በአማራ ክልል የኢንተርኔት መቋረጥ በባንክ፣ በግብረ ሰናይና የምርምር ሥራ ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ
ዓርብ፣ መስከረም 25 2016በአማራ ክልል የኢንተርኔት አገልግሎት በመቋረጡ በምርምር ስራ ላይ ጫና እየፈጠረ እንደሆነ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ተናገሩ። በማህበራዊ አገልግሎት የተሰማሩ ባለሙያዎች ደግሞ ከሌሎች አካላት የሚደረግ የመረጃ መለዋወጥ በመቋረጡ እርዳታ ያገኙ የነበሩ አካላት ለጉዳት እየተዳረጉ ነው ብለዋል፡፡
ከነሐሴ ወር መጀመሪያ ጀምሮ በአማራ ክልል በፋኖ ታጣቂዎችና በመከላከያ ሰራዊት መካከል የተፈጠረውን ጦርነት ተከትሎ በአማራ ክልል ለስድስት ወራት የሚዘልቅ የአስቸኳ ጊዜ አዋጅ ታውጇል፣ የኢንተርኔት አገልግሎትም በሁሉም የአማራ ክልል ከተሞች ከተቋረጠ ወራት እየተቆጠሩ ነው።
ዓለም በቴክኖሎጂ ድጋፍ ወደ አንድ መንደር እየተለወጠች ባለችበት በዚህ ወቅት የኢንተርኔት መቋረጥ የተለያዩ ተቋማትን ስራ እየጎዳ እንደሆነ አስተያየት ሰጪዎች እየተናገሩ ነው፡፡
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ በመተማ ከተማ የሚገኙ የባንክ ሰራተኛ የኢንተርኔት መቋረጥ በስራቸው ላይ ጫና እንደፈጠረባቸው ለዶይቼ ቬሌ በስልክ ገልጠዋ። እንደ ባለሙያው ከዋና መስሪያ ቤት ወደ ቅርንጫፎች የሚደረግ የስራ ግንኙነትና የየእለት የጽህፈት ቤቶችን የስራ አፈጻፀም ማወቅ እንዳልተቻለ ነው የገለጡት፡፡ ግብረ መልስ ለመስጠትና ለመደገፍም አስቸጋሪ ሆኗል ብለዋል፡፡
በባሕር ዳር ከተማ የአንድ ክፍለ ከተማ የሴቶች እና ህፃናት ባለሙያ በበኩላቸው 3000 የሚጠጉ ወላጅ የሌላቸው እና በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሴቶች እርዳታ የሚያገኙት መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በሚደረግ የመረጃ ልውውጥ እንደነበር ጠቁመው አሁን ግን አገልግሎቱ በመቋረጡ ድጋፉም ተቋርጧል ብለዋል፡፡ ለተማሪዎች የትምህርት ቤት ቁሳቁስ፣ ዩኒፎርምና ምገባ ማቅረብ እንዳልተቻለ ነው በምሬት የተናገሩት።
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ዶክተር ሳምሶን ጫኔ የኢንተርኔት መቋረጡ የሁለተኛና የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎች የሚፅፋቸውን የመመረቂያ ጽሁፎች ለማየት አላስቻለም፣ ተማሪዎች ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ጥረት ቢያደርጉም እንዳልተሳካ ነው የሚገልፁት፡፡ አጠቃላይ የዩኒቨርሲቲውን የምርምር ስራም አዳክሞታል ብለዋል፡፡
ሌላ በዩኒቨርሲቲው የጤና ባለሙያ የሆኑ መምህር በበኩላቸው የአገልግሎቱ መቋረጥ በግለሰቦችና በተቋማት ሠራ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ነው ብለዋል፡፡ በግላቸውም ኢንተርኔት መስራት ባለመቻሉ የውጪ ኮንፈረንስ እንዳመለጣቸው፣ የትምህርት እድሎችን የሚጋብዙ መልዕክቶችና ደብዳቤዎችን ማየት እንዳልተቻለ አብራርተዋል፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ እንደሚሰሩ የነገሩን ሌላ ባለሙያ የኢንተርኔት መቋረጥ በኢኮኒሚና ማህበራዊ አገልግሎቶች ላይ ኪሳራ እያስከተለ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ በአማራ ክልል ከኢንተርኔት መቋረጡ በተጨማሪ በበርካታ የክልሉ ከተሞች የስልክ አገልግሎትም ከተቋረጠ ሳምንታት ተቆጥረዋል፡፡
ዓለምነው መኮንን
እሸቴ በቀለ
ሸዋዬ ለገሠ