1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአማራ ክልል እያሳሰበ ያለዉ አለመረጋጋት

ዓርብ፣ ሚያዝያ 27 2015

በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ሰሞኑን አለመረጋጋቶች እንዳሉ የጎንደርና የሸዋ ሮቢት ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ። ከደሴ አዲስ አበባ የሚወስደው አውራ ጎዳና ሸዋሮቢት ላይ በመዘጋቱ እስከዛሬ እረፋዱ ድረስ የትራንስፖርት አገልግሎት አልነበረም። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በመግለጫ በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ግጭቶች መኖራቸውን አስታዉቋል።

https://p.dw.com/p/4Qwxj
Äthiopien Gondar | Bilder zur aktuellen Sicherheitslage
ምስል Nebiyu Sirak/DW

«በጎንደርና ሸዋ ሮቢት ከተሞች አለመረጋጋት ይታያል» ነዋሪዎች

በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ሰሞኑን አለመረጋጋቶች እንዳሉ የጎንደርና የሸዋ ሮቢት ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል፣ ከደሴ አዲስ አበባ የሚወስደው አውራ ጎዳና ሸዋሮቢት ላይ በመዘጋቱ እስከዛሬ እረፋዱ ድረስ የትራንስፖርት አገልግሎት አልነበረም ተብሏል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ግጭቶች መኖራቸውን አስታውሶ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ችግሮቹን በሰላም እንዲፈቱ ጠይቋል የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄም ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ ችግሮች በውይይት እንዲፈቱ ጠይቋል፡፡

Äthiopien Gondar | Bilder zur aktuellen Sicherheitslage
በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ እያሳሰበ ያለዉ ያለመረጋጋትምስል Nebiyu Sirak/DW

በአማራ ክልል በተለያዩ ምክንያቶች በአንዳንድ አካባቢዎች አገልግሎት መስጫ ተቋማትና የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት መዘጋታቸውንና አለመረጋጋት መኖሩን የየአካባቢ ነዋሪዎች አመልክተዋል፡፡ ከትናንት ከትናንት ጀምሮ በጎንደር ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት መቋረጡን፣ የህዝብ አገልግሎት መስጫ ተቋማትም መዘጋታቸውን አንድ የከተማዋ ነዋሪ ለዶይቼ ቬሌ ገልጠዋል፡፡

ሌላው የከተማዋ ነዋሪ በበኩላቸው በአማራ ክልል ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው ጫና ያሉት እየበዛ በመምጣቱን ነገሮችን ከውይይት ይልቅ በኃይል ለመፍታት እየተደረገ ያለውን አሰራር ለመቃዎም ነው እርምጃው የተወሰደው ብለዋል፡፡ በሰሜን ሸዋ ዞን ሸዋሮቢት ከተማ ከሁለት ቀን በፊት በመከላከያና በአካባቢው ታጣቂዎች መካከል ሞትን ያስከተለ ውጊያ እንደነበር አንድ የከተማዋ ነዋሪ ተናግረዋል፡፡

በሸዋ ሮቢት ከተማ አሁን የተረጋጋ ሁኔታ ቢኖርም፣ በዞኑ በአንዳንድ አካባቢዎች ግጭቶች እንዳሉ የገልፁልን እኝህ አተያየት ሰጪ፣ ከደሴ ወደ አዲስ አበባ የሚወስደው አውራ ጎዳና ግን ከተዘጋ ቀናት አልፈዋል ነው ያሉት፡፡ አንድ የደሴ ከተማ ነዋሪ በበኩላቸው ከሰሜን ወደ አዲስ አበባ የሚወስደው አውራ ጎዳና ከተዘጋ ከ4 ቀናት በላይ መሆኑን ጠቅሰው የደሴና የወልዲያ ባለጉዳዮች ከፍተኛ ወጪ በማውጣትና ረጅም ጉዞ በመጓዝ በአፋር በኩል ወደ አዲስ አበባ እንደሚጓዙ አብራርተዋል፡፡

Äthiopien Gondar | Bilder zur aktuellen Sicherheitslage
በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ እያሳሰበ ያለዉ ያለመረጋጋትምስል Nebiyu Sirak/DW

አስተያየት ሰጪዎቹ መንግስት ጉዳዮችን በወይይት እንዲፈታ ነው የጠየቁት፡፡ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሰሞኑን ባወጣው መግለጫም መንግስት “ከባለድርሻ አካላት ጋር በቀጥታ በመወያየት ለተፈጠሩ ችግሮች እልባት የመስጠት ግንባር ቀደም ኃላፊነቱን እንዲወጣ እናሳስባለን” ብሏል፡፡ አብን ለፋኖ፣ ለአማራ ወጣቶችና ለልዩ ኃይል አባላት ባስተላለፈው መልዕክት የህዝብ ሰላም እንዳይናጋ፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች እንዳይስተጓጎሉ የልማት ስራዎች እንዳይደናቀፉና በአካልና በህይወት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ሲል ጥሪ አስተላልፏል፡፡

“በአማራ ህዝብ ላይ ጦርነት ሲከፈትበት “ዳር ቆመው የነበሩ” ያላቸው አካላትም ዛሬ ድንገተኛ ወዳጂና ወኪል መስለው ግጭት ለማነሳሳት የሚያደርጉትን ጥረት እንዲያቆሙና ‘የሚያደርጉትን አደንቋሪ የጥፋት ጥሪዎች’ ያለውን ፈጽሞ እንዳይሰማ” ሲል አብን አስጠንቅቋልየኢትዮጵያ ሰብዐዊ መብት ኮሚሽን በበኩሉ ባወጣው መግለጫ፣ በአማራ ክልል በሰሜን ጎንደር፣ በሰሜን ወሎና በሰሜን ሸዋ አንዳንድ አካባቢዎች ግጭቶች መኖራቸውን ጠቅሶ፣ የሚመለከታቸው አካላት ችግሩን በውይይት እንዲፈቱና ሰብአዊ መብቶች ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ችግሩን የሚያባብሱ ነገሮችን እንዳያደርጉ አሳስቧል፡፡

ዓለምነው መኮንን

አዜብ ታደሰ

ዮኃንስ ገብረግዚአብሔር