በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ታጣቂዎች የፈፀሙት ግድያ
ማክሰኞ፣ መስከረም 21 2017በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ሞጆና ሉሜ ወረዳዎች ዉስጥ ታጣቂዎች 12 ሠላማዊ ሰዎች መግደላቸውን ሁለት የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚ ፓርቲዎች አወገዙ።ሁለቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዳሉት ታጣቂዎች ባለፈዉ መስከረም 16 በከፈቱት ጥቃት ሞጆ ወረዳ ዉስጥ ለረጅም ዓመታት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስትያን አገልጋይ የነበሩ አዛውንትን ናቤተሰቦቻቸውን ገድለዋል።ከሁለት ቀናት በኋላ ደግሞ በዞኑ ሉሜ ወረዳ ስምንት ክርስቲያኖች በታጠቁ ኃይሎች ሌሊት ከየቤታቸው ከተወሰዱ በኋላ ተገድለዋል።እናት ፓርቲና የመላዉ ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ዛሬ በየፊናቸዉ ባወጡት መግለጫ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ዲፕሎማቶች ተደጋጋሚዉን ግድያ በዝምታ ማለፈቸዉ እንዳሳዘናቸዉ አስታዉቀዋል።
ስለ ግድያው የእናት ፓርቲ መግለጫ ምን ይላል?
እናት ፓርቲ በኢትዮጵያ "ሥርዓታዊ የሆነ" ሲል የገልፀውን በእምነት ተቋማት፣ በሃይማኖት አባቶችና ምእመናን ላይ የሚደርስን ጥቃት ማየት አልፎም ምንም እንዳልተፈጠረ በዝምታ ማለፍ የተለመደና "በተዘዋዋሪ ይኹንታ የመስጠት የሚመስል" ክስተት ሆኖ ዓመታት መቆጠራቸውን፣ ድርጊቶቹም መልክና ቦታ እየቀያየሩ አሰቃቂነታቸውም እየከፋ መቀጠሉን ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል።
ጠያቂም፣ ተጠያቂም ሳይኖር ለጥቂት ጊዜያት ጋብ ካለ በኋላ መልሶ የባሰ እልቂት ሲደርስ ይታያል ያለው ፓርቲው በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ሞጆ ወረዳ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ካህን የነበሩት ቀሲስ ወልደ ኢየሱስ አያሌው የተባሉ አዛውንት እና 4 ቤተሰባቸው በግፍ "በአሰቃቂ ኹኔታ መገደል ተራ ግድያ ሳይሆን በእምነት ተቋማት ላይ ያነጣጠረ ቀደም ሲል ከተፈጸሙ መሰል ግድያዎች የጥፋት ደረጃውን ከፍ አድርጎ ያሳየ" ጥቃት መሆኑን ገልጿል። የእናት ፓርቲ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጌትነት ወርቁ።
"በተደጋጋሚ የሚደረግ ነው። በተለይ ደግሞ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በኦሮሚያ ክልል በብዙ ቦታዎች ላይ አገልጋይ ካህናት እና ምእመናን ወደ ገዳማዊየን ጭምር የዘለቀ ነው"
ተጋላጭ የሆኑ የሃይማኖት ተቋማት ጥበቃ እንዲደረግላቸው ውትወታ "ሰሚ በማጣቱ ወይም ሆነ ተብሎ በመታለፉ" ዛሬም ግድያው በከፋ መልኩ እንደቀጠለ ነው የሚለው እናት ፓርቲ መሰል ግድያዎች "በተጠና መልኩ" የሚፈፀሙ ስለመሆኑም ኃላፊው ገልፀዋል።
ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና ዲፕሎማቶች በጉዳዩ ላይ ዝምታን መምረጣቸው እንዳሳዘነው የገለፀው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) በበኩሉ ከምንም በላይ መንግሥት በጉዳዩ ላይ "እያሳየ ያለው ዝምታ" እጅግ እንዳሳሰበው አስታውቋል።
መንግሥት በጉዳዩ ላይ "እያሳየ ያለው ዝምታ" አሳሳቢ ነው - መኢአድ
በጉዳዩ ላይ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያንጠቅላይ ቤተ ክህነት እና ከምስራቅ ሸዋ ዞን ሀገረ ስብከት ተጨማሪ ማብራሪያ እንዲሁም ከኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ምላሽ ለማግኘት ተደጋጋሚ ጥረት ብናደርግም አልተሳካም። በክልሉ ከዚህ ቀደም ሲል በአርሲ፣ በወለጋ እና በሌሎችም አካባቢዎች በሃይማኖት ተከታዮች እና በአብያተ ክርስትያናት ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት መፈፀሙን ያስታወሰው እናት ፓርቲ ከወራት በፊት በአንድ መድረክ ላይ የፓርቲው ኃላፊዎች ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ለኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ጥያቄ አንስተውላቸው እንደነበር አቶ ጌትነት ወርቁ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።
"ለምን ይህንን ነገር አትከላከሉትም የሚል ሀሳብ አንስተውላቸው ነበር [የፓርቲው አባላት] ግን አርኪ መልስ እና ወደ መፍትሔው የሚያደላ መልስ አልመለሱም"
ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና ዲፕሎማቶች በጉዳዩ ላይ ዝምታን መምረጣቸው እንዳሳዘነው የገለፀው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) በበኩሉ ከምንም በላይ መንግሥት በጉዳዩ ላይ "እያሳየ ያለው ዝምታ" እጅግ እንዳሳሰበው አስታውቋል።
የሚፈፀሙ ጥቃቶች እና አሳሳቢነታቸው መጨመር
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ ማትያስ ከቀናት በፊት በተከበረው የመስቀል ደመራ ክብረ በዓል ላይ "ባለፉት ዓመታት ሲፈታተኑን የቆዩ ዙሪያ መለስ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እልባት እንዲያገኙ እና ሕዝባችን ያለምንም ሥጋት ወጥቶ እንዲገባ፣ ሰርቶ እንዲያተርፍ፣ ተምሮ እንዲያውቅ፣ ሃይማኖቱን በነፃነት እንዲከተል፣ መንግሥት እና ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ለዘላቂ ሰለም እና አንድነት አበክረው እንዲሠሩ" በማለት ጥሪ አድርገው ነበር። በሞጆ ወረዳ አራቱ ግለሰቦች የተገደሉት ግን በዚሁ ዕለት ነበር።
በኢትዮጵያ የግጭት ዐውድ ውስጥ ባሉ አምስት ክልሎች ባለፉት ሦስት ወራት ከ 250 በላይ ሰዎች ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት መገደላቸውን ባለፈው ሳምንት ይፋ ያደረገው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፤ የዘፈቀደ፣ የጅምላና የተራዘመ እሥራትና የተፋጠነ ፍትሕ እጦት፣ አስገድዶ መሰወር፣ እገታ እና የሀገር ውስጥ መፈናቀል እሳሳቢ ሆነው መቀጥላቸውን ማስታወቁ ይታወሳል።
ሰለሞን ሙጬ
ነጋሽ መሐመድ
አዜብ ታደሰ