1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አማራጭ የገቢ ለመፈለግ የተገደዱት የዎላይታ መንግሥት ሠራተኞች

ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ረቡዕ፣ ነሐሴ 29 2016

ሠራተኛው ቤተሰቡን ለማስተዳደር ሲል ከድለላ ጀምሮ እስከ ጉልበት ሥራ ያገኘውን ሁሉ እንደሚሰራ የጠቀሱት አስተያየት ሰጭው“በልተን ማደር አለብን በሚል ወደ ቢሮ አይገቡም፤፡በአንዳንድ መ/ቤቶች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ሠራተኞች አይታዩም።ቁጭ ብለን ከምንሞት ብለው ቢሮ ዘግተው ወደ ገጠርና ሌሎች አካባቢዎች ሄደዋል “ ብለዋል ፡፡

https://p.dw.com/p/4kHE3
Äthiopien Wolaita Sodo city
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

አማራጭ ገቢ ምንጭ ለመፈለግ የተገደዱት የዎላይታ መንግሥት ሠራተኞች

አቶ ታደሰ ሻንካ በዎላይታ ዞን ዳሞት ወይዴ ወረዳ ላለፉት 26 ዓመታት በወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት በድጋፍ ሰጪ ሠራተኛነት ሲያገለግሉ መቆየታቸውን ይናገራሉ ፡፡ “ የሚከፈለኝ  ደሞዝ አሁን ካለው የኑሮ ሁኔታ ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ነው “ የሚሉት አቶ ታደሰ  “ እሱንም ቢሆን በወቅቱ ማግኘት አስቸጋሪ ነው ፡፡ በዚህም የተነሳ ከአምስት ቤተሰቦቼ ጋር ችግር ውስጥ እገኛለሁ ፡፡ ቤተሰቦቼን ለመመገብ ለጊዜው የመንግሥት ሥራውን በመተውና ወደ ገጠር በመግባት የጉልበት ሥራን አማራጭ አድርጌ እየሠራሁ እገኛለሁ “” ብለዋል ፡፡

ነዋሪዎችን ቅር ያሰኘው በዎላይታ ዞን ለመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ መክፈያ በሚል ለግለሰቦች ተሽጧል የተባለው ጥብቅ ደን ጉዳይ


በዚሁ የወላይታ ዞን የኪንዶ ኮይሻ ወረዳ የመንግሥት ሠራተኛ የሆኑት ደምሴ ቶጋ በወረዳው ለሦስት ወራትና ከዚያ በላይ ደሞዝ ሳይከፈል እንደሚቆይ ይናገራሉ ፡፡ ደሞዝ ቢከፈልም በመቶኛ ተሰልቶ በግማሽና ከዚያ በታች እንደሚደርሳቸው የጠቀሱት ደምሴ “ አሁን ላይ እኔን ጨምሮ አብዛኛው የመንግሥት ሠራተኛ አማራጭ ኑሮ ለመፈለግ ተገዷል ፡፡ እኔም የቤተሰቤን ረሀብ  ለማስታገስ ስል ገጠር ገብቼ ካዛቫ መትከል ጀምሪያለሁ ” ብለዋል ፡፡

በመንግሥት ተቋማት ላይ ያሳደረው ተፅእኖ

በዎላይታ ዞን በሚገኙ 17 ወረዳዎች የሠራተኞች ደሞዝ ክፍያ አለመፈጸም የጤና ተቋማትን ጨምሮ በመንግሥት አገልግሎት ሰጪ መሥሪያቤቶች ላይ ተፅእኖ እያሳደረ ይገኛል  ፡፡ አሁን ላይ  አብዛኛው ሠራተኛ ተስፋ በመቁረጥ በሥራ ገበታው ላይ እንደማይገኝ የሚናገሩት አስተያየት ሰጪዎች በዚህም የተነሳ አንዳንድ መሥሪያቤቶች በከፊል ሌሎቹ  ደግሞ ሙሉ በሙሉ ተዘግተዋል  ብለዋል፡፡

የዎላይታ ዞን የመንግሥት ሠራተኞች የደሞዝ ጥያቄ አልተመለሰም


 “ ሠራተኛው ቤተሰቡን ለማስተዳደር ሲል ከድለላ ጀምሮ እስከ ጉልበት ሥራ ያገኘውን ሁሉ እየሰራ እንደሚገኝ የጠቀሱት አስተያየት ሰጪዎቹ “ በልተን ማደር አለብን በሚል ወደ ቢሮ አይገቡም ፡፡ በዚህም ምክንያት አንዳንድ መሥሪያቤቶች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ሠራተኞች አይስተዋልባቸውም ፡፡ ምክንያቱም ቁጭ ብለን ከምንሞት ብለው ቢሮ ዘግተው ወደ ገጠርና ሌሎች አካባቢዎች ሄደዋል “ ብለዋል ፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አርማ
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አርማምስል Ethiopian Human Rights Commission

የኢሰመኮ ምክረ ሀሳብ

ነዋሪዎችን ቅር ያሰኘው በዎላይታ ዞን ለመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ መክፈያ በሚል ለግለሰቦች ተሽጧል የተባለው ጥብቅ ደን ጉዳይ

ዶቼ ቬለ በደሞዝ አለመከፈልና መዘግየት ዙሪያ የወላይታ ዞንንም ሆነ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የሥራ ሃላፊዎችን ምላሽ ለማካተት ያደረገው ጥረት አልተሳካም ፡፡ ያም ሆኖ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በያዝነው ሳምንት ባወጣው መግለጫ በደቡብ ኢትዮጵያ እና በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች የደመወዝ መዘግየትና ያለመክፈል በመንግሥት ሠራተኞች ላይ ማህበራዊ ፣ ኢኮኖሚያዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት እያደረሰ ይገኛል ብሏል ፡፡  ኮሚሽኑ  በክልሎች አደረኩት ባለው ምርመራ አዳዲስ አስተዳደር መዋቅሮች መከፈትና መስፋት እንዲሁም የአፈር ማዳበሪያ ዕዳ ለደሞዝ  አለመከፈል ቀዳሚ ምክንያት መሆናቸው በምርመራ ሪፖርቱ ጠቅሷል ፡፡ ክልሎቹ የገቢ አሰባሰብ አቅማቸውን በማሳደግ ፣ ማዳበሪያ ዕዳን በማራዘምና አቅምን ያገናዘበ የሰራተኞች መዋቅር መዘርጋትን ጨምሮ ሌሎች አማራጭ መፍትሄዎችን እንዲያፈላልጉ  አሳስቧል ፡፡


ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ኂሩት መለሰ
እሸቴ በቀለ