባ ሐሰን የስርጭት ሥራው በስድስት መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋሞች እንዲሰራ ስምምነት ላይ በመደረሱ ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በጋምቤላ ክልል ውስጥ ከ30 ያላነሱ ስደተኞች በረሃብና በምግብ እጦት መሞታቸውን የስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት እንደገለፀለት ከዚህ በፊት ገልፆ ነበር።በመተማ በኩል ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ ሱዳናዊያን ስደተኞች መካከል ደግሞ ዘጠኝ ያህሉ ምዕራብ ጎንደር ዞን ውስጥ በተቋቋመው የኩመር መጠለያ ጣቢያ ውስጥ በኮሌራ ወረርሽኝ መሞታቸውን የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር (UNHCR ) ከሰሞኑ አስታውቆ ነበር ። 
ለስደተኞች የምግብ እርዳታ ለስድስት ወራት ሲቋረጥ የደረሰውን የጉዳት መጠን የጠየቅናቸው ወይዘሮ ጠይባ ቁጥሩ ባይጠቅሱም በረሃብም ፣ በበሽታም የሞቱ እንደነበሩ ግን በመግለጫቸው ጠቅሰዋል። እርዳታው ሙሉ በሙሉ ሲቋረጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት ኢትዮጵያን ብለው ለመጡት ስደተኞች ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱንም ኃላፊዋ ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ በግጭት እና መሰል ችግሮች ከአገልግሎት ውጪ የሆኑትን ጨምሮ 26 የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች አሉ። ከተቋሙ ባገኘነው መረጃ  አዲስ አበባ ውስጥ ብቻ 80 ሺህ የተለያዩ ሀገራት ስደተኞች ይኖራሉ። 

የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ሕንፃ
የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንምስል Solomon Muchie/DW

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው የትጥቅ ግጭት እና ከጎረቤት ሀገራት ወደ አማራ፣ ቤንሻንጉል-ጉሙዝ፣ ጋምቤላ እና ሶማሌ ክልሎች የሚደረገው ስደት በመጠለያ ጣቢያዎች ለከፍተኛ የምግብ እጥረት መባባስ ምክንያት መሆኑን መስከረም 10 ቀን 2016 ዓ. ም ባወጣው መግለጫ ገልጿል። በጋምቤላ ክልል ያለው የጸጥታ ችግር የስደተኞችን ፈተና የበለጠ አባብሶታልም ማለቱ ይታወሳል።
ኢትዮጵያየስደተኞችና ተመላሾች አገልግሎት በእርዳታ ስርጭት ወቅት ስደተኞች የማይፈልጉት እህል እንዳይቀርብ ለረጂው አካል በተደጋጋሚ ጥያቄ ማቅረቡንና እርዳታው እንዲቋረጥ ምክንያት ሆነው ነበር በተባሉ አጥፊ ግለሰቦች ላይ እርምጃ መወሰዱን ተናግሯል። በቀጣይ ስደተኞች በዘላቂነት በሚኖሩበት መጠለያ አካባቢ በልማት ሥራ ተሰማርተው እንዲኖሩ ማድረግ ላይ ትኩረት እንደሚደረግም ገልጿል።
ኢትዮጵያ በቀጣዩ ታኅሣስ 2023 በጀኔቫ በሚካሄደው የስደተኞች ጉባኤ ላይ እንደምትሳተፍም በዛሬው መግለጫ ተገልጿል።

ሰለሞን ሙጬ 

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ