1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«አሁን ከሕግ ፍትህ እሻለሁ” ከሰሞኑ በነቀምቴ የተደፈረችው ታዳጊ

ሐሙስ፣ ጥቅምት 21 2017

ከሰሞኑ መነጋገሪያ የነበረውና በርካቶችን እጅግ ያስቆጣው ከነቀምቴ ከተማ ወጣ ወዳለው ስፍራ ሁለት አዳጊ ሴቶች ለአስገድዶ መድፈር ወንጀል ሰላባ ሲሆኑ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል የማኅበረሰቡንም እሴት የጣሰ መሆኑ መነጋገሪያ ሆኗል።

https://p.dw.com/p/4mSJi
የጾታዊ ጥቃት ሰለባ
የጾታዊ ጥቃት ሰለባ ፎቶ ከማኅደር ምስል Nariman El-Mofty/AP/picture alliance

«አሁን ከሕግ ፍትህ እሻለሁ”

በወንጀሉ ከተሳተፉ አምስቱ በፖሊስ ተይዘው ምርመራ እንደተጀመረባቸው የኦሮሚያ ክልል ሴቶችና ሕጻናት ቢሮ እና የነቀምቴ ከተማ ፖሊስ ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል። የወንጀል ድርጊቱ ተጠቂ ከሆኑት አንዷ ለዶቼ ቬለ እንደገለጸችው ከቪዲዮው መለቀቅ በኋላ በደረሰባት የስነልቦና መቃወስ ትምህርቷን ለማቋረጥ ተገዳለች። 

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ነቀምቴ ከተማ የ05 ቀበሌ ነዋሪዋ ገና የ15 ዓመት አዳጊ፤ የ7ኛ ክፍል ተማሪ ናት። ዶይቼ ቬለ ለልጅቷ ደህንነት ስሟን ከመግለጽ ተቆጥቧል። በቅርቡ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በስፋት በተጋራው ተንቀሳቃሽ ምስል በርካቶች እንደተመለከቱት ከተደፈሩ ሁለት ሴት ልጆች አንዷ ናት።

የአስገድዶ መድፈር ወንጀሉ መፈጸምና አስነዋሪ ክንውኖቹ

አዳጊዋ ለዚህ ስነልቦናዊና አካላዊ ጉዳት የዳረጋትን ድርጊት አፈጻጸም እንዲህ ነው የገለጸችልን።

«ነገሩ የተፈጸመው ጥቅምት 07 ቀን 2017 ዓ.ም. ነው። ትምህርት ገና መጀመሩ ነው። በግምት ከሰዓት 8 ሰአት ይሆናል። በሰአቱ ከጓደኛዬ ጋር አንዲት ጓደኛችንን ሸኝተናት ወደ ትምህርት እየተመልስን ነበር። ሁለት ወጣቶች ወደኛ መጡና ጓደኛዬን አናገሯት። እሷም ነይ እንሂድ አለችኝ። እምቢ ስላትም ችግር እንደማይፈጠር አሳምናኝ ወጣን። ከዚያን ከከተማው ወጣ ወዳለ አንድ ጫካ ገባን። ትልልቅ ስልክ የያዙ እረኛ የሚመስሉ የእነዚህ ይዘውን የሄዱ ጓደኞች ነበሩ። ከዚያ ሁለት ምርጫ ሰጡን። ግብረስጋ ግንኙነት ፈጽማችሁ በሰላም ትገባላችሁ ወይስ ተደብድባችሁ ራቁታችሁን መግባት ነው ምርጫችሁ አሉን። ያ ድርጊት ሲፈጸም ምንም አለመረጋጋት ውስጥ ሆኘ ብመለከታቸውም ቢያንስ ቪዲዮ ሲቀርጹ የነበሩ 10 ሰው ይሆናሉ። ቪዲዮውን ለምን ዓለማ እንደቀረጹ አላውቅም» ብላለች ተጎጂዋ፡፡

የአስገድዶ መድፈር ወንጀሉ በሁለቱ ወጣቶች መፈጸሙን የምትገልጸውተጎጂዋ ወንጀል ፈጻመሚዎቹ ባጃጅ የሚነዱና በሰፈር በዓይን የሚተዋወቁ መሆኑንም ግልጻ፤ የአስገድዶ መድፈር ወንጀሉ ከሁለቱ ውጪ በቡድን አለመፈጸሙን ግን አረጋግጣለች። በርካታ ቪዲዮ መቀረጹንም በመግለጽ ያ ደግሞ ትምህርት ቤት መሄድን እስከመፍራት ያደረሳት፤ ስነልቦናዊ ስብራትም እንዳደረሰባት ታስረዳለች። «አሁን በቀደም ፖሊስ ጣቢያ ስንሄድ ቪዲዮ ሲቀርጹን የነበሩትን ጨምሮ ከአንዱ ውጪ አብዛኞቻቸው ተይዘው ተመልክቻለሁ። አሁን ሕግ የሚፈርደውን ብቻ ነው የምጠብቀው። እኔ አሁን ለጤናዬ ደህና ነኝ። ህክምናም ሄጄ ታይቻለሁ» ብላለች።

የሕግና ማኅበራዊ ጉዳይ አካላት ክትትል

የነቀምቴ ፖሊስ መመሪያ ኃላፊ ካሚሽነር ሻሎ ገለታ ከዚህ ጋር ተያይዘው በቁጥጥር ስር የዋሉ መኖራቸውን አረጋግጠው ጉዳዩ በማጣራት ሂደት ላይ እንደመሆኑ ምርመራው ካለቀ በኋላ ሰፊ መረጃ እንደሚሰጡበት ነግረውናል፡፡ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተልኩ ነው ያለን የኦሮሚያ ክልል ሴቶችና ሕጻናት ቢሮ በበኩሉ በወንጀሉ የተጠረጠሩት አብዛኞች ተይዘው በአስገድዶ መድፈር ወንጀሉ በቀጥታ ከተሳተፉ ሁለት ወጣቶች አንዱ ብቻ መሰወሩን አመልክቷል፡፡ የቢሮው ኃላፊ መብራቴ ባጫ ለዶይቼ ቬለ፤ «ጉዳዩን ሕግ ይዞታል አሁን፡፡ ድርጊቱን ከፈጸሙት ሁለቱ አንዱ ተይዟል፡፡ ቪዲዮ ሲቀርጹ የነበሩም ተይዘዋል፡፡ አሁን ለጊዜው ያልተያዙት የሌላ አካባቢ ወደ ቡኖ በደሌ ተወላጅ የሆኑ በአስገድዶ መድፈሩ በቀጥታ የተሳተፈው አንደኛውና ሁኔታውን ያመቻቸው ነው። የተያዙት ምርመራ ላይ ናቸው፡፡ በቅርበት እየተከታተልን ነው፡፡»  ሲሉ ማብራሪያ ሰጥተውናል፡፡

አክለውም ከተደፈሩት አንደኛዋ በድርጊቱ እጇ አለበት የሚል ጥርጣሬ መኖሩን አመልክተዋል።

ሥዩም ጌቱ

ሸዋዬ ለገሠ

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር