1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኤርትራውያን የሙዚቃ ፌስቲቫል ላይ 22 የጀርመን ፖሊሶች ተጎዱ

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 1 2015

በጀርመኗ ጊሰን ከተማ በተዘጋጀ አወዛጋቢ የኤርትራውያን የሙዚቃ ፌስቲቫል ላይ በተቀሰቀሰ ኹከት 22 ፖሊሶች ተጎዱ። የመካከለኛው ሔሰን ፖሊስ እንዳለው አብዛኞቹ ፖሊሶች ጉዳት የደረሰባቸው በሙዚቃ ድግሱ ላይ በነበረ የድንጋይ ውርወራ ነው። በከተማዋ ባለፈው ዓመት በተዘጋጀ መርሐ ግብር ላይ ተመሣሣይ ግጭት ተፈጥሮ ነበር።

https://p.dw.com/p/4TchI
Deutschland | Ausschreitungen beim Eritrea-Festival in Gießen
ምስል Helmut Fricke/dpa/picture alliance

በጀርመኗ ጊሰን ከተማ በተዘጋጀ አወዛጋቢ የኤርትራውያን የሙዚቃ ፌስቲቫል ላይ በተቀሰቀሰ ኹከት 22 ፖሊሶች ተጎዱ። ፖሊስ በሙዚቃ ድግሱ ላይ የተፈጠረውን ጠብ አስለቃሽ ጭስ በመተኮስ እና ውኃ በመርጨት ለመቆጣጠር ሞክሯል። 

ፖሊስ መርሐ ግብሩ ከመጀመሩ በፊት 22 ሰዎች በቁጥጥር ሥር እንዳዋለ የጀርመን ዜና አገልግሎት ዘግቧል። የጀርመን ዜና አገልግሎት የሔሰን ግዛት ባለሥልጣናትን ዋቢ አድርጎ እንደዘገበው ፖሊሶች የሙዚቃ ድግሱ ወደ ተዘጋጀበት አዳራሽ ለመመግባት በሚፈልጉ ሰዎች ጥቃት ተሰንሮባቸዋል።

ፖሊሶች የሙዚቃ አዳራሹ ወደሚገኝበት የሔሰንአለ ቅጥር ግቢ አጥር ዘለው ለመግባት የሞከሩ ከ100 በላይ ሰዎችን ለመከላከል ሙከራ ማድረጋቸውን የጀርመን ዜና አገልግሎት አክሎ ዘግቧል። በፖሊሶቹ ላይ ድንጋይ እና ጠርሙሶችን ጨምሮ የተለያዩ ቁሳቁሶች ተወርውረውባቸዋል። 

የግዛቲቱ ፖሊስ 22 ፖሊሶች መጎዳታቸውን አስታውቋል። የመካከለኛው ሔሰን ፖሊስ በትዊተር ባሰራጨው መልዕክት እንዳለው አብዛኞቹ ፖሊሶች ጉዳት የደረሰባቸው በሙዚቃ ድግሱ ላይ በነበረ የድንጋይ ውርወራ ነው። 

ከፍራንክፈርት በስተሰሜን በምትገኘው እና 80,000 ነዋሪዎች ባሏት ጊሰን ከተማ ለመርሐ ግብሩ አንድ ሺሕ ገደማ ፖሊሶች ተሰማርተው ነበር። እስከ ነገ እሁድ ይዘልቃል ተብሎ በነበረው የሙዚቃ ድግስ ከ2,000 እስከ 3,000 ሰዎች ይታደማሉ ተብሎ ይጠበቅ ነበር።  የመርሐ ግብሩ አዘጋጆች ከኤርትራ መንግሥት ጋር ጥብቅ ቁርኝት አላቸው በሚል እንደሚከሰሱ የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። 

በከተማዋ ባለፈው ዓመት በተዘጋጀ መርሐ ግብር ላይ ተመሣሣይ ግጭት ተፈጥሮ ነበር። የከተማው አስተዳደር በዚህ ዓመት የታቀደውን የሙዚቃ ድግስ የማገድ ፍላጎት የነበረው ቢሆንም ፍርድ ቤት አሳማኝ ምክንያት ባለማግኘቱ እንዲካሔድ ተደርጓል።