አቶ ሽመልስ አብዲሳ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጡ
ቅዳሜ፣ ጳጉሜን 2 2011የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ክልሉ በአመቱ ያከናወናቸውን ስራዎች አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ሰፊ ውይይት መደረጉንና ውጤት መገኘቱን አመልክተዋል።
በክልሉ በአቶ ዳውድ ኢብሳ ይመራ የነበረው የኦነግ ሰራዊት ጋር ተያይዞ አሳዛኝ ሁኔታዎች ተፈጥረው እንደነበር ገልጸዋል።
ሰላምና ጸጥታን ለማስጠበቅም በምዕራብና ደቡብ ኦሮሚያ ይንቀሳቀስ የነበረው ይሄው ሃይል በሰላም ወደ ቀያቸው እንዲመለስ በሃገር ሽማግሌዎችና በአባገዳዎች በተሰራው ስራ ውጤት ተገኝቷል ብለዋል።
ከዚህ ውጭ የሆነውን ሃይል ግን አቶ ዳውድ ኢብሳ ቡድኑ እኛ የምንመራው ሀይል አይደለም የ ሽፍታ ቡድን ነው ብሎ ወስኗል ያንን ውሳኔ ማዕከል በማድረግም ህግን የማስከበር ስራ ተሰርቷል ብለዋል።
ይህ ስራበመሰራቱም አሁን ላይ ሁሉም መንገዶች ክፍት መሆናቸውን ፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መጀመሩን ፣ሰው ተረጋግቶ መኖር የጀመረበት ከፍተኛ ለውጥ መጥቷል ብለዋል።
የህዝቦች መፈናቀልን ለማስቆም በተሰራው ስራም ብዙ ለውጥ መምጣቱንና በአጥፊዎች ላይም ህጋዊ እርምጃ ተወስዷል ነው ያሉት። ከክልሎች ጋር ያለን ግንኙነት በማጠናከርም የፌዴራል ስርአቱን ይልማጠናከር ስራ ተከናውኗል ብለዋል።
በአመቱ ከፍ ያለ አስተሳሰብ ያለውና የገዳ ስርአትን መሰረት ያደረገ ትውልድ ለመገንባት " ተጃጅለ ለሙማ " የተባለ የዜግነት ጉዳይ የተጀመረበት አመት መሆኑን አመልክተዋል።
የኦሮምኛ ቋንቋ የፌደራል የስራ ቋንቋ እንዲሆንም እየተሰራ ነው ያሉት ምክትል ርእሰ መስተዳድሩ የፌዴራል ስርአቱን አማርኛን ብቻ የስራ ቋንቋ በማድረግ እንዲሁም ኦሮምኛንም በመጨመር ብቻ ማጠናከር አይቻልም ብዙ ስለሆንን ብዙ የስራ ቋንቋ ያስፈልገናል ብለዋል።
የሰሞኑን የኦሮምያ ቤተ ክህነት የማቋቋም ጥያቄ ተከትሎ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ መሪዎች ጋር ስለነበራቸው ውይይት ሲናገሩ በህገ መንግስቱ ሀይማኖት እና መንግስት የተለያዩ በመሆናቸው ሌሎች ነገሮችን የመወሰን ስልጣን የለንም ብለዋል። በመሆኑም ልዩነቶች በውይይት እንዲፈቱ ምክረ ሀሳብ ሰጥተናል እንጅ መደራጀት አለበት የለበትም በሚለው ዙሪያ ሀሳብ የመስጠት ሀላፊነትም ስልጣንም የለንም ብለዋል።
ሰለሞን ሙጬ
እሸቴ በቀለ