1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ወለጋ፦ በፀጥታ ኃይላትና ሸማቂዎች ግጭት የ5 ሰዎች ሕይወት አለፈ

ረቡዕ፣ ኅዳር 12 2016

ሰኞ፤ ኅዳር 10 ቀን፣ 2016 ዓ.ም በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ሱሉላ ፍንጫኣ የተባለ ወረዳ ውስጥ በመንግስት ፀጥታ ኃይላትና መንግስት «ሸኔ» ብሎ በአሸባሪነት በፈረጀው ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ በሚጠራው ሸማቂ መካከል በተፈጠረው ግጭት የአራት ያልታጠቁ ሰዎችn 1 ታጣዊ ሕይወት ማለፉን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ።

https://p.dw.com/p/4ZJFz
የኦሮሚያ ክልል መልከዓምድር
የኦሮሚያ ክልል መልከዓምድር ከፊል ገጽታ ። ፎቶ፦ ከማኅደርምስል G. Fischer/blickwinkel/picture alliance

4 ያልታጠቁና 1 ታጣቂ መገደላቸው ተገልጿል

ሰኞ፤ ኅዳር 10 ቀን፣ 2016 ዓ.ም በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ሱሉላ ፍንጫኣ የተባለ ወረዳ ውስጥ በመንግስት ፀጥታ ኃይላትና መንግስት «ሸኔ» ብሎ በአሸባሪነት በፈረጀው ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ብሎ በሚጠራው ሸማቂ መካከል በተፈጠረው ግጭት የአራት ያልታጠቁ ሰዎች ሕይወት ማለፉን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ።  በዕለቱ ታጣቂዎች ወደ ወረዳው በመግባት  ከፀጥታ ኃይላት ጋ ለሰዓታት የቆየ የተኩስ ልውውጥ ካደረጉ በኋላ ከወረዳው መውጣታቸውን ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።  በግጭቱ ሕይወታቸው ካለፈው ሰዎች በተጨማሪ 3 ሰዎች መቁሰላቸውንም ተናግረዋል ። ተጨማሪ ማብራሪያ ከሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪና ከኦሮሚያ ክልልኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ማብራሪያ እንዲሰጡን በስልክ ያደረግነው ጥረት ስልክ ባለመነሳቱ አልተሳካም ። 

በተኩስ ልውውጡ የሞቱት እነ ማን ናቸው?

በኦሮሚያ ክልል በተለይም ታጣቂዎች በስፋት በሚንቀሰቃሱበት አካባቢዎች ሰላም ያሰፍናል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት የነበረው የታንዛኒያው የሰላም ድርድር እየተካደ በነበረበት ወቅት በተለያዩ ቦታዎች በመንግስት ፀጥታ ኃይላትና ታጣቂዎች መካከል የተኩስ ልውውጥ እንደነበር ተገልጿል። የመንግስት ፀጥታ ኃይላትና መንግስት «ሸኔ» ብሎ የሚጠራቸውና ራሳቸውን የኦሮሞ ነጻነት ስራዊት ብሎ  በሚጠሩ ሸማቂዎች መካከል ከትናንት በስትያ ኅዳር 10 ቀን፣ 2016 ዓ.ም በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ሱሉላ ፍጫኣ ወረዳ ውስጥ ወጊያ እንደነበር ያነጋርናቸው የአካባቢው  ነዋሪዎች  አመልክተዋል። የሱሉላ ፍንጫኣ ወረዳ ነዋሪ መሆናቸውና ለደህንነታቸው ስለሚሰጉ ስሜ አይገለጽ ያሉ ነዋሪ በሰጡን አስተያየት ሰኞ ዕለት ከንጋቱ 12፡00 ሰዓት ገደማ ታጣቂዎች ወደ  ከተማው በመዝለቅ በስፍራው ከነበሩ የጸጥታ ኃይላት ጋር መጋጨታቸውን ተናግረዋል፡፡  ጠዋት 2 ሰዓት ገደማ ደግሞ ታጣቂዎች ከከተማ መውጣቸውን ገልጸው በአካባቢው የነበሩ 3 ነዋሪዎች መቁሰላቸውን ሌሎች አራት ሰዎች ደግሞ ሕይወት ማለፉን ጠቁመዋል፡፡

ሌላው የአካባቢው ነዋሪም ከትናንት በስትያ በመንግሥት ፀጥታ ኃይላትና ሸማቂዎች መካከል ለ3 ሰዓት ያህል የተካሄደው የተኩስ ልውውጥ ከሱሉላ ፍንጫ ወረዳ የፍንጫ ስኳር ፈብሪካ በቅርብ ርቀት ላይ እንደነበር ገልጸዋል፡፡ በሁለቱም ኃይላት መካከል በተከሰተው ግጭት ሕይወታቸው ያለፈው አራቱ ያልታጠቁ ሰዎች ሲሆኑ፤ ከሸማቂዎች ደግሞ አንድ ሰው ተገድለው ከተማ ውስጥ ማየታቸውን  ነዋሪው ገልጸዋል፡፡ ሕይወታቸው ካልፈው ከአራቱ መካከል አንዱ ዘመዳቸው እንደሆነ ጠቁመው  በመኪና ውስጥ እያለ በበራሪ ጥይት ሕይወቱ ማለፉንም ተናግረዋል፡፡

የፍንጫኣ ስኳር ፍብሪካና የታጣቂዎች እንቅስቃሴ

በፍንጫ ስኳር ፍብሪካ አካባቢ በግንቦት ወር 2015 ዓ.ም ግጭት ተከስቶ እንደነበር የገለጹት ነዋሪው ፀጥታ ኃይላትና ሸማቂዎች በፋብሪካ አካባቢ የሚያደርጉት የተኩስ ልውውጥ በአካባቢው ከፍተኛ ስጋት መፍጠሩን ጠቁመዋል።

በፍንጫ ስኳር ፍብሪካ
በፍንጫ ስኳር ፍብሪካ አካባቢ ፀጥታ ኃይላትና ሸማቂዎች ከዚህ ቀደም ያደረጉት የተኩስ ልውውጥ ከፍተኛ ሥጋት ፈጥሮ ቆይቷልምስል Negassa Dessalegn/DW

በሱሉላ ፍንጫኣ የተከሰተው የፀጥታ ችግር አስመልክቶ መረጃ እንዲሰጡን ከሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ እና ኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት  በተደጋጋሚ ስልክ ብንደውልም ስልካቸውን ባለማንሳታቸው ሀሳባቸውን ማካተት አልተቻለም፡፡ በምዕራብ ኦሮሚያ በተደጋጋሚ ሲከሰት በነበሩ ግጭቶችና ጥቃቶች በሰላማዊ ሰዎች ሕይወት ላይ ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኙ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ ከዚህ ቀደም በሸማቂዎች እና መንግስት ጸጥታ ኃይላት መካከል በነበሩት አለመግባባቶችም በሰው እና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን በተለያዩ ጊዜያት መዘገባችን ይታወሳል፡፡ መንግስት እና የኦሮሞ ነጻነት ስራዊት መሪዎች በታንዛኒያ ሲያካሂዱ የነበረው 2ኛ ዙር ድርድር ያለ ስምምነት መጠናቀቁን ሁለቱም ወገኖች በየፊናቸው ትናንት ማምሻውን ባወጡት መግለጫ አስታውቋል። በመግለጫው ለሰላም ድርድሩ አለመሳካት ምክንያት ለተባሉ ጉዳዮች ሁለቱም ዕርስ በዕርሳቸው ሲወነጃጀሉ ተስተውሏል።

ነጋሣ ደሳለኝ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር