ተደጋጋሚ የተፈጥሮ አደጋዎች ያስከተሉት ጉዳት እና የመከላከል ሥራዎች በኢትዮጵያ
እሑድ፣ ነሐሴ 26 2016በኢትዮጵያ ከሰሞኑ የተከሰቱ ተደጋጋሚ የተፈጥሮ አደጋዎች ለበርካቶች ሞት እና መፈናቀል ሰበብ ሆነዋል ። በጎፋ የመሬት መንሸራተት ከሁለት መቶ አምሳ በላይ ሰዎች መቀጠፋቸው ያጫረው የሐዘን ጠባሳ ገና አልጠገገም ። ጎንደር፤ ሰሜን ሸዋ ዞን፤ ኦሮሚያ ክልል ዶዶላ ወረዳ፤ መካከለኛው ኢትዮጵያ ሥልጤ ዞን፤ ደቡባዊ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በዎላይታና በጋሞ ዞኖችንም ሰሞኑን ተከታታይ የጎርፍ እና የመሬት መንሸራተት አደጋዎች ከተከሰቱባቸው አካባቢዎች የሚጠቀሱ ናቸው ።
አደጋዎቹ በሰው ሕይወት እና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል ። በአዝርእት እና ሰብሎች ምርት ላይ ብርቱ ጉዳትን አስከትለዋል ። በእርግጥ የተፈጥሮ አደጋዎችን ሙሉ ለሙሉ መከላከል አይቻልም ። ሆኖም በየትኛውም የዓለማችን ክፍሎች ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን እና መጠናቸውን በተመለከተ ግን በሳይንሳዊ ትንታኔ ቅድመ ትንበያ የሚሰጡ ተቋማት አሉ ። በኢትዮጵያም አደጋዎችን የመለየት እና የቅድመ ጥንቃቄ ርምጃዎች እንዲወሰዱ የሚያሳስቡ፤ አደጋ ከደረሰ በኋላም ምላሽ የሚሰጡ ተቋማት እንቅስቃሴ ያደርጋሉ ።
የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን፤ የአየር ጠባይ ትንበያ ላይ የሚሠራው የሜትሪዮሎጂ ኢንስቲትዩት እንዲሁም፤ በዩኒቨርሲቲ ደረጃም ምርምሮችን እና ጥናቶችን የሚያከናውነው የከርሰ ምድር ጥናት ተቋም ተጠቃሾች ናቸው ። ከሦስቱም ተቋማት ባልደረባ የሆኑ ኃላፊዎች እና አጥኚዎች በዛሬው የእንወያይ መሰናዶ ተካፋይ ናቸው ። «ተደጋጋሚ የተፈጥሮ አደጋዎች ያስከተሉት ጉዳት እና የመከላከል ሥራዎች በኢትዮጵያ» የዛሬው እንወያይ መሰናዶ ዐቢይ ትኩረት ነው ።
በዶዶላ የጣለው ከባድ ዝናብ ያስከተለው የከፋ ጉዳት
በውይይቱ 3 እንግዶች ተሳታፊ ናቸው ። እንግዶቻችን፦ 1-ፕሮፌሰር አታላይ ዓየለ፦ በአዲስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፤ የጂኦ ፊዚክስ፤ ሕዋ ሣይንስ እና አስትሮኖሚ ተቋም የመሬት መንቀጥቀጥ ሳይንስ ተመራማሪ እና መምሕር እንዲሁም የሴስሞሎጂ ክፍል ኃላፊ፤
2-ዶ/ር አሳምነው ተሾመ፦ በኢትዮጵያ ሜትሪዮሎጂ ኢንስቲትዩት የሜትሪዮሎጂ ትንበያ እና ቅድመ ማስጠንቀቂያ ምርምር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር፤ እንዲሁም
3-አቶ አታለል አቡሀይ፦ የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት እና የኮሙኒኬሽን ተወካይ ሥራ አስፈጻሚ ናቸው ።
ሙሉውን ውይይት በድምፅ ማዕቀፉ መከታተል ይቻላል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ