1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኢትዮጵያ ጎርፍ ከ15 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን አፈናቀለ

ሐሙስ፣ ጥር 28 2012

በደቡብ ክልል ጋሞ ዞን አርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ የጎርፍ መጥለቅለቅ ከአስራ አምስት ሺህ በላይ ነዋሪዎችን አፈናቀለ ። አደጋው የደረሰው ሰጎ እና ፊሌ የተባሉ ወንዞች ከገደባቸው አልፈው በወረዳው የሚገኙ ሶስት የገጠር ቀበሌያትን በማጥለቅለቃቸው ነው ። 

https://p.dw.com/p/3XLs0
Äthiopien Überschwemmung

ከ15 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ያፈናቀለው ጎርፍ

የአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መስፍን ደነቀ እንዳሉት የጎርፍ አደጋው ሊከሰት የቻለው ከባለፈው ማክሰኞ ጀምሮ በአካባቢው እየጣለ የሚገኘውን ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ተከትሎ ነው።

በዚህም በወረዳው ቆላ ሸሌ ፣ ሸሌ ሜላ እና ዘይሴ ኤልጎ በተባሉ የገጠር ቀበሌያት ውስጥ የሚኖሩ ከአስራ አምስት ሺህ በላይ ነዋሪዎችን በጎርፍ መጥለቅለቅ መፈናቀላቸውን ነው ዋና አስተዳዳሪው ለዶቼ ቨለ ( DW ) የገለጹት።   

Äthiopien Überschwemmung

በወረዳው የሸሌ ሜላ ቀበሌ ነዋሪ ነኝ ያሉ አንድ ተፈናቃይ ባለፈው ማክሰኞ የጣለውን ዝናብ ተከትሎ በድንገት አካባቢውን ያጥለቀለቀው ጎርፍ በርካታ የመኖሪያ ቤቶችን ፣ ሱቆችን ፣ የእምነት ተቋማትን እና የእርሻ ማሳዎችን ማውደሙን ተናግረዋል።

በጎርፍ አደጋው የተፈናቀሉ ነዋሪዎች በየቀበሌያቱ የመስተዳድር ጽህፈት ቤቶች ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙ የጠቀሱት ዋና አስተዳዳሪው በአሁኑወቅትም የዕለት ደራሽ ድጋፎችን ለማድረግ ከወዲሁ እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል።

<< እስከአሁን የአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ መስተዳድር ካቢኔ ትናንት አስቸኳይ ስብስባ በማድረግ ለተፈናቃዮቹ የምግብ አህል መግዣ የሚሆን አንድ ሚሊዮን ብር ለመስጠት ወስኗል። በጋሞ ዞንና በክልል ደረጃም ተመሳሳይ ድጋፎችን ለማድረግ የሚያስችሉ ጥረቶች በመደረግ ላይ ይገኛሉ >> ብለዋል።

በደቡብ ክልል የተፈጥሮ ደን መመናመንን ተከትሎ የሚከሰቱ ድንገተኛ አደጋዎች እየተበራከቱ መምጣታቸውን በየጊዜው የሚወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

በክልሉ በተያዘው ዓመት ብቻ በጋሞ ፣ በዎላይታ ፣ በዳውሮ ዞኖችና በኮንታ ልዩ ወረዳ በደረሱ የመሬት መንሸራተት አደጋዎች የበርካቶች ህይወት ማለፉ የሚታወስ ነው።

 

ሸዋንግዛዉ ወጋየሁ 

ልደት አበባ

አዜብ ታደሰ