1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አሰብ ደርሶ መልስ

ረቡዕ፣ መስከረም 2 2011

ሰባት የመርከብ መቆሚያዎች ያሉት የአሰብ ወደብ ኢትዮጵያ ከምትገለገልበት ጅቡቲም ይሁን ሽርክና ከገባችበት በርበራ በተሻለ ቅርበት ላይ ቢገኝም ለሁለት አስርት አመታት ሥራ ፈቶ ቆይቷል። ከ6-20 ቶን ማንቀሳቀስ የሚችሉ 18 ቋሚና ሰባት ተንቀሳቃሽ የዕቃ መጫኛና ማውረጃ ክሬኖች፣ 280 ሺህ ቶን ዕቃ ማስቀመጥ የሚችል ቦታም አለው።

https://p.dw.com/p/34mCf
Somaliland Reportage alter Hafen in Berbera
ምስል DW/J. Jeffrey

አሰብ ደርሶ መልስ

መስከረም አንድ ብሎ ሲጠባ ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ ከአዲስ አበባ የአፋር ክልሉ ነዋሪ ከቡሬ ተነስተው ወደ አሰብ አቀኑ። "ጠቅላይ ምኒስትሩ በሔሊኮፕተር ሲጓዙ እኛ በመኪና በምድር ተከተልናቸው። አሰብ ገብተን የተዘጋጀልንን የምሳ ፕሮግራም ታደምን። አሰብን ዞረን አየን። ባሕርም ዋኘን። ከቀኑ ስምንት ሰዓት ሲሆን ተመልሰን ወጣን" የሚሉት የቡሬው ነዋሪ "እደሩ" የሚል ግብዣ ቀርቦላቸው ነበር።

በደቡባዊ ኤርትራ ከጅቡቲ ድንበር በ55 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው አሰብ እንዲህ እንደዛሬ ጊዜ ሳይጥለው ሥራ ከሚበዛባቸው የአፍሪቃ ቀንድ ወደቦች መካከል አንዱ ነበር። በወታደራዊ እና የስለላ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ የሚሰራው ግሎባል ሰኪዩሪቲ የተባለ ተቋም በድረ-ገፁ እንዳሰፈረው በጎርጎሮሳዊው 1988 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ሰባ በመቶ የገቢ እና ወጪ ንግዷን የከወነችው በአሰብ ወደብ በኩል ነበር። በጎርጎሮሳዊው 1986/87 የበጀት አመት መጨረሻ ከ2.8 ሚሊዮን ቶን በላይ የደረቅ ጭነት በአሰብ በኩል ተንቀሳቅሷል። ከዚህ ውስጥ 66 በመቶው ወደ ኢትዮጵያ የሚገባ ሸቀጥ 792 ሺሕ ቶን ደግሞ በወደቡ ለሚገኝ ማጣሪያ የታለመ ድፍድፍ ነዳጅ እንደነበር ይኸው ድረ-ገፅ ያትታል።

ኤርትራ እንደ አገር ስትቆም ኢትዮጵያ የአሰብ ወደብን ያለ ክፍያ እና ያለ ገደብ እንድትጠቀም ሁለቱ መንግሥታት ስምምነት ነበራቸው። የዓለም አቀፍ ወቅታዊ ጉዳዮች ጥናት ማዕከል (The Institute of Current World Affairs) ተመራማሪው ማርክ ሚካኤልሰን እንደፃፉት በወቅቱ ከወደቡ ሥራ 95 በመቶው ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ አሊያም ከኢትዮጵያ የሚወጡ ሸቀጦችን ማስተናገድ ነበር። የጨው አምራች እና የነዳጅ ማጣሪያ ሰራተኞች ኅልውናም መቶ በመቶ በኢትዮጵያ ገበያ ላይ ጥገኛ ነበር። 

የጭነት ማመላለሻ መኪኖች አሽከርካሪዎች፣ የመርከብ ሰራተኞች፣ እና ነጋዴዎች የሚያዘወትሯት አሰብ ሞቅ ደመቅ ያለች ነበረች። ግንቦት 1990 ዓ.ም. ደርሶ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ወዳጅነት ሲቀዛቀዝ ግን አሰብም ወደ ሥራ ፈትነት አዘነበለ። ወይም የወደብ እንቅስቃሴው እጅጉን ተዳከመ። የቡሬው ነዋሪ መስከረም አንድ ቀን 2011 ዓ.ም. አሰብ ሲደርሱ ያገኙት "ሰው የናፈቀው ከተማ" ነበር። "ከተማው ሰው የናፈቀው መሆኑ ነው የሚያስታውቀው። ነዋሪዎቹም ሰው ናፍቋቸዋል። እኛ መጀመሪያ ስንገባ አንዲት ትልቅ አዛውንት አስቆመችን እና ሰንደቅ ዓላማ ሰጠናት። ከዚያ መሬት ተደፍታ አለቀሰች። እንዳለ መኪናው ላይ የነበረው ሰው እሷን ተከትሎ ለቅሶ በለቅሶ ሆነ" ሲሉ የተመለከቱትን ተናግረዋል።

ለቡሬው ነዋሪ ከጥቂት ጊዜያት በፊት ድንበር እና የወታደር ምሽግ ተሻግሮ አሰብ መጓዝ የሚሞከር ቀርቶ የሚታሰብ አልነበረም። ላለፉት ሁለት አስርት አመታት የቡሬ አካባቢን ጨምሮ ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የሚጎራበቱባቸው የድንበር አካባቢዎች በከፍተኛ ወታደራዊ ጥበቃ ሥር በመውደቃቸው እንቅስቃሴ ተዳቆ ቆይቷል። እንደ አሰብ ሁሉ ትንሺቱ ቡሬ የነበራት እንቅስቃሴ እና የነዋሪዎቿ ተስፋ በጦርነቱ ተዳፍኗል።

አሰብ ደርሰው የተመለሱት ግለሰብ "የቡሬ ከተማ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ምክንያት በሰው ልጅ ላይ የደረሰ ጉዳት አለ። በንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት አለ። ጦርነቱ ካለቀ በኋላ ደግሞ በኤኮኖሚውም ሆነ በኑሮ ደረጃ በጣም አስከፊ ኑሮ ውስጥ የነበረ ሕዝብ ነው። ገጠር ያለው ማኅበረሰብ ወደ ምሽግ አትሒድ ተብሎ ሲደበደብ ነበር። ከተማ ያለው ማኅበረሰብ ደግሞ የመንግሥት ተረጂ ሆኖ፣ ከመንግሥት የሚጠብቅበት ምንም አይነት እንቅስቃሴ የለም። ልንቀሳቀስ ያለ የኤርትራ መረጃ ነህ እየተባለ በብዙ ጫና እና በመከራ መሐል ያለፈ ሕዝብ ነው" ሲሉ አስረድተዋል። 

ከኢትዮጵያ እና ኤርትራ ደም አፋሳሽ ጦርነት በኋላ ሁለቱ አገሮች በሚዋሰኑበት የድንበር አካባቢ ለሁለት አመታት የዘለቀው ውጥረት የከፋ ተፅዕኖ አሳድሮ ቆይቷል። በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳንይንስ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ረዳት ፕሮፌሰሩ አቶ መረሳ መሳይ «ቤተሰብ ተበትኗል፤ ወንድማማቾች ለ20 አመታት ተለያይተዋል። ለ20 አመታት በመለያየታቸው የስነ-ልቦና ቀውስ አጋጥሟል። የኤኮኖሚ ቀውስ አጋጥሟል። ኤርትራውያን ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣት እስከ ዓለም ስደት እና የሲና በረሐ ተጠቂዎች ሆነዋል። የሰሜን ዕዝ እና የመካከለኛው ዕዝ ትግራይ ነው ያለው። ወታደር ድንበር ለመጠበቅ አስፈላጊ ቢሆንም ትግራይ ከኢንቨስትመንት ውጪ ሆናለች። የአማራ ክልል፣ የትግራይ ክልል፣ የአፋር ክልል እነዚህ ከዓለም ኤኮኖሚ በጣም ርቀዋል» ሲሉ ጫናውን ይገልጹታል። 

ከኤርትራ ድንበር 15 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ የምትገኘው ቡሬ የከተማ መልክ ይኑራት እንጂ የነዋሪዎቿ ቁጥር ከአምስት ሺህ አይበልጥም። አንድ ጤና ጣቢያ እና አንድ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አላት። ነዋሪዎቿ የተሻለ ሕክምና ካሻቸው ሁለት መቶ ገደማ ኪሎ ሜትር አቋርጠው ዱብቲ መሔድ አለባቸው። ስምንተኛ ክፍል ያጠናቀቁ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የሚፈልጉ ወጣቶች ወደ ኤልደአር ወረዳ ያቀናሉ። የቡሬው ነዋሪ እንደሚሉት የከተማዋ እንቅስቃሴ የተፋዘዘ ሆኗል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የአሰብ ወደብን ለመጠቀም ፍላጎት ካሳየ በኋላ በቡሬ አቋርጦ ወደ ኤርትራ የሚያመራው መንገድ ነፍስ ይዘራ ጀምሯል። የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ሳምሶን ወንድሙ ከዲቼቶ እስከ ጋላፊ 40 ኪሎ ሜትር መንገድ እየተገነባ መሆኑን ገልጸዋል። ኃላፊው ነባሩ መንገድ አሁን ባለው ይዞታው አገልግሎት ሊሰጥ ቢችልም ጥገና የሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ የኤርትራን ወደቦች ለመጠቀም ዝግጁ መሆኗን ብትገልጽም በትክክል መቼ እንደሁ ግን የሚታወቅ ነገር የለም። ጠቅላይ ምኒስትር አብይ አሕመድ የምፅዋ ወደብን በጎበኙ ወቅት መቐለ የሚል መጠሪያ የተሰጣት የኢትዮጵያ እቃ ጫኝ መርከብ ከሁለት አስርት አመታት በኋላ የኤርትራን ሸቀጥ ለመጫን ከምፅዋ ወደብ ደርሳለች። መርከቧ ምፅዋ የደረሰችው ቢሻ ተብሎ ከሚታወቀው የኤርትራ የማዕድን ማውጫ ሥፍራ የተመረተ ዚንክ ወደ ቻይና ለማድረስ ነበር። የኤርትራው የማስታወቂያ ምኒስትር አቶ የማነ ገብረመስቀል በትዊተር ገፃቸው እንዳሰፈሩት መርከቧ የዚንክ ምርቱን ለመጫን የተደረገውን ውድድር አሸንፋ ነው ከምፅዋ ወደብ የደረሰችው።

ከጅቡቲ የወደብ ጥገኝነት ለመላቀቅ በበርበራ የወደብ ልማት ሽርክና ለገባችው ኢትዮጵያ አሰብ የተሻለ ቅርበት አለው። የተባበሩት መንግሥታት የንግድ እና ልማት መሥሪያ ቤት ያዘጋጀው ሰነድ እንደሚጠቁመው የአሰብ ወደብ ሰባት የመርከብ መቆሚያዎች አሉት። ወደቡ ከስድስት እስከ 20 ቶን ማንቀሳቀስ የሚችሉ 18 ቋሚ እና ሰባት ተንቀሳቃሽ የዕቃ መጫኛ እና ማውረጃ ክሬኖች፣ 280 ሺህ ቶን ዕቃ ማስቀመጥ የሚችል ቦታም ተዘጋጅቶለታል።

የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ አሮባ መገርሳ  በአካባቢው ሊጓጓዝ የሚችለውን የዕቃ መጠን እና አይነት ለመለየት ዝግጅት መጀመሩን ለጋዜጠኞች ተናግረዋል። አቶ አሮባ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ሸቀጦችን የሚያጓጉዙ መርከቦች ሥምሪት ዕቅድ እንደሚዘጋጅም ጠቁመዋል። የኤርትራ ባሕር ትራንስፖርት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን አበራ ኢትዮጵያ የአገራቸውን ወደቦች መጠቀም መጀመሯ ለሁለቱም አገሮች የሚበጅ ጥቅም ይዞ እንደሚመጣ ዕምነታቸውን ተናግረዋል። አቶ መኮንን ቡሬን አልፎ ወደ አሰብ የሚጓዘውን መንገድ ይዞታ ከጎበኙ በኋላ «መርከብ ይመጣል፤ መርከበኞች ይመጣሉ፤ መኪና ይመጣል ሾፌሮች ይመጣሉ፤ አስመጪዎች ይመጣሉ፤ ላኪዎች ይመጣሉ። ስለዚህ ሕዝብ ለሕዝብ ለኤኮኖሚም ግንኙነት እና ትስስርም እንደ ወደብ አጠቃቀም ያክል ሁለቱንም ሊያጣብቅ የሚችል ነገር የለም» ሲሉ ለኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ተናግረዋል። መስከረም አንድ ምሽግ ፈርሶ መንገድ ሲከፈት የተመለከቱት የቡሬ ነዋሪ ኢትዮጵያ የኤርትራን ወደቦች መገልገል ከጀመረች የእርሳቸው እና የአካባቢያቸው እንቅስቃሴ ይለወጣል የሚል ተስፋ አላቸው።

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ