1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አማራ ክልል በመከላከያና የፋኖ ፍጥጫ ውጥረት አይሏል

ረቡዕ፣ ጥቅምት 7 2016

በአማራ ክልል በመከላከያ እና የፋኖ ታጣቂዎች ፍጥጫ ውጥረት ማየሉን ነዋሪዎች ለዶይቸ ቬለ ተናገሩ ። የባሕር ዳር ከተማ ውስጥ ትናንት ማምሻውን የተኩስ ድምፅ ይሰማ እንደነበረም ነዋሪዎች ገልጸዋል ። በቡሬ፣ ደብረማርቆስ፤ ፍኖተ ሰላም፣ ጎንደር እና ደብረታቦርን በመሳሰሉ ከተሞች መከላከያ በከተሞች በትንሽ ርቀት ግን የፋኖ ታጣቂዎች አሉ ተብሏል ።

https://p.dw.com/p/4XhO3
ኢትዮጵያ፤ ጎንደር ከተማ
ከፊል የጎንደር ከተማ ከከፍታ ሲታይ ። ፎቶ፦ ከማኅደር ምስል Alemnew Mekonnen/DW

በክልሉ የተለያዩ ከተሞች የፀጥታ ሥጋቱ ከፍ ብሏል

በአማራ ክልል የተለያዩ ከተሞች እና የአቅራቢያ ወረዳዎች በመከላከያ እና የፋኖ ታጣቂዎች ፍጥጫ ውጥረት ማየሉን ነዋሪዎች ለዶይቸ ቬለ ተናገሩ ።  የባሕር ዳር ከተማ ውስጥ ትናንት ማምሻውን የተኩስ ድምፅ ይሰማ እንደነበረም ነዋሪዎች ገልጸዋል ። በቡሬ፣ ደብረማርቆስ፤ ፍኖተ ሰላም፣ ጎንደር እና ደብረታቦርን በመሳሰሉ ከተሞች መከላከያ እንደሚገኝ፤ በትንሽ ርቀት ግን  የየፋኖ ታጣቂዎች እንዳሉ ነዋሪዎች አክለዋል ። 

በተደጋጋሚ ውጊያዎች ተወጥሮ የሚገኘው የአማራ ክልል በመከላከያ እናየፋኖ ታጣቂዎች መካከል ከነገ ዛሬ ውጊያ ሊቀሰቀስ ይችላል በሚል ነዋሪዎች በሥጋት መዋጣቸውን ገለጹ ። የክልሉ ርእሰ መዲና በሆነችው ባሕርዳር ውስጥ ትናንት ማምሻውን የተኩስ ድምፅ ይሰማ እንደነበረም ዶይቸ ቬለ ከነዋሪዎች ማረጋገጥ ችሏል ። በከተማዪቱ የፀጥታው ሥጋት እጅግ ከማየሉ የተነሳ ግን ነዋሪዎች አስተያየታቸውን በድምፅ ለመስጠት መስጋታቸውንም አልሸሸጉም ። ይህ ዘገባ እስከጠናከረበት ምሳ ሰአት ድረስ ከተማዪቱ ውስጥ የመከላከያ ወታደሮች በከፍተኛ ሁኔታ ጥበቃ እያደረጉ መሆኑንም አክለዋል ።  ጎጃም ውስጥ በምትገኘው የቡሬ ከተማ ነዋሪ የሆኑ አንድ ግለሰብ ለዶይቸ ቬለ እንደተናገሩት በከተማዪቱ የፀጥታው ሥጋት ከምን ጊዜውም በላይ አይሏል

«ሰሞኑን በተለይ እሁድ አካባቢ ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው መከላከያ ገብቶ ከባድ መሣሪያ ነበር ሲያዘንብ የዋለው ከሰአት በኋላ ጀምሮ በጣም ብዙ ተከታታይ የሆነ ከባድ መሣሪያዎችን ሲተኩስ ነበር ያመሸው ከዚያ በኋላ ምሽት ላይ ግማሹ ኃይል ተመለሰ ግማሹ ኃይል እዚሁ ከተማ ላይ ቀረ መጀመሪያ ላይ በፋኖ ቁጥጥር ስር ነበር የቆየ ከተማው፤ ከዚያ አሁን ግን ሥጋት ነው ማለት የፋኖ ኃይል አብዛኛው በተለያያ አቅጣጫ  እየተቃረበ ያለበት ሁኔታ እና እንዲሁም መከላከያ እዚሁ ከተማ ላይ አለ »

መከላከያ እሁድ ዕለት ወደ ከተማዪቱ እንደገባ በተደጋጋሚ ተተኮሰ ባሉት ከባድ ጦር መሣሪያ እሳቸው በሚያውቁት አራት ሰዎች መገደላቸውን ነዋሪው ጠቅሰዋል ። ከሟቾቹ መካከል ሁለቱ ከብት ጥበቃ ላይ የነበሩ ልጆች ሲሆኑ፤ አንደኛው የአእምሮ ኅመምተኛ ነው ብለዋል ። የፋኖ ኃይል በከተማዋ ሳለ የነበረው አብዛኛው መደበኛ እንቅስቃሴ ከእሁድ ጀምሮ  እጅግ መቀነሱን ነዋሪው አክለዋል ። ሌላው የደብረማርቆስ ነዋሪ በበኩላቸው ከነገ ዛሬ ጦርነቱ ዳግም ሊጀመር ነው በማለት ነዋሪው በስጋት መዋጡን ለዶይቸ ቬለ (DW) ተናግረዋል ።

ኢትዮጵያ፤ ነፋስ መውጪያ ከተማ
ኢትዮጵያ፤ ነፋስ መውጪያ ከተማ ። ፎቶ፦ ከማኅደር ምስል Belete Tigabe

«አሁን ከተማው ላይ ያለው መከላከያ ነው።  ነገር ግን ፋኖ ይመጣል ምናምን በሚል ውጥረት አለ በየቀኑ ማለት ነው ነጻ ሆነህ አትንቀሳቀስም እንቅስቃሴም ብዙም የለም በጣም ብቻ ከባድ ነው አሁን ያለው ሁኔታ በጣም ነው የሚያስጠላው ዙሪያ ገባውን ትንንሽ የወረዳ ከተሞችን በሙሉ ፋኖ ተቆጣጥሯቸዋል ነው የሚባለው እነሱን በሙሉ ፋኖ ነው በቁጥጥር ስር ያደረጋቸው »

መጓጓዣዎች አገልግሎት በከተማዪቱ ከዐሥር ከሃያ እጥፍ በላይ እየተከፈለባቸው መሆኑንም ተናግረዋል ። በፍኖተሰላም ከተማ ነዋሪ የሆኑ አንድ አስተያየት ሰጪ በከተማዪቱ አንጻራዊ ሰላም እንዳለ ተናግረዋል ። ዐርብ እና ሰኞ የክልሉ ባለሥልጣናት ከመንግሥት ሠራተኞች እና ከኅብረተሰቡ ጋ ከተነጋገሩ በኋላ በከተማዪቱ መደበኛ እንቅስቃሴ ለማስጀመር እየጣሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል ። ፍኖተ ሰላም ያው እንደምታውቁት ባለፉት ሦስት ወራት ከሐምሌ ጀምሮ ጦርነት ነበረች

«በአሁኑ ወቅት የመከላከያ ሠራዊት እና የአድማ ብተና ኃይሉ ነው ከተማ ውስጥ ያለው ድርጅቶችም በግድ ክፈቱ እያሉ የመንግሥት ኃይሎች እያስከፈቱ ነው ካፌዎች ሃያ ሰላሳ ከመቶ ከፍተዋል ሱቆች ትንሽ ተከፍተዋል። ዐርብ እና ሰኞ ከመንግሥት ሠራተኛው እና ከማኅበረሰቡ ውይይት ነበር የክልልሉ ፕሬዚደንት ከምሥራቅ እዝ አዛዥ ሆነው መጥተው ነበር ከዚያ በኋላ ነው ትናንትና እና ዛሬ እያስገደዱ እያስከፈቱ ነው አሁን የመንግሥት ኃይሎች ድርጅቶችን ክፈቱ ሥራ ይጀመር በሚል በውድ ሳይሆን በግድ ከፍተው እንዲሠሩ አድርገዋል »

የጎንደር ከተማ
ኢትዮጵያ፤ የጎንደር ከተማ ። ፎቶ፦ ከማኅደር ምስል Alemnew Mekonnen/DW

ለደኅንነታቸው በመፍራት ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የጎንደርነዋሪ በበኩላቸው በከተማዪቱ አንጻራዊ ሰላም እንዳለ ገልጸዋል ። ሆኖም ከነገ ዛሬ ውጊያ ሊቀሰቀስ ይችላል በሚል ነዋሪው ብርቱ ስጋት እንደገባው ተናግረዋል ።  ከተማው ውስጥ የመከላከያ ወታደሮች ቢኖሩም ብዙም ሳይርቅ ግን እንደ አብዛኛ የክልሉ ከተሞች ሁሉ ዙሪያ ገባው በፋኖ ቁጥጥር ላይ ነው ብለዋል ። በለሳ አካባቢ ግጭቶች መኖራቸውንም ጠቁመዋል ።

«እብናት ከተማ ላይ ነበር የቆየው መከላከያው፤ እሱ ለሌላ ተልእኮ ሲወጣ ፋኖ ተቆጣጥሮታል ከተማውን። »

በደብረ ታቦር ከተማ ነዋሪ የሆኑ አንድ የዐይን እማኝ ከተማው ውስጥ መከላከያ ከዚያ ውጪ ደግሞ በቅርብ ርቀት የፋኖ ታጣቂዎች ይገኛሉ ብለዋል። መከላከያ እብናት ከተባለው ከተማ እንደወጣ እና ፋኖ ከተማዋን እንደያዘ ገልጸዋል ። ከሌሎች የአማራ ክልል አካባቢዎች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት በስልክ መስመር ችግር እና አስተያየት ለመስጠት በመስጋት ሊሳካ አልቻለም ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ 

አዜብ ታደሰ