1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያን ዲጂታል የማድረግ ውጥን፡ ኢትዮ ቴሌኮም

ሐሙስ፣ መስከረም 9 2017

በ2017 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚን መሰረተ ልማት ለመዘርጋት ከአንድ ቢሊየን በላይ የአሜሪካ ዶላር መመደቡን የኢትዮ-ቴሌኮም አስታወቀ። ኩባንያው የኔተዎርክ እና ኢንተርኔት አገልግሎት ጥራት ላይም በዚህ ዓመት አተኩሮ እንደሚሠራ አሳውቋል።

https://p.dw.com/p/4krae
Frehiwot Tamiru and Ethio Telecom
ምስል Seyoum Getu/DW

ኢትዮ ቴሌኮም

 

በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ስለሚቆራረጡ የኢንተርኔትና ኔትዎርክ አገልግሎትም በዶይቼ ቬለ የተጠየቁት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ፤ ከጸጥታ ችግሮች ጋር ተያይዞ በተቋረጡ የቴሌኮም አገልግሎቶች ላይ ማብራሪያ መስጠት እንደማይችሉ በማስረዳት ለአገልግሎቱ መቋረጥ ግን ደንበኞችን ይቅርታ ጠይቀዋል። 

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ እንደሚሉት የኩባንው የዘንድሮ 2017 ዓ.ም. በጀት ዓመት ከዚህ በፊት ኩባንያው ያስቀመጠው የሦስት ዓመታት ስልታዊ እቅድ የሚጠናቅበት ነው። በተያዘው ዓመት ከወቅታዊው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር እቅዱን ገምግሞ ማየቱን ያሳወቀው ኩባንያው የዓመቱ የኩባንያው እቅድ የኢትዮጵያ የኮሚዩኒኬሽን እና የዲጅታል መፍትሄ መሪ አቅራቢ ሆኖ መቀጠል የሚስችለውን ሥራ መሥራትም ነው ተብሏል።

ኩባንያ ከኔትዎርክ መቆራረጥ ጋር ተያይዞ ደንበኞች በስፋት የሚያነሱትን ጥያቄ እልባት ለመስጠት በዓመቱ በኔትዎርክ እና ዲጂታል መሰረተ ልማት ግንባታ ላይ አተኩሮ እንደሚሠራም ነው የጠቆመው።  የኩባንያው ሥራ አስፈጻሚዋ ፍሬሕይወት ታምሩ እንደሚሉትም «አገርን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ማድረግ የሚያስችል የቴሌኮም ቴክኖሎጂ ፈጠራን የሚያበረታቱ የዲጂታል መሰረተ ልማት ላይ በትኩረት ይሠራል» ነው ያሉት። በተለይም የኔትዎርክ-ኢንተርኔት ማስፋፊያው እቅድ ከነበረው አቅም በ15 በመቶ የማሳደግ ነው ተብሏልም።

ትኩረት የተሰጠው የዲጂታል ቴሌኮም መሰረተ ልማት ግንባታ

የሚገነቡ የቴሌኮም ዲጂታል መሰረተ ልማቶች በዋናነት ኢኮኖሚውን የማነቃቃትና ዲጂታል ኢኮኖሚውን ለመርዳት የወጠነ ነው ያሉት ሥራ አስፈጻሚዋ፤ ከዚህ በፊት የተገነቡ መሰል መሰረተ ልማቶችን ማጠናከር እና አሁን ያለውን የቴሌኮም ሽፋን ማሻሻል በዓመቱ እቅድ ትኩረት የተሰጠውም ነው ሲሉ አብራርተዋል።

«የዋይፍአይ አገልግሎት ለማጠናከር በመላ ሀገሪቱ 1,298 የሞባይል ኔትወርክ ጣቢያዎችን ይገነባሉ» ያሉት ኃላፊዋ በ500 ከተሞች የ4ጂ እንዲሁም በ15 ከተሞች የ5ጂ አገልግሎቶችን ለማስጀመርም እቅድ ተነድፏል ብለዋል። አዳዲስ የፋይበር ዝርጋታ ሥራ እና ነባሮችን የመጠገን ተግባርም በማከናወን በተለይም የኢንተርነት ዓለም አቀፍ አቅሙንም በ25 በመቶ ለማሳደግ ማቀዱን ኩባንያው አሳውቋል።

ኩባንያው ዲጂታል ኢኮኖሚን በኢትዮጵያ እውን ለማድረግ በበጀት ዓመቱ የቴሌኮም እና የዲጂታል መሰረተ ልማት ማስፋፊያዎችን ለማከናወን ከአንድ ቢሊየን በላይ የአሜሪካ ዶላር መመደቡንም ነው ያሳወቀው። ኩባንያው አቅርቦትን ለማረጋገጥ ያስችለናል ያለውን ከ1.1 ሚሊየን በላይ የቴሌኮምና ዲጂታል አገልግሎት መስጫ መሳሪያዎች (devices) ለግለሰብ እና ድርጅት ደንበኞቹ ለማቅረብ ስለማቀዱም ይታወቅልኝ ብሏል። «የዲጂታል ኢትዮጵያ እና ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ በቴሌኮምና በዲጂታል መሰረተ ልማት ላይ ተመስርቶ ዘላቂ እንዲሆን ሰፊ ማስፋፊ እናደርጋለንም» ያሉት ፍሬሕይወት ከአንድ ቢሊየን ዶላር የላቀ ገንዝብ መመደቡን አስረድተዋል።

የኢትዮ ቴሌኮም  ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩ
የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬሕይወት ታምሩምስል Seyoum Getu/DW

ኩባንያችን ግዙፍ የዲጂታል መሰረተ ልማት ግንባታ በማከናወን የድርጅት ደንበኞችን አሠራር የሚያዘምኑ የክላውድ እና ኤጅ ኮምፒውቲንግ፣ አይኦቲ (IoT) የመረጃ እና የጥሪ ማዕከል፣ የይዘት፣ የዲጂታል ግብርና፣ ጤና፣ ትምህርት፣ ስማርት ከተማ የመሳሰሉትን የዲጂታል ሶሉሽኖች በስፋት ለማቅረብም እሠራለሁ ነው ያለው።

የኩባንያው የገቢ እቅድ

በዓመቱ ፈጣን ያለውን አገልግሎት በማስፋፋት ከ163 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ለማግኘት ማቀዱን ነው የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ያስታወቁት። «ለዚህም የደንበኞቻችንን ቁጥር ከ78 ሚሊየን ወደ 83 ሚሊየን ከፍ የማድረግ እቅድ ይዘናል» ያሉት ፍሬሕይወት ተጨማሪ አምስት ሚሊየን ደንበኞችን በማፍራት ገቢውን በተጨማሪ 6 በመቶ ለመጨመር መታሰቡን አስረድተዋል።

ኩባንያው በአገር ውስጥ ከሚሠራው ሥራ በተጨማሪ ከአገር ውጪ በሚከውናቸው ተግባራትም ባለፈው በጀት ዓመት ያሳካውን የ198 ሚሊየን ዶላር ገቢ ዘንድሮ ወደ ከ282 ሚሊየን ዶላር በላይ ለመሰብሰብም አቅዷል። ይህም በዚህ ዓመት የተዘረጋው የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር በመሆኑ ተጨማሪ 84 ሚሊየን ዶላር ከውጪ ደንበኞቹ እንደሚሰበስብ አሳውቋል። ኢትዮ ቴሌኮም ገጠሪቱን ኢትዮጵያ በኔትዎርክ ለማገናኘትም በዚህ ዓመት በትኩረት እሠራለሁ ነው ያለው።

የኩባንያው የገቢ እቅድ
የኩባንያው የገቢ እቅድምስል Seyoum Getu/DW

የጸጥታ ተግዳሮት በተለኮም አገልግሎት

በተለያዩ አከባቢዎችበኔትዎርክ መደበኛ መቆራረጥ የሚቸገሩ ደንበኞች መኖራቸውን በተለያዩ አጋጣሚዎች ይነሳል። ለአብነትም ከሰሜን ሸዋ ዞን ፊቼ ከተማ ወደ አዲስ አበባ መምጣታቸውን አንስተው አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ ግለሰብ ላለፉት ሁለት ሳምንታት ገደማ የስልክ አገልግሎት ተቋርጧል ብለዋል።

የዚህን አካባቢ ስልክ መቋረጥ መንስኤ እና በተለያዩ ጊዜያት ስለሚቆረጠው የኔትዎርክ አገልግሎት እንዲሁም ግጭት ባለባቸው የአገሪቱ አካባቢዎች በኔትዎርክ እና ኢንተርኔት አገልግሎት መቆራረጥ ኩባንያው ላይ ስለደረሰው ጉዳት ከዶቼ ቬለ ማብራሪያ የተጠየቁት የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ፤ የችግሩን መኖር አረጋግጠው ዝርዝር ማብራሪያ ከመስጠት ግን ተቆጥበዋል። ያም ሆኖ ግን ኩባንያቸው አገልግሎቱ የተቋረጠባቸውን ደንበኞቻቸውን ይቅርታ እንደሚጠይቅም አሳውቀዋል።

ሥዩም ጌቱ

ሸዋዬ ለገሠ

ፀሐይ ጫኔ