1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ተፈናቃዮች በዓልን በሻምቡ ከተማ

ማክሰኞ፣ መስከረም 1 2016

በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞንና በምስራቅ ወለጋ ዞን ውስጥ የሚገኙ የተፈናቀሉ ዜጎች በ2016 ዓ.ም በአካባቢአቸው ሠላም ሰፍኖ ወደየቀያቸው መመለስ እንደሚሹ ተናገሩ፡፡ ከሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ ተፈናቅለው በሻምቡ ከተማ የነበሩ የተወሰኑ ተፈናቃዮች ወደ ቀያአቸው ተመለሰው በዓሉን ማሳለፋቸውን ገልጸዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4WFIb
ኪረሙ ወረዳ፤ ኢትዮጵያ
የኪረሙ ወረዳ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጅሬኛ ሂርጳ በወረዳቸው 52 ሺ 8 መቶ የሚደርሱ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ ገልጸዋል፡ምስል Privat

ኪረሙ 52 ሺ 8 መቶ የሚደርሱ ተፈናቃዮች እንዳሉ ይነገራል

በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞንና በምስራቅ ወለጋ ዞን ውስጥ የሚገኙ የተፈናቀሉ ዜጎች በ2016 ዓ.ም በአካባቢአቸው ሠላም ሰፍኖ ወደየቀያቸው መመለስ እንደሚሹ ተናገሩ፡፡ ከሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ ተፈናቅለው በሻምቡ ከተማ የነበሩ የተወሰኑ ተፈናቃዮች ወደ ቀያአቸው ተመለሰው በዓሉን ማሳለፋቸውን ገልጸዋል፡፡ በምስራቅ ወለጋ ኪረሙ ወረዳደግሞ አዲሱን ዓመት በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ማሳለፋቸውን ገልጸዋል፡፡ የአሶሳ ወኪላችን ነጋሣ ደሳለኝ ተጨማሪ አለው ።

የፀጥታ ችግር 

ባለፈው ዓመት ነሐሴ 24 ቀን፣ 2014 ዓ.ም ከሆሮ ጉዱሩ ዞን አሙሩ ወረዳ አጋምሳ ከተማ በፀጥታ ችግር ወደ ዞኑ ዋና መቀመጫ ሻምቡ ከተማ ተፈናቅለው መቆየታቸውን የነገሩን አንድ ነዋሪ ከአንድ ዓመት በኋላ ወደ ቀያአቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል፡፡ ነሐሴ 28 ቀን፣ 2015 ዓ.ም ወደ ቀድሞ ቀያቸው አሙሩ ወረዳ አጋምሳ ከተማ ተመልሰው አዲሱን ዓመት ማሳለፋቸውን ገልጸዋል፡፡ ወደ ቀያቸው ቢመለሱም በ2015 ዓ.ም በአካባቢያቸው የግብርና ሥራ በመስተጓጎሉ በርካቶች የዕለት ደራሽ ድጋፍ እንደሚያስልጋቸው አመልክተዋል፡፡

በምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት እና ለደህንነታቸው ስለሚሰጉ ስሜ አይጠቀስ ያሉ ሌላው አንድ አርሶ አደር ከ3 ሳምንት በፊት በስፍራው 25 ኪ.ሎ እህል ድጋፍ እንደተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡ በወረዳው 18 ከሚደርሱት ቀበሌ ውስጥ ነዋሪዎች ተፈናቅለው በአንድ ከተማ የሚገኙ ሲሆን ሰብአዊ ድጋፍ ከሰው ብዛት አንጻር እንደማይዳረስም ገልጸዋል፡፡ በዚህ አዲሱ ዓመት አካባቢው ሰላም ሰፍኖ ወደ ቀበሌአቸው መመለስ እንደሚፈልጉ ጠቁመዋል፡፡

‹‹ወደ ቤቱ የተመለሰ አንድም ተፈናቃይ የለም፡፡ 25 ኪ.ሎ ስንዴ ከተሰጠን 3 ሳምንት ሆኖናል፡፡ እንደ አጠቃላይ ያልተነገሩ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ ከከተማ ወጣ ብሎ ርቀት መንቀሳቀስ አንችልችም፡፡ በዚሁ ነው በዓሉን እያሳለፈን ያለነው፡፡»

የሆሮ ጉዱሩ ተፈናቃዮች በከፊል፦ ፎቶ ከማኅደር
የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ተፈናቃዮች በከፊል። በአካባቢው በተደጋጋሚ በተከሰተው ግጭት በርካቶች በአብዛኛው ሕጻናት እና ሴቶች ከመኖሪያቸውለመፈናቀል ተገደዋል ። ምስል Seyoum Getu/DW

በርካቶች የተፈናቀሉባት የኪረሙ ወረዳ

ሌላው የኪረሙ ወረዳ ነዋሪም በሰጡን አስተያየት በአካባቢው በተለያዩ ስም ተደራጅተው የሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ኃይሎች እንዳሉና በአብዛኛው ቀበሌዎች የፀጥታ ስጋት በመኖሩ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደቀአያቸው መመለስ አለመቻላቸውን ጠቁመዋል፡፡ ነዋሪው እንደሚሉት ከ 3 ሳምንት በፊት ተሰጥተዋል የተባለው ሰብአዊ ድጋፍም እንዳልደረሳቸው ጠቁመዋል፡፡ በአዲሱ ዓመት በአስቸኳይ ይደረግልን ያሉትን ሀሳብ አጋርተዋል፡፡

የኪረሙ ወረዳ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጅሬኛ ሂርጳ በወረዳቸው 52 ሺ 8 መቶ የሚደርሱ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ ለእነዚህ ለተፈናቀኩ ዜጎች በተለያየ ወቅቶች በመንግስት እርዳታ የመጣ ቢሆን ሰብአዊ ድጋፍ ከተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ጋር አለመመጣጠኑን አክለዋል፡፡ ከዚህ ቀደም የተላኩ ሰብአዊ ድጋፍ በተገቢው መልኩ ባለመሰራጨቱ የወረዳው የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ጽ/ቤት (ቡሳ ጎኖፍ ጽ/ቤት) ባለሞያዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጋቸውን አብራርተዋል፡፡

‹‹የኪረሙ ወረዳ ቡሳ ጎኖፋ ቢሮ ኃላፊና ባለሞያዎችም በትክክለኛው መንገድ ባለማሰራጨታቸው በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡ ወደ ቀበሌአቸው የተመለሱ የተፈናሉ ነዋሪዎች ብዙም የሉም፡፡ እውነት ነው በቂ የሆነ ሰብአዊ ድጋፍም የለም፡፡ 52ሺ 8 መቶ 22 የተፈናቀሉ ዜጎች ናቸው በወረዳ ላይ ያሉት፡፡»

የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አስተዳደር ከዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች ተፈናቅለው በዞኑ ከተማ ሻምቡ የነበሩ የተፈናቀሉ ዜጎች ወደየ ወረዳቸው መመለሳቸውን ገልጸዋል፡፡ በአራቱም የወለጋ ዞኖች ውስጥ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በልዩ ልዩ ምክንያቶቸ ተፈናቅለው እንደሚገኙ የመንግስታቱ ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዩች ማስተባበሪያ ቢሮ ዘገባ ያመለክታል፡፡

ነጋሣ ደሳለኝ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ