አማራ ክልል በረሀብ ሰዎች መሞታቸውን ተፈናቃዮች ተናገሩ
ማክሰኞ፣ የካቲት 26 2016በአማራ ክልል፤ ደቡብ ወሎ ዞን፤ ተሁለደሬ ወረዳ፤ «ቱርክ» በተባለ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ የሚገኙተፈናቃዮች «ለከፍተኛ ረሀብ ተጋልጠናል» አሉ ። በረሀብ ሰዎች መሞታቸውንም ተፈናቃይ አስተያየት ሰጪዎች ለዶይቸ ቬለ (DW) አመልክተዋል ። የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት በበኩሉ፦ «በረሀብ ምክንያት ‘ተፈናቃይ ሞቷል' የሚባለው ሀሰት ነው» ሲል ምላሽ ሰጥቷል ። በቅርቡ ተቋረጠ ያለው ርዳታም ሁኔታዎች ሲሻሻሉ እንደሚሰጥ ጽ/ቤቱ አክሏል ።
«በምግብ እጥረት ሰዎች እየሞቱ ነው ።» ተፈናቃዮች
በለፉት 4 እና 5 ዓመታት በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ውስጥ በነበሩ ግጭቶች ምክንያት በአካባቢው ይኖሩ የነበሩ በርካታ የአማራ ተወላጆች ከነበሩባቸው ቀዬዎች ተፈናቅለው በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በመጠለያ ጣቢያዎችና ከኅብረተሰቡ ጋር ተቀላቅለው ይኖራሉ ። ተፈናቃዮቹ እንደሚሉት በአደጉባቸው የኦሮሚያና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ዞኖች በነበሩ ግጭቶች ብዙዎች ተገድለዋል ፤ ሌሎች ደግሞ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ ከሞት ያመለጡት ደግሞ «ቤት ንብረቴን» ሳይሉ መፈናቀላቸውን ነው የሚናገሩት ። ተፈናቅለው ወደመጡበት አካባቢም በቂ ርዳታ እንደማያገኙ አንዳንዶቹ ይገልፃሉ ።
በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ተሁለደሬ ወረዳ «ቱርክ» በተባለ መጠለያ ጣቢያ ከሚገኙ ተፈናቃዮች መካከል አንዱ በመጠለያ ጣቢያው ያለውን የምግብ እጥረት በተመለከተ ለዶይቼ ቬለ በስልክ ሲገልፁ፦ «... ነሐሴ 25 ቀን፣ 2015 ዓ.ም ላይ ነበር ቦቆሎ፣ ጥሬና ሽርክት (ዶቄት መሰል ነገር) የተሰጠነው፣ ከነሐሴ ጀምሮ እስካሁን የምግብ ድጋፍ የሚባል ነገር የለም ። ባለፈው ዓመት በረሀብ 7 ያህል ሰዎች ሞተዋል፣ ስም ዝርዝራቸውን ካስፈለገ ማቅረብ ይቻላል፣ በቅርቡ ደግሞ አንድ ህፃንን ጨምሮ 3 ሰዎች ሞተዋል፣ ሁሉም በረሀብ ነው የሞቱት፣ አሁን ደግሞ ቢያንስ እስከ 18 የሚደርሱ ሰዎች ምንም ነገር፣ እህል ውኃ የማይሉ በአስጊ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ ። እዚህ ቱርክ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ ።»
«ምግብ የለም ልጆቻችን እየተሰቃዩብን እየተጎዱብን ነው ።» ተፈናቃይ
ከምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ወረዳ እንደተፈናቀሉ የሚገልፁትና የ5 ቤተሰብ አስተዳዳሪ የሆኑ እናት በበኩላቸው ከነሐሴ 2015 ዓ.ም ጀምሮ ርዳታ በመቋረጡ እስከልመና መውጣታቸውን ያስረዳሉ ፡፡
«በ2014 ዓ.ም ከኦሮሚያ ክልል ምእራብ ወለጋ ዞን ተፈናቀልሁ ። አሁን ያለንበት ሁኔታ አስቸጋሪ ነው ። ምግብ የለም ልጆቻችን እየተሰቃዩብን እየተጎዱብን ነው ። እየለመንን ነው የነበርነው ። ኅብረተሰቡ እየሰለቸ በመምጣቱ ልመናውንም እየተውነው ነው ። ልጆቻችን እጅግ ተርበዋል። ውኃ ውኃ ይሉናል፤ ሲጠጡት ደግሞ ያማቸዋል ። [ከንፅህና ጉድለት አንፃር]የምግብ ጉዳይ በጣም አስቸጋሪ ሆኖብናል ። ጭንቅ ላይ ነው ያለነው ። ርዳታ ከወሰድሁ 3 ወራት አልፈዋል ።»
ሌላ ተፈናቃም በመጠለያ ጣቢያው «የሚላስ የሚቀመስ» እንደሌለ ነው የሚናገሩት ። የመንግስት አካላትን የምግብ ርዳታ ሲጠየቁ ጠብቁ እንደሚባሉ የገለፁልን እኚህ አስተያየት ሰጪ ሰዎችም በረሀብ እየሞቱ እንደሆነ አስረድተዋል ።
«ተፈናቃይ በረሀብ ሞቷል» የሚባለው አሉባልታ ነው፦ የአካባቢው ባለሥልጣን
የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አሊ ሰኢድ ጉዳዩን በተመለከተ ለዶይቼ ቬሌ በሰጡት ምላሽ፦ «አንዳንድ የማይመቹ» ባሏቸው ምክንቶች በቅርቡ ርዳታ ወደ አካባቢው እንዳልሄደ ጠቅሰው፤ ሁኔታዎች ሲመቻቹ ርዳታው ይደርስላቸዋል ነው ያሉት ።
«ርዳታ የሚለግስ አካል ሰላሙ የተረጋገጠ ሲሆን ነው የሚሰጥህ ። እዚህ አካባቢ ደግሞ አልፎ አልፎ የማይመቹ ነገሮች አሉ ። በአጋጣሚ ለእነኚህ ተፈናቃየች ርዳታ ተገኝቷል ። ለሌላው ደግሞ እየጠየቅን ነው ። ሁኔታው ሲመቻች ርዳታው ይላክላቻዋል» ብለዋል ።
«ተፈናቃይ በረሀብ ሞቷል» የሚባለው ግን አሉባልታ እንጂ ተጨባጭ መረጃ የለም ሲሉ ስሞታው «ሀሰት» መሆኑን አብራርተዋል ።
«... ሰው ሞተ ማለት ከባድ ነው፣ ሰው ሞተ ማለት እውነት ነው ወይ? ብለህ ስትጠይቅ እዚያ የሚያደርስ ነገር የለም፣ ርዳታም በቅርብ ነው የተቋረጠ ርዳታ እየቀረበ ነው የነበረው፤ የሞት ሪፖርት አልደረሰንም ። እንደዚህ ዓይነት ሪፖርት እየዋሹም ጭምር ይናገራሉ ነው» ሲሉ ነው ተፈናቃዮች በረሀብ ምክንት ሞተዋል የሚለውን ስሞታ ያስተባበሉት ።
በደቡብ ወሎ ዞን ብቻ 12 የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያዎች ይገኛሉ ። በመጠለያ ጣቢያዎቹ 16 ሺህ ተፈናቃዮች ሲኖሩ 30ሺህ ያክሉ ደግሞ ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው የሚኖሩ እንደሆኑ ከዞኑ ያገኘነው መረጃ ያሳያል ።፡ የአማራና የኦሮሚያ ክልል መንግስታት ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ የጋራ መግባባት ላይ ደርሰው የተወሰኑ በአማራ ክልል የነበሩ ተፈናቃዮች ወደ ኦሮሚያ ክልል በቅርቡ መመለሳቸው ይታወሳል።
ዓለምነው መኮንን
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ