1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በትግራይ አጽቢ ወረዳ በሶስት ወራት 111 ሰዎች በረሐብ መሞታቸውን ባለሥልጣናት ገለጹ

ሐሙስ፣ ኅዳር 27 2016

"አርሰን አምርተን እንበላ ነበር፣ ካልሆነ ደግሞ ወጣ ብለን ሰርተን እንበላ ነበር። አሁን ግን የት ልሂድ?" የሚሉት የ70 ዓመቱ አዛውንት ገብረማርያም ሓጎስ ቤተሰቦቻቸው በአጽቢ ወረዳ በተከሰተው ረሐብ ወደሌላ አካባቢ ሸሽተዋል። የወረዳው ኃላፊዎች በሶስት ወራት 111 ሰዎች በረሐብ መሞታቸውን ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል።

https://p.dw.com/p/4ZtHg
ድርቅ በእጅጉ ባጠቃው በትግራዩ በአጽቢ ወረዳ የሚገኝ መሪት
ድርቅ በእጅጉ ባጠቃው በትግራዩ በአጽቢ ወረዳ የሚገኝ መሬትምስል Million Hailesilassie/DW

የአፅቢ ወረዳ አስተዳደር ባለፉት ሶስት ወራት 111 ሰዎች በረሃብ መሞታቸውን ገልጿል

በትግራይ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ረሃብ የበርካቶችን ሕይወት እየቀጠፈ እንደሚገኝ ተገለፀ። ትላንት በትግራይ ክልል አፅቢ ወረዳ በሚገኙ የተለያዩ የገጠር አካባቢዎች ባደረግነው ቅኝት፥ ሰዎች የከፋ ሕይወት ላይ መሆናቸው ታዝበናል።

የአፅቢ ወረዳ አስተዳደር በወረዳዋ ብቻ ባለፉት ሶስት ወራት 111 ሰዎች በረሃብ መሞታቸውን ለዶቼቬለ ገልጿል። በአፅቢ የተለያዩ የገጠር ጣብያዎች መታዘብ እንደሚቻለው ወንዞችና የውሃ አካላት ደርቀዋል፣ የሰውና እንስሳት ምግብ ከፍተኛ እጦት ተከስቷል፣ ወጣቶች ተሰደዋል፣ አቅመ ደካሞች የከፋ ሕይወት ይገፋሉ።

አቶ ገብረማርያም ሓጎስ የተባሉ የአካባቢው በዋሪ "ረሃብ አለ፣ እየተራብን ነው። እኔ ችግር ላይ ነኝ። የምገዛበት ካገኘሁ ለዕለቱ እመገባለሁ። አንዳንዴ እበላለሁ ፥ ከሌለ ፆማችን ማደራችን ነው። የት እንሄዳለን ? ምን እናረግ ታድያ" ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። 

እኝህ የ70 ዓመት አዛውንት ገብረማርያም ሓጎስ በቀዬአቸው የትግራይ ምስራቃዊ ዞን አፅቢ ወረዳ ጉደም ተብሎ የሚታወቅ አካባቢ ያገኘናቸው የወዳደቁ ጥራጥሬዎች ለቃቅመው በመሰብሰብ ለምግብነት ለማዋል ሲሞክሩ ነው።

እኝህ አባት "እንደ ወፍ ጥሬ እየለቀምኩኝ ነው" ይላሉ በሰለለ አንደበታቸው። አሁን ላይ በሰፊው በቤታቸው ብቻቸው የሚኖሩት አዛውንቱ አቶ ገብረማርያም ልጆቻቸው እና ሚስታቸው ጨምሮ መላ ቤተሰባቸው በረሃብ ምክንያት ወደተለያየ ቦታ መሰደዳቸው ነግረውናል።

ድርቅ ባጠቃው በትግራይ በምትገኘው በገጠርዋ አጽቢ የሚኖሩት አቶ ገብረ መድኅን ሐጎስ ሞታችንን እየጠበቅን ነው ይላሉ
ድርቅ ባጠቃው በትግራይ ገጠርዋ አጽቢ የሚኖሩት አቶ ገብረ መድኅን ሐጎስ ሞታችንን እየጠበቅን ነው ይላሉምስል Million Hailesilassie/DW

ያለፈው ክረምት በትግራይ በቂ የዝናብ ስርጭት ባለመኖሩ በተለይም በክልሉ ሶስት ዞኖች ድርቅ መከሰቱ የተገለፀው ባለፈው መስከረም ወር ነበር። ይህ ድርቅ አሁን ላይ በአብዛኞዎቹ የትግራይ አካባቢዎች የሰው እና እንስሳ ምግብ ወደማይገኝበት ረሃብ እየተቀየረ ይገኛል።

ትላንት በትግራይ ክልል አፅቢ ወረዳ በሚገኙ የተለያዩ የገጠር አካባቢዎች ባደረግነው ቅኝትም ፥ ሰዎች የከፋ ሕይወት ላይ መሆናቸው ታዝበናል። የአፅቢ ወረዳ አስተዳደር በወረዳዋ ብቻ ባለፉት ሶስት ወራት 111 ሰዎች በረሃብ መሞታቸው ለዶቼቬለ ገልጿል።

በአፅቢ የተለያዩ የገጠር ጣብያዎች መታዘብ እንደሚቻለው ወንዞችና የውሃ አካላት ደርቀዋል፣ የሰውና እንስሳት ምግብ ከፍተኛ እጦት ተከስቷል፣ ወጣቶች ተሰደዋል፣ እንደ አቶ ገብረመድህን የመሰሉ አቅመ ደካሞች የከፋ ሕይወት ይገፋሉ።

ድርቅ በትግራይ

"አርሰን አምርተን እንበላ ነበር፣ ካልሆነ ደግሞ ወጣ ብለን ሰርተን እንበላ ነበር። አሁን ግን የት ልሂድ? አይኔም እየከዳኝ ነው። የምሸጠው በግ የለኝ፣ በሬ የለኝ ምንም ነገር የለኝም። ሰውነቴ አይቶ መረዳት ይቻላል" ይላሉ። ሌላዋ በአካባቢው ያነጋገርናቸው እናት ወይዘሮ ፍፁም ወልደገብርኤል ባለፈው ክረምት በአካባቢያቸው ሁለት ግዜ ብቻ ዝናብ መዝነቡ፣ የዘንድሮው የዝናብ እጦት የከፋ መሆኑ የሚያነሱ ሲሆን እንደዚህ ዓይነት የድርቅና ረሃብ ግዜ በሕይወቴ አጋጥሞኝ አያውቅም በማለት ያክላሉ።

ወይዘሮ ፍፁም "የዘራነው ሁሉ አንድም አልበቀለም። መክኖ ነው የቀረው። አሁን ረሃብ ሆነ በሀገሩ። እናቴ ከምትወልደኝ እንዲህ ዓይነቱ ረሃብ አላየሁም አልሰማሁም። ድሮ ችግር ሲመጣ ተሰደህ ሄደህ ይበላ ነበር። አሁን ለመሰደድም ጉልበት የለንም" ይላሉ።

በአጽቢ ወረዳ ለረሃብ የተጋለጡ እናት
በድርቅ ክፉኛ የተጎዳው አጽቢ የሚኖሩ እናት ምስል Million Hailesilassie/DW

ተራድኦ ድርጅቶች በትግራይ የረሀብ አደጋ ተደቅኗል አሉ

እንደ አቶ ገብረማርያምም ቢሆኑ "እግዚአብሔር ያመጣው ምን ይታወቃል ? ካገኘን ከረዳን እንበላለን፥ ካላገኘን እንሞታለን። ምንም ማድረግ አይቻልም" ባይ ናቸው።ሁኔታው እንዲህ እንዳለ ዓለምአቀፍ ስብአዊ እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች ይሁኑ መንግስት ለተራቡት የምግብ እርዳታ እያቀረቡ እንዳልሆነ ነዋሪዎች ነግረውናል። የአፅቢ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ መዝገበ ግርማይ ሁኔታው ከቁጥጥር ውጭ እየወጣ ስለመሆኑ ይገልፃሉ። 

እንደ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር መረጃ በአሁኑ ወቅት በትግራይ 2 ሚልዮን ዜጎች ለረሃብ ተጋልጠው ይገኛሉ። አሁን ላይ ለረሃብ ተጋልጠው ካሉ የማሕበረሰብ ክፍሎች በተጨማሪ የእርዳታ ለጋሾች እጅ የሚጠብቁ 1 ነጥብ 1 ሚልዮን ተፈናቃዮች በትግራይ በከፋ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ይገለፃል። እርዳታ ማቅረብ አቋርጠው የቆዩ ዓለምአቀፍ ለጋሾች በቅርቡ በትግራይ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ሰብአዊ ስራቸው እንደሚቀጥሉም ተስፋ ሰጥተው ነበር።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

ኂሩት  መለሰ

አዜብ ታደሰ